አንድን አገር ለማስተዳደር ውክልና የወሰደ መንግሥት ከሚጠበቅበት ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ተጠቃሽ የሆነው የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅና ኅብረተሰቡን በልማት ተጠቃሚ ማድረግ ነው። ኅብረተሰቡን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ደግሞ ራሱ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ተግባር ማካሄድ ዋንኛ ተመራጭ ጉዳይ ነው።
ከዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት እየተካሄዱ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን ለዛሬ ማንሳት ወደድኩ። በቅድሚያ በቤት ግንባታ ዙሪያ ያለውን እንመልከት። የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በቤት ተደራሽነት ዙሪያ ያስጠናው ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ቤትን ለዜጋ ተደራሽ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት በግንባታ እቃዎች አቅርቦት የዋጋ ንረት ምክንያት ፈተና ውስጥ ወድቋል ።
ከዚህ የተነሳም ዜጎች ደረጃውን ባልጠበቀ ቤት ውስጥ እየኖሩ ከምግብና ሌሎች ፍላጎቶች ቀንሰው ከገቢያቸው 30 በመቶ በላይ ለቤት ኪራይ የሚከፍሉ ቁጥራቸው ከፍተኛ እየሆነ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ቤት መግዛት የማይታሰብ እስከመሆን ደርሷል። ቤት መግዛት ቀርቶ የአነስተኛው የስቱዲዮ ቤት የኪራይ ዋጋም ለአብዛኛው ሠራተኛ የሚቻል አይደለም።
መንግሥትም ለዚህ ጉዳይ እልባት ለመስጠት የቤት ግንባታ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው። አቅም ላላቸው ለነዋሪዎችም መሬት በዝቅተኛ ዋጋ በሊዝ በማከራየት የራሳቸውን መኖሪያ ቤቶች እንዲገነቡ እያገዘ ነው። ከዚህም አልፎ የመንግሥት ተቋማትና ባለሀብቶችን በማሰለፍ የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ ላይ ይገኛል ።
የቤት ማደስ ሥራው ትኩረት ተሰጥቶት በሁሉም ክፍለ ከተማዎች በሚባል መልኩ በተገጣጣሚ ቤቶች እየተሠራ እንደሆነ ይታወቃል። ፕሮጀክቶቹን ከግብ ለማድረስም በከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ጠንካራ ክትትል እየተደረገ ይገኛል።
ከፐሮጀክቶቹ ብዙ ትምህርት እየተወሰደ ሲሆን፣ ቁርጠኝነት ካለ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል በማሳያነት እየተጠቀሱም ነው። በቀጣይም በሚኖሩ የግንባታ ሥራዎች የከተማውን ውበትና ደረጃ በጠበቀ መልኩ ግንባታዎች እንደሚቀጥሉም እየተነገረ ነው ።
ይህ ለከተማዋ ነዋሪዎች በተለይም ለአቅመ ደካሞች ትልቅ እፎይታ ሆኗል ።
በከተማ እየተከናወኑ ካሉ ሰው ተኮር የልማት ሥራዎች ሌላኛው የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ የቀድሞ ይዘቱን ሳይቀይር ከዚህ ቀደም ሲሰጥ የነበረውን ሃይማኖታዊ ፣ሕዝባዊ እና ሌሎች ማኅበራዊ ዝግጅቶች በተሻለ እና ምቹ በሆነ መልኩ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ተገንብቷል።
ፕሮጀክቱ በአካባቢው የሚስተዋለውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ ጥበትን ከመቅረፍ አንጻር እስከ አንድ ሺህ 400 የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችን የሚያስቆሙ ባለሁለት ወለል የመኪና ማቆሚያ ያለው ነው። በተጨማሪነት 35 ሱቆች፣ 140 መፀዳጃና 20 መታጠቢያ ቤቶችም አሉት።
ለቢሮ መገልገያ ክፍሎች፣ ዘመናዊ አሳንሳሮች (ሊፍቶች)፣ ለ24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጡ የደህንነት ካሜራዎች፣ ዘመናዊ ዲጂታል ስክሪኖች እና የእሳት መከላከያ አለው። ሱቆቹ የኢትዮጵያን ባህል እና ቅርሶች የሚያሳዩ እና ለጎብኚዎች ለመሸጥ በሚያመች መልኩ የተገነቡ ናቸው። በአደባባዩም ነጻ የዋይ.ፋይ (WiFI) ኢንተርኔት አገልግሎት ይሰጣል።
ሌላው ደግሞ በቅርቡ የሚገነባው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ለሚ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቶች በመሐል ከተማ ብቻ ሳይሆን በዳር አካባቢዎችም ማዳረስን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆነም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያሳያል። እንደመረጃው ከሆነ ግንባታው በአንድ ነጥብ ሶስት ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነባ ነው።
አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር ታሳቢ በማድረግ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ኤግዚቢሽኖች በማስተናገድ ለአካባቢው ተያያዥነት ያለው ጠቀሜታ እንዲኖረው ታስቦ የተገነባ ማዕከል ነው። አካባቢውንም በማስዋብ ከመንገድ አካፋዮች፣ አደባባዮችንና የእግረኛ መንገዶች ጋር ተናቦ የሚሠራ ሲሆን፣ 14ሺህ 400 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ፕሮጀክት ነው።
ፕሮጀክቱ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ከጥበብ ዲዛይንና ቢዩልዲንግ ፒ.ኤል.ሲ ጋር በመተባበር በ10 ወራት ተገንብቶ የሚጠናቀቅ ነው። ይህ ፕሮጀክት የስብሰባ አዳራሽ፣የሕዝብ መሰባሰቢያ ስፍራ (public space)፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ (gym) ፣ የሠርግና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል መናፈሻ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ ሱፐርማርኬት ፣ የቢሮ አገልግሎት የሚሰጡ ቦታዎች ፣ የማንበቢያ ስፍራ እና የመሳሰሉት የሚገኙበት ነው።
ይህ ፕሮጀክት በግንባታው ወቅት እስከ 1 ሺህ 100 ያህል ዜጎች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ በቀጣይ በቋሚነት ለ400 ዜጎቻችን የሥራ እድል የሚፈጥር ይሆናል። ከነዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ የኢትዮ- ቻይና ወዳጅነት ፓርክ፣ አንድነት ፓርክን መጥቀስ ይቻላል ።
በአጠቃላይ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ያለው ሰው ተኮር የልማት እንቅስቃሴ የሚበረታታ፤ እውቅና የሚሰጠው ነው።
በእርግጥ የሰው ተኮር የልማት ፕሮጀክቶች በማለት ማሳያ የሚሆኑትን ለማንሳት ወደድኩ እንጂ ሌሎችም በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች የተሠሩ ስለመኖራቸው ከመዲናዋ ነዋሪዎች የተሰወረ አይደለም። ከእነዚህም መካከል የከተማ ግብርና፣ የአረጋውያን የምገባ ማዕከላት፣ የሽገር ዳቦ መሸጫ ማዕከሎች እና ሌሎችም ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።
በእርግጥ እነዚህ የተጠቀሱት የሰው ተኮር ፕሮጀክቶች በቂ ናቸው የሚል አተያይ የለኝም፤ አይኖረኝምም። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያንም መዲና ናት። ከዚህ አንጻር ሲታይ ከዚህም በላይ ሰው ተኮር ልማት እንደሚያስፈልጋት እሙን ነው። ስለዚህም የተጀመረውን ሰው ተኮር ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የባለድርሻ አካላት ብሎም የነዋሪውም ቀና አመለካከት የግድ ይላል።
ታዝበው ዘመኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም