አሰላ ከኢትዮጵያ ከተሞች የምትለየው የበርካታ ብርቅዬ አትሌቶች መናኸሪያ በመሆን ነው። የኦሊምፒክና የዓለም ቻምፒዮኖችን በብዛት በማፍራት የሯጮች ምድር ከተሰኘችው አርሲ ዞን የፈለቁ አትሌቶች ወደ ታላቅነት በሚያደርጉት ጉዞ አሰላ መሸጋገሪያ ናት። ስፍር ቁጥር የሌላቸው የዓለም የምንጊዜም ምርጥ አትሌቶች ከዚህች ከተማ ተነስተው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ከማስጠራት ባሻገር የዓለም አትሌቲክስ ጌጥና ድምቀት ሆነዋል።
አሰላ በአትሌቲክሱ የገነባችውን ከፍ ያለ ስም በእግር ኳሱም ለመድገም ደፋ ቀና በማለት ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በእግር ኳሱ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ተወካይ ክለብ እንዲኖራት ለማድረግ ጠንካራ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የአሰላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገልጿል። ቢሮው ከተማዋ በእግር ኳሱ ከአምስት ዓመታት በፊት መቀመጫውን አሰላ አረንጓዴው ስቴድየም ያደረገው ሙገር ሲሚንቶን ዓይነት ተወካይ ክለብ እንደነበራት ይታወቃል።
አሰላ በአሁኑ ወቅት በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ የሚመጥን ክለብ በስሟ እንዲኖራት በመገንባት ላይ የሚገኝ ቡድን እንዳለ ተጠቁሟል።
የአሰላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በዶ ዳባ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ እንደገለፁት፣ አሰላ ከተማን እንዲወክል የተቋቋመው አዲስ ክለብ ከፍተኛ የበጀት ችግር ያለበት ቢሆንም ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
ክለቡ ያለበት የበጀት ችግር ብቻ እንዳልሆነና የአመራርና ሌሎች ውስጣዊ ችግሮችም እንዳሉበት የጠቆሙት የቢሮው ኃላፊ፣ «አንድ ክለብ የእኔ ነው ብሎ ትኩረት ከተሰጠውና በጀት ከተያዘለት የመቀጠል ተስፋው ትልቅ ነው» ይላሉ። የአሰላ ከተማ አትሌቲክሱ ላይ ትኩረት በማድረግ እየሠራች እንደምትገኝ ያስታወሱት አቶ በዶ ከአምና ጀምሮ በእግር ኳሱም ብዙ ሥራዎች በመሠራት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮም ባለሀብቶችን በማሰባሰብና ኮሚቴ በማዋቀር የተከናወኑ ሥራዎች ለውጥ እያመጡ በመሆኑ ቢሮ የእግር ኳስ ቡድኑን ለማጠናከር የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አሰላ ጠንካራ የእግር ኳስ ቡድን ኖሯት በፕሪሚየር ሊግ እንድትወከል ከታዳጊዎች ጀምሮ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ። በዚህም በከተማዋ ከስምንት የሚበልጡ የታዳጊ እግር ኳስ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የቢሮው ኃላፊ ጠቁመው፣ እነዚህን ፕሮጀክቶች በማጠናከር ከተማዋ በከፍተኛ ደረጃ የሚወዳደር ክለብ እንዲኖራትና የታዳጊ ፕሮጀክቶችም ልፋት እንዳይባክን ከከተማው አስተዳደር ጋር በመነጋገር በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እግር ኳስ ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት በአንደኛ ሊግ ተወዳድሮ በአንደኝነት መጨረስ የቻለ ሲሆን፣ በዘንድሮ የውድድር ዓመትም በሁለተኛ ሊግ በመወዳደር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ያም ሆኖ በክለቡ ውስጥ ያለው ችግር በመንግሥት ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ሕዝቡን የማስተባበር ሥራም በመሰራት ላይ መሆኑም ተገልጿል። በዚህም በከተማዋ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር በመተባበር በከንቲባው እውቅና ከተለያዩ ምሁራን ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።
« ወ ደ ፊ ት ም ብዙ ችግሮች እ ን ደ ሚ መ ጡ እ ና ው ቃ ለ ን የሚመጣውን ችግር በመቋቋም ክለቡን ወደ ፕሪሚየር ሊግ እናሳድጋለን» ያሉት አቶ በዶ፣ ክለቡ አሁን ካለበት ሁለተኛ ሊግ በሂደት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ቢያድግ በርካታ ተ ግ ዳ ሮ ቶ ች ሊ ገ ጥ ሙ ት እ ን ደ ሚ ች ሉ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ሊገጥሙ ለሚችሉ ችግሮች እራን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንደሚገባም አክለዋል።
ክለቡ በትልቅ ደረጃ ተፎካካሪ ለመሆን ብዙ ተጫዋቾችን ማስፈረምና ደመወዝ መክፈል ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ መሠረት ያለው በጀት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከከተማዋ ከንቲባና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ክለቡን ሕዝባዊ መሠረትና ድጋፍ እንዲኖረው ከወዲሁ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የቢሮው ኃላፊ አብራርተዋል።
በሰው ኃይል በኩል ክለቡን የማጠናከር ሥራም የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሁለት ባለሙያዎች እስከ ዓመቱ መጨረሻ በኮንትራት ተቀጥረው ክለቡን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
«እግር ኳስ ሲባል ቀላል ይመስላል፣ ከባዱ ነገር እግር ኳስን ማሳደግ ነው። እግር ኳስ እንዲያድግ አጀንዳ አድርገን ልንሠራ ይገባል» ያሉት አቶ በዶ፣ እንደ ኦሮሚያ ክልል ለስፖርቱ ትኩረት አልተሰጠም ባይ ናቸው። ስለዚህም የመንግሥት ድጋፍና በጀት ከሌለ የስፖርት ቢሮ ብቻ በራሱ የጀመረው ጥረት ከግብ ስለማይደርስ የሚመለከተው አካል ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም