የሕግ ታራሚ አስናቀች ጌታቸው ቃሊቲ የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት በ2006 ዓ.ም ነው የገባችው። የ20 ዓመት የነፍስ ግድያ ፍርደኛ በመሆኗ አሁንም የቅጣት ጊዜዋን እየፈፀመች ትገኛለች። እሷ ጥፋተኛ በተባለችበት የነፍስ ወንጀል ተከሳሾች ሰባት ነበሩ። ቅጣቱ የተጣለባቸው በዛው በተከሰሱበት 2006 ዓ.ም በወጣው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት እንደሆነም ታወሳለች። በወቅቱ ሰባራ ባቡር ተብሎ በሚጠራውና አሁን አራዳ በተባለው እሷ በቀረበችበት ፍርድ ቤት ከታሰረችበት አዲስ አበባ ፖሊስ 23 ጊዜ ተመላልሳ ውሳኔ አገኘች። ውሳኔ ያገኘችው በሦስት ዓመት ከሰባት ወሯ መሆኑንም ታነሳለች።
‹‹እንደ ወንጀል ሕግ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች ሲከናወኑ አንድ ሰው ጥፋተኛ ሊሆን ይችላል›› የምትለው ታራሚዋ ከሦስቱ አንዷ እሷ እንደነበረችና ለሟቹ ምክንያት እኔ ነኝ ብላ ቃሏን በመስጠቷ እንደተፈረደባትም አጫውታናለች። እሷ እንደምትለው ከሟች ቤተሰቦች ጋር በኦሮሞ ገዳ ሥርዓት በአገር ሽማግሌ እርቅ ፈፅማ የፍርድ ሂደቷን በመከታተል ላይ ትገኛለች።
ከዚህ ቀደም በማረሚያ ቤቱ የሞት ፍርደኛ ከብዙ መብቶች ይገለል ነበር። ትምህርትም አይማርም ነበር። በአሁኑ ሰዓት ግን የሞት ፍርደኛ በዕድሜ ልክ ተፈቅዶለት ከመሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ፈለገው ድረስ የሚማርበት ዕድል ተመቻችቶለታል። እሷም ብረታ ብረትና ኮምፒውተርን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች በመሰልጠን ትሠራለች። ምርቶቿን በመሸጥም ተጠቃሚ ሆናለች።
ታራሚዋ እንደነገረችን በሙያዋ ፖሊስ የነበረች በመሆኗ ማረሚያ ቤት ከመግባቷ በፊት የነበረውን አብዛኛውን ጊዜዋን በስልጠና ነው ያሳለፈችው። በመሆኑም ነገ ዛሬ እያለች ትዳር ቶሎ አልያዘችም። እንዲህም ሆኖ በ2006 ዓ.ም ወደ ማረሚያ ቤቱ ልትገባ አካባቢ ትዳር መሥርታና የራሷን ጎጆ ቀልሳ ነበር። ነገር ግን ልጅ አልወለደችም። ልጅ ሳትወልድ ዘንድሮ በማረሚያ ቤት ውስጥ ሆና 38ኛ ዓመቷን ይዛለች። የመውለጃ ጊዜዋ ሊያከትም ጥቂት ዓመታት ብቻ ቀርተዋታል። ሆኖም መውለድ ሰብዓዊ መብት ነው በመሆኑም የግድ መውለድ አለብኝ የሚል አቋም አላት።
ታራሚው ባትወልድም በማረሚያ ቤት ቆይታዋ በማረሚያ ቤቱ ያሉ ሴት ታራሚዎችን ልጆች እንደ ልጆቿ ተንከባክባ አሳድጋለች። በማረሚያ ቤቱ ካሉት ሴት ታራሚዎች ቀደም ብላ ወደ ማረፊያው መግባቷ ሕፃናት ልጆቻቸውን እንድትንከባከብላቸው አስችሏታል። አስናቀች የታራሚ ሴት ኮሚቴ አባልም ነች። በኮሚቴው በኩል ከማረሚያ ቤቱ ጋር በመሆን ከማረሚያ ቤት መልካም ትምህርት አያገኙም በሚል ልጆቻቸው ወደ ሕፃናት ማሳደጊያ እንዲሄዱ ትሠራለች። አንዲት የምትወዳትና እንደ ልጇ ተንከባክባ ያሳደገቻት ሕፃን ሰላም የተሰኘ የሕፃናት መንደር እንድትሄድ በማድረጉ ሚና አላት። ይህችን ልጅ እንደ ልጇ ታያትና ትቆጥራት ስለነበር ስትነጠላት አብዝታ እንዳለቀሰችም ታራሚዎችና የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ይመሰክሩላታል።
ሆኖም ማረሚያ ቤት ለሕፃን መልካም ሥፍራ ባለመሆኑ ልጅቱ ከዛ በመራቋ ደስተኛ ነበረች። ግን ደጋግማ እንደምትለው ልጅ መውለድ የሰብዓዊ መብት በመሆኑ ሴት እስረኞች የመውለድ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ስትል ትጠይቃለች።
በዚህ በቃሊቲ የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ቤት እንደ አስናቀች ልጅ ያልወለዱ ሌሎች ታራሚዎችም አሉ። የመውለጃ ዕድሜያቸው በእስር ሊያልፍባቸው መሆኑ አብዝቶ እንደሚያሳስባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ። የመውለጃ ጊዜያቸው በዛው በእስር ቤት ያለፈባቸው ታራሚዎችም ይገኛሉ። እነዚህም የመውለጃ ጊዜያቸው በማለፉ አብዝተው የሚቆጩበት ሁኔታ አለ።
በተለያየ ደረጃ ያሉ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ይሄንን ያውቁላቸዋል። በተለይ ሴቶቹ ሕግ ማስከበሩ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እንደ ወላድ ሴት የመውለድ ሰብዓዊ መብት ስሜታቸውን ይጋሩላቸዋል።
‹‹ስሜታቸው ይሰማኛል››ይላሉም በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ምክትል ኮሚሽነር ዓለም ጥላሁን፤ምክትል ኮሚሽነሯ በተለይ የሕግ ታራሚ አስናቀች አብዝታ ልጅ ስለመውደዷና መውለድ ስለመፈለጓ እንደሚያውቁ ይናገራሉ። እንደ አስናቀች ሁሉ ሌሎችም ታራሚዎች የመውለጃ ዕድሜያቸው ሳያልፍ በብርቱ መውለድ መፈለጋቸውን ይጠቅሳሉ። ይሄ የታራሚዎቹ ፍላጎትና ሁኔታ እንደማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር በተለይም እንደ ሴትና ኃላፊም የሚሰማቸው መሆኑን ይገልጻሉ፤በተለያዩ መድረኮች የታራሚዎቹን ሀሳብ በማንሳት የሚያንፀባርቁ መሆናቸውንም ይናገራሉ። የመውለጃ ጊዜያቸው በእስር ምክንያት የሚያልፋቸውና ዘር የመተካት ዕድል ያጡ ታራሚ ሴቶች የመውለጃ ጊዜያቸው ሳያልፍ የሚወልዱበት ሁኔታ ቢመቻች እንደሚፈልጉም ያወሳሉ ምክትል ኮሚሽነር ዓለም።
ሰው ወንጀል የሚሠራው በማወቅም ባለማወቅም፤ በቸልተኝነትም እንደሆነ ደጋግመው የሚያወሱት ምክትል ኮሚሽነሯ የሰው ልጅ አንዳንድ ጊዜ ለሰኮንድ መታገስ እያቃተው ትልቅ ወንጀል ውስጥ በመግባት ብዙ መብቶቹን የሚያጣበት ወይም ሊያሳካቸው በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ የሚገባበት ጊዜ እንዳለም ይጠቅሳሉ። ይሄን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቢያንስ ሴት ታራሚዎች የሚወልዱበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም መሆኑንም ያብራራሉ። ‹‹ፈጣሪ ከፈቀደለት የሰው ልጅ ዘር ተክቶ ቢያልፍ መልካም ነው››ሲሉም ያክላሉ።
ይሁንና ይሄ የሴት ታራሚዎች በእስር ምክንያት መውለጃ ዕድሜ ማለፍ ጉዳይ እንደ ማረሚያ ቤት እስከ አሁን ከመድረክ ግብዓትነት ባለፈ የተሠራበት አለመሆኑንም ይናገራሉ። በጉዳዩ ላይ ከሰብዓዊ መብት አንፃር መሠራት አለበት የሚልም እምነት አላቸው ምክትል ኮሚሽነሯ ።
ይሄ የሕግ ታራሚ ሴቶች መብት በሕግ ዓይን እንዴት እንደሚታይ የሕግ ባለሙያም ጠይቀን ነበር። በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ21 ዓመታት ያገለገሉት የሕግ ባለሙያው አቶ ተሾመ እሸቱ የሴት ታራሚዎቹ የመውለድ መብት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ እንደሆነ በማስቀደም ምላሻቸውን ሰጥተውናል።
ቢሆንም ከወንጀል ሕግ አንፃር እንዲህ በዋዛ ምላሽ የሚያገኝ አለመሆኑን ያነሳሉ። እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ታዲያ ሕጎቹ ሲወጡ ተልኳቸው ምንድነው? ምን ያክል የኅብረተሰቡን ችግር ይፈታሉ? የሚለው ይታያል። የወንጀል ሕግ በባሕርይው ዋና ዓላማው ሰዎችን ማስተማር ሲሆን ሁለተኛው ዓላማው የተረጋጋ ኅብረተሰብ እንዲኖር ማድረግ ነው፤ ለምን ቢባል አንድ ወንጀል ሲፈፀም ወንጀሉ በተፈጸመበት አካባቢ ያለ ኅብረተሰብ ይረበሻልና ነው። ይሄ ማለት የተለያዩ እንቅስቃሴዎቹ ይስተጓጎላሉ፤ የተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮቹም ይደነቃቀፋሉ። በንብረት ላይ የተለያየ ጉዳት ይደርሳል። ሰዎች ሊፈናቀሉ ይችላሉ። ሕጉ ታዲያ ይሄን ተጎጂ ኅብረተሰብ ከጉዳት ይከላከላል። በሌላ በኩል ሕጉ ጎጂው አካል በፈፀመው ጥፋት እንዲማር የማድረግ ዓላማ ይኖረዋል። የመብት ጉዳይም ቢሆን ሴቲቱ ወንጀል ስትፈጽም ገና በዕዳ አሲዛዋለችና ከምግብና መጠጥ እንዲሁም መጠለያ ውጪ መነሳቱ በፍፁም አይታሰብም። የመውለድም መብት ቢሆን በዚህ ረገድ እንደሰብዓዊ ጥያቄ ይቅረብ እንጂ ተቀባይነቱ አጠራጣሪ ነው።
ሰዎች ለምን ይታሰራሉ ለምንስ ከባድ ቅጣት ይወሰንባቸዋል በተለይ ሴቶች ለምን ለረጅም ጊዜ ይታሰራሉ ? የወንጀል ሕግ መሠረቱ ኅብረተሰብን የመጠበቅ ጉዳይ ከሆነ ኅብረተሰብን ያወኩ ሰዎች ለረጅም ጊዜ መታሰራቸው የማይቀር ይሆናል። ኅብረተሰቡ በድርጊቱ ታምሷል አልታመሰም ? የሚለውም የሚታይ ነው። በድርጊቱ አባት አልባ የሆነ ልጅ አለ የለም? ባሏን ያጣችስ ሴት አለች የለችም? ጧሪ ያጣ ወላጅስ አለ የለም? የሚለው ይፈተሻል። በተለይ በገጠሩ ባሏ የሞተባት ሴት ድጋሚ የማግባት ዕድሏ የመነመነ ነው። ምክንያቱም ሁለት ሦስት ልጅ ይኖራታል። ልጆቿን ይዞ የሚያገባ ወንድ የለም። ሦስት አራት ልጅ መውለድ ስትችል ባሏ ሞቶባታል። በመሆኑም አንድ እንደወለደች ልትቀር ትችላለች። ውጤቱ በጣም ከባድ የሚያደርገው ይሄ ነው። እነዚህ ሰዎች ሊማሩ፤ማኅበራዊ ግንኙነታቸው ጤናማ ሊሆን፤አዕምሯቸው የተረጋጋ ሊሆን ይችላል ወይ ተብሎ ሲታሰብ አንዳንዶቹ ሰው ሊጠሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ደም ለመመለስ የሚሹ ይሆናሉ። በመሆኑም ጉዳቱ እስር ቤት የገቡ ብቻ ሳይሆን እስር ቤት ያልገቡትም ጭምር ነው። ፍርዱ የሚሰጠውም ይሄን ጉዳት በማመዛዘን ነው።
እንደ ባለሙያው ታዲያ ሴቶች ለረጅም ጊዜ ማረሚያ ቤት ይቆያሉ። የመውለጃ ጊዜያቸው ያልፋል። መውለድ ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብት ነው የሚለው አያከራክርም። ይሄ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ሁለት ጭብጥም ያነሳሉ። አንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ ታራሚ ሴቶች እንዳይወልዱ የሚደነግግ ሕግ የለም። በተመሳሳይም ሁለተኛው ወንጀል ሠርተው ቢታሰሩም አይውለዱ የሚል ሕግ የለም የሚለው ነው። እንዲወልዱ የሚፈቅደውን ሕግ ጥሶም እንዳትወልድ የፈረደ ዳኛም የለም ባይ ናቸው። እንደ ማብራሪያቸው ታዲያ ሆኖም ሳይወልዱ የመቅረት አደጋ የተጋረጠባቸው ሴቶች ማረሚያ ቤቶች ውስጥ አሉ። ሆኖም ይውለዱ ተብሎ እስካሁን የተሰጠ ውሳኔም የለም። እንዲወልዱ የሚለውን ሕግ ጥሶ የተሰጠ ውሳኔም የለም። ቢሆንም መውለድ ሰብዓዊ መብት ነውና በቅንነት ተነሳስተን እንየው ቢባል እንኳን መውለድ ሰብዓዊ መብቷ መሆኑን የምታነሳው ሴት በሕይወት የመኖር መብት ያለውን ሰው በራሷ ውሳኔ ገድላዋለች። የሰብዓዊ መብት ጥያቄ እያነሳ ያለው ማነው ፤ምን ያደረገ ሰው ነው? ሲባል በሕይወት የመኖር መብትን የገሰሰ ሰው ነው። በዚህ ምክንያትም እንድትታረም ማረሚያ ቤት የገባች ሴት ናት ጥያቄውን እያነሳችው ያለችው፤ ጥያቄውን እንቀበለው ቢባልም ሕጎች ኅብረተሰብ የሚጠብቁና አድሏዊ መሆን የለባቸውም። በተጨማሪም ሕጎች ተፈፃሚም መሆንም አለባቸው።
አድሏዊ መሆን የለባቸውም የሚለውን ሲያብራሩት ትዳሩ የተበተነና ልጆቹ አላሳዳጊ የቀሩበት ወንድ አለ። ሰው ከመግደሉ በፊት 30 ዓመት ከገደለ በኋላ 25 ዓመት ቢፈረድበት 55 ዓመት ይሆነዋል። ከዚህ በኋላ ትዳር ይዞ ቢወልድ የልጁን ፀጋ ውጤት ሊጠቀምበት ይችላል ወይ? ሲባል ማንም ሰው መውለድ የሚፈልገው የሚያሳድገው ልጅ ነው። የሚያስተምረው፤ ጤንነቱን የሚንከባከብለት፤የተሟላ አዕምሮ እና ጤንነት ያለውን ልጅ ነው መውለድ የሚፈልገው። የማኅበረሰቡን ሀብት ተጠቅሞ አድጎ ለማኅበረሰቡ አስተዋፅዖ የሚያደርግ ሰው ነው መውለድ ያለበት። 50 ዓመት ከሞላኝ የወለድኩት ልጅ እኔም ለእሱ አልሆንም እሱም ለእኔም ለኅብረተሰቡም አይሆንም። ጎዳና ላይ ወጥቶ ይበጠብጣል።
በሌላ በኩል በሴትና በወንድ ታራሚ መካከል አድሎ የሚፈጥር ሕግ ልናወጣ እንችላለን ወይ የሚለው ያነጋግራል። እንዲህ ዓይነት ሕግ ቢወጣ ማረሚያ ቤት ውስጥ ሊተገበር ይችላል ወይ? ቤት ያሉ ሴቶች ጽንስ የማስወረድ ጥያቄ እያነሱ ባሉበት እውነት ልጅ ናፍቀው ነው ወይ ጥያቄውን ያነሱት የሚል እሳቤ በሚነሳበት ወቅት የታራሚዎቹ የመውለድ ጥያቄን ምን ያክል በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ይኖረዋል የሚለውንም መመልከቱ አስፈላጊ ነው። የማይፈፀም ሕግ መውጣት የለበትምና ሕጉ ከወጣ እንዴት ሊፈጸም እንደሚገባ ከወዲሁ መጠናት አለበት። የማይፈፀም ሕግ መውጣት የለበትም። እንዴት ነው፤የት ነው የሚፈፀመው፤መቼ ነው የሚፈፀመው፤ማነው የሚያስፈፅመው ማረሚያ ቤቱ ነው፤ማኅበራዊ ጉዳይ ነው፤ ፍርድ ቤት ነው ሲሉ ይጠይቃሉ ባለሙያው። ይወለድ ቢባል የት ይኖራል? ትዳር ያልነበራቸው እንዴት ነው የሚወልዱት ባል አግብተው ነው ወይስ ለመውለድ ሲባል ከሆነ ሰው ጋር ተገናኝተው ነው? በዚህ ላይ በዝርዝር መነጋገርም ይጠይቃል። አፈፃፀሙ ከባድ ነው። የከበደ ሁሉ ሊሆን አይችልም ማለት አይደለም። የወንጀል ሕግ ዓላማ ማኅበረሰብን ማረጋጋት ነው የሚለውን ዓላማ እንዳይጎዳ መጠንቀቅም ይገባል። ወንጀል ፈጻሚን ይሄን ያህል መብት ካለኝ ወንጀል መፈፀም የተባረከ ነው ሊያሰኝም ሁሉ ይችላል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም