በአለም አትሌቲክስ ትልቅ ትኩረት ከሚሰጣቸው አንዱ የሆነው የዱባይ ማራቶን በየአመቱ ሲካሄድ ሁሌም በውጤት ረገድ ተመሳሳይ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለእነሱ ብቻ የተዘጋጀ ውድድር እስኪመስል በዱባይ ማራቶን በሁለቱም ፆታ ሁሌም ፍፁም የበላይነት አላቸው። ይህ የበላይነት ደግሞ ቀዳሚዎቹን ደረጃዎች ይዞ በማጠናቀቅ ብቻ የተገደበ አይደለም። በሁለቱም ፆታ ከአንድ እስከ አስርና ከአንድ እስከ ሃያ በማጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ባለፉት በርካታ አመታት ፍፁም የበላይነት አላቸው። በዚህ ውድድር ሁሌም የየትኛው አገር አትሌት ያሸንፋል የሚለው ጉዳይ ሳይሆን የትኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ያሸንፋል ወይም ፈጣን ሰአት ያስመዘግባል የሚለው ጉዳይ ትኩረት ይስባል።
የዱባይ ማራቶን የኮቪድ-19 ወረርሽን ከተከሰተ ከ2019 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ ሲካሄድም በውጤት ረገድ የተለየ ታሪክ አልተፈጠረም። ለአመታት የዘለቀው የኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዱባይ ማራቶን የበላይነት ለሃያ ሁለተኛ ጊዜ ባለፈው እሁድ ሲካሄድም በሁለቱም ፆታ ከአንድ እስከ አስር በማጠናቀቅ ቀጥሏል።
በዘንድሮው የዱባይ ማራቶን የታየ አንድ አዲስ ወይም የተለየ ነገር ቢኖር ውድድሩ በአንድ ቤተሰብ የበላይነት መጠናቀቁ ነው። ሃያ ሁለተኛውን የዱባይ ማራቶን በወንዶች የሃያ ሁለት አመቱ አትሌት አብዲሳ ቶላ በ2:05:42 ሰአት ሲያሸንፍ፣ በሴቶች ዴራ ዲዳ 2:21:11 በመግባት አሸናፊ ሆናለች።
ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሮጦ አሸናፊ የሆነው አብዲሳ ቶላ የወቅቱ የማራቶን የአለም ቻምፒዮኑ አትሌት ታምራት ቶላ ታናሽ ወንድም ሲሆን፣ በሴቶች መካከል የተካሄደውን ውድድር በበሳል ታክቲክ ከወሊድ ተመልሳ ማሸነፍ የቻለችው ዴራ ዲዳም የታምራት ቶላ ባለቤት ናት። ይህም በውድድሩ የታየ አንድ አዲስ ነገር ሆኖ በአለም መገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።
ወጣቱ አትሌት አብዲሳ ቶላ ከዘንድሮው የዱባይ ማራቶን በፊት አርባ ሁለት ኪሎ ሜትር ተወዳድሮ ባያውቅም በግማሽ ማራቶን 59:54 የሆነ የራሱ ፈጣን ሰአት አለው። በዚህም ዱባይ ላይ በማራቶን የተሻለ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች በድንቅ የአጨራረስ ብቃት ለማሸነፍ አልከበደውም። ያምሆኖ ከታላቅ ወንድሙ የተሻለ ፈጣን ሰአት ማስመዝገብ አልቻለም። ታላቅ ወንድሙና የአለም የርቀቱ ቻምፒዮን ታምራት ቶላ በዱባይ ማራቶን እኤአ 2017 ላይ 2:04:11 በሆነ ሰአት ማሸነፉ ይታወቃል።
አዲሱን የዱባይ ማራቶን ቻምፒዮን ተከትሎ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ደሬሳ ኡልፋታ 2:05:51 በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው ሰአት በርቀቱ የግሉ ፈጣን ሰአት መሆን ችሏል። 2:05:58 በማጠናቀቅ አስደናቂ ፉክክር ያደረገው አትሌት ሃይማኖት አለው በሰባት ማይክሮ ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ ሶስተኛ ደረጃን መያዝ ችሏል።
በድንቅ የታክቲክ ፍልሚያ የታጀበው የሴቶች ውድድር አሸናፊ የሆነችው ዴራ ዲዳ ባለፉት ሶስት የማራቶን ውድድሮቿ ከ2:21:45 የፈጠነ ሰአት ርቀቱን ማጠናቀቅ አልቻለችም ነበር። በነዚያ ውድድሮቿ ከአምስተኛ ደረጃ የተሻለ ውጤት ይዛ ማጠናቀቅም አልቻለችም ነበር። እንደ ቤተሰብ ውጤታማ በሆኑበት የዘንድሮ የዱባይ ማራቶን ግን ከወሊድ ተመልሳ ቀዳሚ ሆና ከማጠናቀቅ ባለፈ ያስመዘገበችው ሰአትም በርቀቱ የግሏ ምርጥ ሰአት ሆኖ ሊመዘገብላት ችሏል።
ቀዳሚ ሆና ያጠናቀቀችው ዴራን ተከትላ የ2019 ቶኪዮ ማራቶን ቻምፒዮኗ አትሌት ሩቲ አጋ 2:21:24 በሆነ ሰአት ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ አትሌት ስራነሽ ይርጋ 2:21:59 በሆነ ሰአት ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሩን ፈጽማለች።
ባለ ድሉ አትሌት አብዲሳ ቶላ ከውድድሩ መጠናቀቅ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን አስተያየቱን ሲሰጥ “ ለዚህ ውድድር በደንብ ተዘጋጅቻለሁ፣ እንዳሸንፍ የረዳኝም ይሄው ምክኒያት ነው፣ በውድድሩ ወቅት የነበረው የአየር ጸባይ ጥሩ ቢሆንም መጠነኛ ወበቅ ነበር፣ ለዚህም ቢሆን ጥሩ ተዘጋጅቼ ቀሪውን ስራ ለፈጣሪ ሰጥቼ ነበር” በማለት ተናግሯል።
የሴቶቹ ባለድል አትሌት ዴራ በበኩሏ፣ “በጥሩ ፉክክር የታጀበ አስደናቂ ውድድር ነበር፣ እኔም እዚህ የተገኘሁት ለማሸነፍ ነው፣ ውድድሩ በታክቲክ ፉክክር የጠነከረ ቢሆንም ፈጣሪ ረድቶኛል፣ ይህን ውድድር እንደማሸንፍ በራስመተማመን ነበረኝ ይህም ባለድል ለመሆን ጠቅሞኛል” በማለት አስተያየቷን ሰጥታለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም