አንድ ማኅበረሰብ በብዙ ፈተናዎች እና ውጣ ውረዶች ያልፋል። በድቅድቅ ጨለማ ተከቦ መውጫ የሚያጣበት፤ ዙሪያ ገባው ገደል የሚሆንበት ጊዜያት ብዙ ናቸው። የፈተናዎች መብዛት ጨለማውን የማይሻገረው፣ ተራራውን የማያልፈው መስሎ እንዲታይ ቢያደርገውም ከጨለማው በኋላ ብርሃን፣ ከገደሉ ውጪ ሰፊ ሜዳ መኖሩ ማሰብ ተገቢ ነው።
የቀደሙት አባቶቻችን “የማይገል ፈተና ያጠነክራል” ይላሉ። የማኅበረሰብን መንፈስ የሚረብሹ፣ ሕልውና የሚፈታተኑ፣ ትዕግስትን የሚገዳደሩ ጉዳዮች ይገጥሙናል። ጭራሽኑ የማያጠፉን እክሎች ለጊዜው ግን የጭቃ ውስጥ እሾክ ሆነው አላራምድ ይሉናል። ያን ጊዜ ነው ከቀደሙት አያቶቻችን ፈተናዎችና ብልሃቶች ለመማር የምንገደደው ።
ከመናወጥ ወዲያ መስከን፣ ከወጀቡ በኋላ ሰጥ ያለና የተረጋጋ ውቅያኖስ፣ ከፍፁም ተስፋ ማጣት ወደ ተረጋጋ ስብዕናና ስኬት እንደምንደርስ ከዛሬ ሳይሆን ትናንት ህያው ከነበሩ አባቶቻችን ታሪክ ለመማር የመነቃቃታችን እውነታ ችግሮቹን አሸንፈን ለመሻገር ትልቅ አቅም ይፈጥርልናል።
ለዚህ ደግሞ “ለመሆኑ ከዚህ ቀደም የት ነበርን? ዛሬስ የቱ ጋር ነው ያለነው?” ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አሁን ሳይሆን ከሺህ ዘመናት ወዲህ በብዙ መልኩ ተፈትነዋል። አያት ቅድመ አያቶቻችን ይገቡበት ስፍራ ይሸሸጉበት ጥግ አጥተው ቀኑ ጨለማ የሆነባቸው ጊዜያትን ዞር ብለን ብንመለከት በብዙ መልኩ ትምህርት ልንወስድ እንችላለን።
እንዲያውም ዛሬ ሰቅዘው ለያዙንና እንፈታቸው ዘንድ ብልሃት ላጣንላቸው ስብራቶቻችን መፍትሔ እንደምናገኝ አያጠራጥርም። “በሽታውን ያወቀ መድኃኒት አያጣም” እንዲሉ ሕመሞቻችን ምን እንደሆኑ ዞር ስንል አቧራ የለበሱ የታሪክ ዶሴዎቻችን ይነግሩን ይሆናል። እኛ ግን ከትናንት ታሪኮቻችን ለመማር እንደ ማኅበረሰብ ምን ያህል ዝግጁ ነን?
