በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ቢሊዮን የሚገመቱ አካል ጉዳተኞች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ባሉ አገራት የሚገኙና በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸው ይገለጻል፡፡
ለእነዚህ አካል ጉዳተኞች አድልዎና መገለል የእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው አካል መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ መገለል ሲባልም ከትምህርት፣ ከመረጃ፣ ከስራ፣ ከመሰረታዊ ልማት፣ ከጤና አገልግሎት፣ ከልማት እቅዶች፣ ከኢኮኖሚ ማሻሻያ እቅዶች፣ ከትራንስፖርት አገልግሎትና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ነው፡፡
አካል ጉዳተኞች፣ የአገር ደህንነትን የሚወክሉ እንደ አየር ንብረት መታወክና ተፈጥሯዊ አደጋዎች፣ ስደትና ጦርነት፣ ሰላም ማጣትና የብሄር ግጭቶች፣ ረሃብና በምግብ ራስን ያለመቻል ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው ፡፡
ዘንድሮ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ27ኛ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ ከተለያዩ ከተሞች የተውጣጡ አካል ጉዳተኞችና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት ተከብሯል፡፡
በዕለቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበር ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ፤ ዘንድሮ በዓሉ የሚከበረው፤ ‹‹የአካል ጉዳተኞችን በማብቃት አሳታፊነትና እኩልነትን እናረጋግጥ›› በሚል መሪ ሃሳብ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ መሪ ቃሉ ትኩረት ያደረገው የ2030 እ.ኤ.አ ልማት አጀንዳ አካል የሆነውን ሁሉን አቀፍ አካታችና ዘላቂ ልማት ውስጥ አካል ጉዳተኞችን ማብቃት ላይ ነው፡፡
2030 እ.ኤ.አ የልማት አጀንዳ ቃል የተገባው አካል ጉዳተኞችን የለውጡ ተጠቃሚ በማድረግ አካታችና ዘላቂ ልማት ለማምጣት የሚደረገውን ሂደትና ጥረት ማፋጠን መቻል ነው ያሉት ወይዘሮ ምህረት፤ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መንግስት የአካል ጉዳተኞችና የሚወክሏቸው ማህበረሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የትምህርት ምርምር ተቋማትና የግሉ ዘርፍ በለውጡ በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡
የአካል ጉዳተኞችን እኩልነትና ተካታችነት ወደፊት ማራመድ እንዲቻል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን ጎን ለጎን የአፍሪካ አካል ጉዳተኞች መብት ፕሮቶኮል መጽደቁን አስታውሰው፤ ፕሮቶኮሉ በአፍሪካውያን ዘይቤ የተቃኘና አካል ጉዳተኞች እኩል ተጠቃሚ መሆናቸውንና አለመገለላቸውን እንዲያረጋግጡ እንደሚያስችልም ይናገራሉ፡፡
የአካል ጉዳተኞች ማህበር እንደ አካል ጉዳተኞች ተወካይነቱ ፕሮቶኮሉን የማስፈጸምና የመከታተል ሚና ሊጫወት እንደሚገባው ጠቁመው፤ አካል ጉዳተኞች አባሎቻቸውን በመደገፍ ማብቃት እንደሚኖርባቸውም ይገልጻሉ ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡
በመላው ኢትዮጵያ የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች በልማቱ አፈጻጸም ሂደት ከእቅድ ንድፍ እስከ ክትትልና ትግበራው በየደረጃው በባለቤትነት ተሳታፊ መሆናቸውን በመጠቆምም፤ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋሮች የአካል ጉዳተኞችን እኩልነት ለማረጋገጥ በጋራ መትጋት ይገባቸዋል ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው፤ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መንግስት በኢኮኖሚና ማህበራዊ ተደራሽነት የሚገጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በመሪ ሃሳቡ እንደተቀመጠው አካል ጉዳተኞችን በማብቃት በሁሉም ዘርፎች አካታች በሆነ መልኩ በአስተሳሰብም ይሁን በተግባር እኩልነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን መገንባት እንደሚጠይቅም ያመለክታሉ፡፡
በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተነደፈ ብሄራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ በክልሉ ለመተግበር አበረታች ትግበራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ነው ያመለከቱት፡፡
የክልሉ መንግስት በጀት በመመደብ በሀዋሳ ከተማ ጽህፈት ቤት በመገንባት ለክልሉ አካል ጉዳተኞች ማህበር ማስረከቡን አቶ ሚሊዮን አስታውሰው፤ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ቤት፣ የብድር አገልግሎት በገጠርና በከተማ ተግባራዊ በማድረግ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የሚናገሩት፡፡ የአሰራር ስርአት በመዘርጋትም ፍትሀዊ ተጠቃሚ በማድረግ የልማት ተቋዳሽነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ በከተማው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ የአካል ጉዳተኞች ቀን እንዲከበር ታሳቢ ማድረጉንም ነው የገለጹት፡፡
በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የሚስተዋሉ የተዛቡ አመለካከቶች፣ የተገነቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ አሁንም ብዙ መስራት እንደሚገባ በመጠቆምም፤ የክልሉ መንግስት የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለለውጥ ይተጋል ሲሉ ነው ያስገነዘቡት፡፡
የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጌጎ ተስፋዬ፣ አካል ጉዳተኞችን በማብቃትና በማካተት አሳታፊነትና እኩልነትን ማረጋገጥ የሁሉም አካላት የጋራ ስራ ሊሆን እንደሚገባ ይጠቁሙና፤ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ሁሉም በኃላፊነት የሚተገብረው አገራዊ አጀንዳ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ህይወት ውስጥ ምሉዕ ለማድረግ የማብቃት ስራ መሰራት ይገባዋል፡፡ የማብቃት ስራ በእምነትና በጋራ መግባባት ለመስራት፣ ማህበራዊ ፍትህ የሰፈነበትና እኩልነት የተረጋገጠበት ዘመናዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ይህም የአካል ጉዳተኞችን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ልማትን ለማፋጠን ሰፊ ዕድል ይፈጥራል፡፡
አገሪቱ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽንን በአዋጅ እንዲጸድቅ ማድረጓ፣ ብሄራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መርሃ ግብርና የአካላዊ ተሃድሶ ስትራቴጂ ነድፋ እየሰራችበት መሆኑን የሚጠቁሙት ዶክተር ኤርጌጎ፤ ለአካል ጉዳተኞች ከቀረጥ ነጻ ተሽከርካሪ ማስገባት መፈቀዱ በርካታ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ማድረጉን ያመለክታሉ፡፡ ጥረቶቹ እንደ መልካም ጅምር የሚታዩ እንጂ ድጋፍና ክትትሉ አመርቂ እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ ተቋማቸው በአንድ መቶ እቅዱ ውስጥ አካትቶ እየሰራበት ከሚገኝባቸውም የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳው እንደሆነም ይጠቅሳሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2011
ማህሌት አብዱል