ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ሳምንቱ በምን አለፈ? ሳምንቱን በትምህርት እንዳሳለፋችሁት እርግጠኛ ነኝ። ምክንያቱም ጎበዝ ተማሪ ሳምንቱን የሚያሳልፈው በትምህርትና የተማረውን በማጥናት ነው። እኔ ደግሞ እናንተ ጎበዝ ተማሪ ስለሆናችሁ ሳምንታችሁን በትምህርትና በጥናት እንዳሳለፋችሁ እርግጠኛ ነኝ።
ልጆች ዓለም ላይ ‹‹እችላለሁ የሚያቅተኝ የለም፤ እኔ ከችግሮቼ በላይ ነኝ፤ ችግሮቼ ሊያሸንፉኝ ጉልበት የላቸውም›› ብለው በማመን በርካታ ሰዎች እጅግ በጣም አስደናቂና ለማመን የሚከብዱ ስራዎችን በመስራት በዓለም መድረክ ላይ ማንነታቸውን በተግባር አሳይተዋል። ለመድመቅና ለመናኘትም በቅተዋል። እጆቻቸውን በአደጋም ይሁን በተፈጥሮ ያጡ የዓለም ድንቅ ልጆች አውሮፕላን ሲያበሩ፣ በእጆቻቸው ምትክ እግሮቻቸውን በመጠቀምም ሁሉን የሰው ልጅ የሚያደርገውን ተግባር ሲያከናውኑ መመልከት የተለመደ ሆኗል። ለዚህ ነው እችላለሁ ብለው ካመኑ የማይቻል ነገር የለም የሚባለው አይደል ልጆች? አሁንስ እውነታውን ተረዳችሁ?
የሰው ልጅ በምድር ላይ የሚኖረው ብዙ ፈተናዎች እየገጠሙትና እያለፋቸው ነው። ነገር ግን እነዚህን ፈተናዎች አልፎ ነገን ለማየትና ጠንካራ ሆኖ ለመገኘት እንደብረት የጠነከረ ውስጣዊ በራስ መተማመን እና ለሚደርሱብን ችግሮች የሚኖረን በጎ አመለካከት ወሳኝ ነው። ልጆች ዛሬ የማስተዋውቃችሁ እጅግ በጣም ጠንካራና ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ያላቸውን ሁለት የስድስት ዓመት ልጆች ነው። እነዚህ ልጆች ‹‹በቪዥን የአይነ ስውራን ትምህርት ቤት›› የኬጂ አንድ ተማሪዎች የሆኑት ተማሪ አሜን ወንደሰን እና ተማሪ ያብስራ ምትኩ ናቸው።
ልጆች ያብስራ ብዙ ችሎታ ያለው ልጅ ነው፤ በራስ መተማመኑ ደግሞ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ‹‹ምንም የሚያቅተኝ ነገር የለም ማድረግ የምፈልገውን ነገር ማድረግ እችላለሁ›› ብሎ የሚያምን ልዩ ልጅ ነው። ከአሜን ጋርም የሚያመሳስላቸው ይህ ነገር ነው። ምንም እንኳን ሁለቱም ነገሮችን ማየት ባይችሉም ለራሳቸው የሚያምኑት ግን ማየት እንደሚችሉና ምንም የሚያቅታቸው ነገር እንደሌለ ነው። ይህ ደግሞ ብዙ ሰዎች ጋር የሌለና ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉት ለራስ ትልቅ ክብረት የመስጠት ፀጋ ነው። እናንተም ከአሜንና ከያብስራ መማር ያለባችሁ ይህንን ነው።
ያብስራና አሜን ለሰው ያላቸው ፍቅር ልዩ ነው፤ ከሰዎች ጋር ቶሎ ይላመዳሉ ሰው ያከብራሉ እርስ በእርስም ይከባበራሉ ይዋደዳሉ። ይህ መከባበር እና መዋደዳቸው ደግሞ ለብዙ ልጆች አርአያ የሚሆን ነው። ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሰው ማክበር፣ በዙሪያቸው ያለውን ሰው ሁሉ ያለ ምንም ልዩነት አንዱን ከአንዱ ሳይለዩ መውደድ አለባቸው። ፈጣሪም የሚወደው ይህንኑ ነው፤ ልጆች ደግሞ ፈጣሪ የሚወደውን በጎ ነገር የሚያደርጉ ልዩ ጎበዞች ስለሆኑ ይህን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው። ያብስራና አሜንም የሚመክሯችሁ ይህንኑ ነው።
አሜን እና ያብስራ ሲያድጉ መሆን የሚፈልጉት አውሮፕላን አብራሪ ነው። የኢትዮጵያን አውሮፕላኖች ወደ ተለያዩ ሀገራት እያበረሩ መንገደኞችን በማገልገል እግረ መንገዳቸውን የተለያዩ ቦታዎችን መጎብኘትና በሄደበት ሁሉ ኢትዮጵያን ማስተዋወቅ ይፈልጋሉ። ልጆች የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ አየር መንገዶች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ መሆኑን ታውቃላችሁ አይደል? እንግዲህ አሜን እና ያብስራም ሲያድጉ መስራት የሚፈልጉት በዚህ መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው።
አሜን ለኢትዮጵያ የሚመኝላት ብዙ ምግብ እንዲኖራት ነው። ‹‹ብዙ የተራቡ ሰዎች በሀገራችን ላይ አሉ›› የሚለው አሜን ‹‹ሁሉም ምግብ ስለሚያስፈልጋቸው ሀገሬ ሁሉም ጠግቦ የሚኖርባት እንድትሆን እፈልጋለሁ›› ብሏል። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ልጆች ጠንክረው ማጥናት እንዳለባቸው ይመክራል። ምክንያቱም ሁሉም ልጆች ጠንክረው ተምረው ትልቅ ቦታ ደርሰው ለሀገራቸው ጥሩ ስራ መስራት አለባቸው። ያብስራ በበኩሉ ለኢትዮጵያ የሚመኝላት ሰላም እንድትሆን ነው፤ ‹‹ሀገራችን ሰላም ካልሆነች እኛ ሰላም ሊኖረን አይችልም፤ በሰላም ትምህርት ቤት ሄደን ተምረን መመለስ አንችልም፤ ስለዚህ ኢትዮጵያ ስላም እንድትሆንና ሰው ሁሉ በሰላም እንዲኖር እፈልጋለሁ›› በማለት ለሀገሩ የሚመኝላትን ይናገራል።
ልጆችዬ አሜን ያለው ልዩ ችሎታ ምን መሰላችሁ፤ ሰዎችን በእጆቹ በመዳሰስ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የሰዎችን ስም የማስታወስ ችሎታ ነው። ከተዋወቃችሁት በኋላ ሌላ ጊዜ ስታገኙት የሚያስታውሰው ማን እንደሆናችሁ ብቻ አይደለም ስማችሁንም ጭምር እንጂ። ልጆች አሜን መዝሙር ሲዘምር ብታዩት ድምፁ እንዴት እንደሚያምር ልነግራችሁ አልችልም።
ያብስራ ቤት ውስጥ አልጋ በማንጠፍ የራሱን እቃዎች በቦታው በስርአት በማስቀመጥና ሌሎች በሱ አቅም የሚሰሩ ስራዎች በመስራት ቤተሰቡን ያግዛል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ስዕል ይስላል፤ ለሚወዳቸው ሰዎች የሚሰጠው ስጦታ ራሱ የሚስለውን ስዕል ነው። ከዚህ ቀደምም ኮሜድያን እሸቱ መለሰ ትምህርት ቤታቸውን ለመጎብኘት በመጣበት ወቅት ስዕል ስሎ ሰጥቶታል።
‹‹ልጆች ቤተሰብ የሚላችሁን መስማት፣ መምህራኖቻቸውን ማክበርና ትምህርታቸውን በአግባቡ መማር አለባቸው። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከልባቸው እርስ በእርስ መዋደድና መከባበር አለባቸው›› የያብስራ የአሜን መልዕክት ነው። እኔም የዛሬው ፅሁፌን የነሱን መልዕክት ተግባራዊ እንድታደርጉ በመንገር አበቃሁ መልካም የትምህርት ሳምንት ይሁንላችሁ።
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን የካቲት 5/2015