ኢትዮጵያውያን ከሦስት ሺህ ዓመት ዘለግ ያለ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ ታሪክ የነበረን እና በቀደምት ሥልጣኔ የዓለም ቁንጮ ባለታሪኮች ነን። ይህ አኩሪ ማንነታችን ግን መንገራገጭ የሌለበት አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ ወደ ኋላ መሄድ ሳይጠበቅብን ከ1760 እስከ 1847 ዓም ያለውን ታሪካችንን ብናገላብጥ ንጉሠ ነገሥታቸውን ንቀው፣ ጡንቻቸውን አፈርጥመውና “በማን ያህለኛል” ልባቸውን አሳብጠው በነበሩ መሳፍንቶች ኢትዮጵያውያን የሚጨነቁበት ዘመን እንደነበር መጥቀስ ይቻላል።
ዜጎች ይመሩበት ሥርዓት፤ይገብሩበት አስተዳደር አጥተው ልባቸው፣ ሃሳባቸው፣ መንፈሳቸውና አንድነታቸው እንደ አምባሻ ከብዙ ቦታ ተቆራርሶ ወደ ፈጣሪያቸው አንጋጠው ጥሩ ቀን እንዲመጣ የሚለምኑበት ግዜ ነበር።
“ኢትዮጵያዊነት ብዙ ሺህ ዘመናትን የተሻገረ ነው” የምንለው ምንም ችግር ሳይገጥመው እንደ ጅረት ኩልል ብሎ ፈስሶ ሳይሆን አለት ከሆኑ ችግሮች ጋር ተላትሞ፣ ጥልቅ ወደሆኑ ፈተናዎች ቁልቁል እንደ ፏፏቴ ውሃ ተፈጥፍጦ ከሰከነው ውቅያኖስ ጋር እንደሚቀላቀል ውሃ ባሕሪን ተላብሶ እንደሆነ ስለምንረዳ ጭምር ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ጥንትም በአያሌ መንገራገጭና መጣረዞች ውስጥ አልፏል። ኢትዮጵያውያን በአስተዳዳሪያቸው ብቻ ሳይሆን በማኅበራዊ መሪዎቻቸው፣ በተፈጥሮ፣ በውጪ ወራሪ በልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ ተፅዕኖዎች ተፈትነዋል። ያ ሁሉ ግን ዛሬ ታሪክ ሆኖ ትውልድ የራሱን ውጣ ውረዶች እንዲመዝንበትና ትምህርት እንዲቀስምበት በዶሴዎች ላይ ተከትቦ ይገኛል።
ግዜው በ1888 ነው። ዓድዋ ላይ ውቅያኖስ አቋርጦ ሐቃችንን ሊበላና በግዞቱ ስር ሊያደርገን ያሰፈሰፈ የፋሺስት ጣሊያንን ጦር ሉዓላዊነታችንን ደፍሮ ድንበራችንን ጥሶ እደጃፋችን ጦር ሰብቆ የወረረን ወቅት። ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያውያን ከባድ የሕልውና ፈተና የተጋረጠብን ጊዜ። ይህ ጥቁር ቀን ግን አብዝቶ ይፈትነን እንጂ አንድነታችንን ገዝግዞ አልጣለውም። በእሳት ውስጥ ተፈትኖ እንደሚወጣ ወርቅ ክርናችንን አፈርጥሞ ድልንና ማሸነፍን፣ ኅብረትና አንድነትን፣ መተባበርና ፍቅርን አስተምሮን አለፈ። ፋሺስት ጣሊያን የሽንፈት ካባ ተከናንቦ የኢትዮጵያን ምድር ለቆ ወጣ።
ይሄ በውጪ ጠላት የተቃጣብን የመጀመሪያውም የመጨረሻውም ጥቃት አልነበረም። አያሌ ጊዜያት መሰል ሕልውናችንን የፈተኑ፣ገንድሰው ሊጥሉን ከጫፍ ደርሰው ብዙ ሙከራዎች ነበሩ። እንደ ሕዝብ በጋራ የደማንባቸው፣ በአንድነት የቆሰልንባቸው፣ አልፎ ቀና ያልን ቢሆንም አንገታችንን የደፋንባቸው እዚህም እዚያም የነበሩ የታሪክ ክፍሎች ነበሩን።
ለበቀል ያሰፈሰፈው ጣሊያን ከ35 ዓመታት በኋላ ዳግም ኢትዮጵያን በመውረር ብዙ አትዮጵያውያንን በግፍ ለሞት የዳረገበት የጥቁር መዝገባችን ለዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል። የዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) የተመሠረተ ቢሆንም ኢትዮጵያ ለዚሁ ማኅበር የዳግም የበቀል ወረራው በተመለከተ አቤት ብትልም አጋርነት ካሳዩ ጥቂት ሀገራት ውጭ ሰሚ ያጣችበትና በዓለም ሀገራት የተከዳንበት የጥቁር የኃዘንና የመከራ ታሪክ ክፍል አለን።
ኢትዮጵያውያን አንድ ሆንን። ደጋግሞ ዳር ድንበራችንን ሊፈትን የመጣን ጠብ አጫሪ አደብ ለማስገዛት አበርን። አርበኞች ሀገርን ላለማስደፈር ከፍተኛ ተጋድሎ አደረጉ። ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ የጣሊያንን ድርጊት ለማስወገዝና በሕዝባቸው ላይ የተደቀነውን ፈተና ለማስቀረት ቢሞክሩም ሰሚ ሳያገኙ ቀርተው ለስደት ተዳረጉ።
በዚህ አስከፊ ግዜ ግን አውራውን እንዳጣ የቀፎ ንብ ሳይሆን እራሱንና ማንነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ መሠረቱንና የተገነባበትን ፅኑ አለት የሚገነዘብ ኢትዮጵያዊ በዱር በገደሉ እራሱን ሰውቶ ፋሽስትን ዳግም አሳፍሮ ወደመጣበት መለሰው። ይሄ የሚያሳየን ኢትዮጵያዊነት በፈተናዎች ውስጥ ቢያልፍም የማይበገር መሆኑን ነው።
ማኅበረሰባችንን ሰቅዘው የያዙ ፈተናዎች መቼም ቢሆን የሚያበቁ አይደሉም። በየዘመናቱ እረፍት እየወሰዱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ይገዳደራሉ። የተፈጥሮ ድርቅ የማኅበረሰቡን ሌማት ባዶ አድርጎት ያውቃል። ገበሬም የሚዘራው ይቅርና የሚቀምሰው አጥቶ ነበር። ወረርሽኝ መልሶ መላልሶ ጎብኝቶናል።
የኅዳር በሽታ ተብሎ የሚታወቀው የአንደኛውን የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ተከትሎ የተከሰተውና በመላው ዓለም ለ200 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው የእስፓኒሽ ፍሉ ወረርሽኝ የዚህ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
መርስኤ ኃዘን ወልደ ቂርቆስ “የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ” በተሰኘ የታሪክ መጽሐፋቸው ላይ እንደከተቡት በ1911 ዓ.ም የበሽታ መቅሰፍት በኢትዮጵያ ላይ ወርዶ ነበር። በዚያ ምክንያት ብዙ ሰው ማለቁን በታሪክ ክታባቸው ላይ አጫውተውናል።
መለስ ብለን ከተመለከትን የተፈተንባቸው እልፍ ጉዳዮች አሉ። የማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ስንክሳሮች ከግራም ከቀኝም ጎነታትለውናል። ልንወድቅ ጫፍ ደርሰን ከአፋፍ ተመልሰን እናውቃለን። ጠላቶቻችን ገዝግዘው የጣሉን የመሰላቸው ግዜ ዳግም በሁለት እግራችን ቆመን እናውቃለን።
የእርስ በእርስ ግጭቱ፣ እርዛቱ፣ የውጪ ወራሪው የተፈጥሮ ቁጣው ብቻ በየዘርፉ ያልጎነተለን ጉዳይ ያልዳሰሰን መከራ አልነበረም። 50 እና 60 ዓመታትን መለስ ስንል እሁንም ድረስ ባለቀቀን የዘርና የጎጥ አባዜ ተፈትነናል። “ቀይ ሽብር” “ነጭ ሽብር” በሚል ተቧድነን ለቁጥር የሚታክቱ ዜጎቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል። እናቶች አልቅሰዋል። ሀገር ምሑራኖቿን፣ የማኅበረሰብ መሪዎችና ሽማግሌዎችን አጥታ ታላቅ ድብታ ውስጥ ገብታ ታውቃለች።
በ”ቸ” እና በ”ች” ሳይቀር ተጣልተናል። አርሶና ቆፍሮ የሚያበላን ገበሬ ለራሱ መቆም ሳያቅተው ለፖለቲካዊ ትርፍና ንግድ በነቀዙ የምዕራብ ሀገራት ፍልስፍና አስጨንቀውን እናውቃለን። እነዚህ ሁሉ ከጉድለቶቻችን ውስጥ የሚመደቡ፤ ከገጠሙን ወጣ ገባዎች ተርታ የሚሰለፉ ጥቁር ጠባሳዎቻችን ናቸው። ግን አንደ ሀገር አፈረሱን? እንደ ሕዝብስ አጠፉን? በፍፁም።
ዛሬስ? ዛሬም በመልካም ዕድሎች መካከል እንደቀደመው የታሪኮቻችን አካል ብዙ ጋሬጣዎች ከፊታችን ተደቅነዋል። አሁንም እንድንጎድል፣ እረፍት አልባ እንድንሆንና ስለ እድገታችን እንዳናማትር የሚጋርዱን መሰናክሎች በየጋቱ ተደንቅረዋል። አስተሳሰባችንን የሚፈትኑ፣ አንድነታችንን የሚጋርዱ፣ በፍቅርና በመተሳሰብ የሰከነ ሕይወት እንዳንመራ ሌት ተቀን ዕረፍት የሚነሱ አጀንዳዎች እዚህም እዚያም ተኮልኩለው ይታያሉ።
እንደ “ዘመነ መሳፍንት” በጎጥ ሸንነው በጎበዝ አለቆች ሊመሩን የሚሹ የውስጥ ሸረኞች ብቅ ብቅ እያሉ ነው። በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሰመሩ ቀይ መስመሮችን ነፍስ እንደማያውቅ ጨቅላ የሚጎነታትሉም እንዲሁ በየስፍራው እንደትናንቱ ዛሬም አሉ። የውጪ ቀበኞቻችን የትናንቱን ጠንካራ ክርናችንን ዘንግተው በብዙ መልኩ ይፈታተኑናል።
አንድነታችን በፅኑ መሠረት ላይ የቆመና ጠንካራ “ኢትዮጵያ!” የሚል አለት የሆነች አገር የገነባን ቢሆንም በሕዝቦች መካከል ጠብን የሚጭሩ፣ የሀገር ምልክትና ባለውለታ የሆኑ ታላላቅ ተቋማትን ለመናድ አይናቸውን በጨው አጥበው ፍም እሳት ውስጥ እጃቸውን የሚከቱ ዛሬም እንደ ትናንቱ አልጠፉም።
ለዚህ ነው ትናንት የት ነበርን? ዛሬስ ምኑ ጋር እንገኛለን? ከታሪክስ ምን እንማራለን ብለን ለመጠየቅ የምንገደደው። የጠቃቀስናቸው ውጣውረድና ፈተናዎች በዘመን ዑደት ውስጥ ተከስተው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊ መንፈስን የመበተን አቅም ከሌላቸው፤ የሺህ ዘመን ባሕል፣ ማንነት፣ ጠንካራ ሉዓላዊነትን የማነቃነቅ ኃይሉን ካላገኙ፤ ዛሬ ብልጭ ብለው ነገ ለሚከስሙ ነገር ግን እኛነታችንን ለማይለውጡ ፈተናዎች ስለምን እንበገራለን? ፤ስለምንስ እንርዳለን? ።
እንደቀደሙት አባቶቻችን በፈተና ቀን ፀንቶ መቆም፣ አንድ ሆኖ መገኘት፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትና መልክን እንደ አለት ማጠናከር ከእኛ የሚጠበቅ የትውልዱ የቤት ሥራ መሆኑን እንገንዘብ። ታሪክ እራሱን ሲደግም እኛም የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን እናስመስክር። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም