በኢትዮጵያ እግር ኳስ ሕዝባዊ መሰረት ካላቸው ጥቂት ክለቦች መካከል አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ግንባር ቀደም ናቸው። ፈረሰኞቹና ቡናማዎቹ የኢትዮጵያ እግር ኳስ የጀርባ አጥንት በመሆን ባለፉት በርካታ ዓመታት ተፅእኗቸው ጎልቶ መውጣት ችሏል። መሰረታቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት ሁለቱ የኢትዮጵያ ሃያል ክለቦች ከየትኛውም ክለብ በላይ የደጋፊ ሀብት አላቸው። እነዚህ ውብ ደጋፊዎቻቸውም የመቀመጫቸው አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ድምቀት በመሆን የተለየ ክብር ይሰጣቸዋል። ይህ ድምቀታቸው ደግሞ ጎልቶ የሚወጣው በእርስ በእርስ ግንኙነት “ሸገር ደርቢ” ጨዋታ ነው።
ሁለቱን የአንድ ከተማ ተቀናቃኝ ክለቦች የሚያገናኝ ጨዋታ ሁሌም ተጠባቂ ነው። አዲስ አበባም በሁለቱ ታላላቅ ክለቦች ጨዋታ የተለየ ድምቀት ትላበሳለች። ባለፉት ሶስት ዓመታት ግን የሁለቱ ክለቦች በርካታ ውብ ደጋፊዎች በጉጉት የሚጠብቁትን ፍልሚያ በመዲናቸው ካምቦሎጆ ታድመው ለመመልከት አልታደሉም። ቀጣዩን ጨዋታ ጨምሮ የሸገር ደርቢ በስደት ድሬደዋ፣ ሐዋሳ፣ አዳማ ለ3 ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን የአሁኑ ለ4ኛ ጊዜ ነው ከከተማቸው ውጭ የሚደረገው።
ዛሬም ታላቁ የሸገር ደርቢ ስደት ላይ ነው። ሁለቱ ክለቦችም ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ በድሬዳዋ ስቴድየም
በፕሪምየር ሊጉ ለ45ኛ ጊዜ እርስ በርስ ሲገናኙ ዘንድሮ በሁለቱም ክለብ ደጋፊዎች በኩል የፈዘዘው ደርቢ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ዛሬ በ12ኛው ሳምንት ተስተካካይ የቤቲንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ የሚገናኙትን ሁለቱን ክለቦች ፍልሚያ ኢንተርናሽናል አልቢትሮች ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል። በዚህም ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ከረዳቶቹ ትግል ግዛው እና ፋሲካ የኋላሸት እንዲሁን አራተኛ ዳኛው ለሚ ንጉሴ ጋር በመሆን በጋራ ጨዋታውን እንደሚመሩ መረጃዎች ጠቁመዋል።
ሁለቱ ክለቦች በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ1991 ዓ.ም ጀምሮ 44 ጊዜ እርስ በርስ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶችም ቅዱስ ጊዮርጊስ 21 ጊዜ ድል ሲቀናው ቡና ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፏል ፤ 16 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
በ44ቱ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 88 ግቦች መረብ ላይ አርፈዋል። 60ውን ግብ በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 28 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።
የወቅቱ የሊጉ ቻምፒዮን የሆኑት ፈረሰኞቹ አምና በተቀናቃኛቸው ላይ የነበራቸው የበላይነት ዘንድሮስ ይቀጥላል? የስፖርት ቤተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀው ጉዳይ ነው። ፈረሰኞቹ በአምናው የውድድር ዓመት ቡናማዎቹን በሊጉ በገጠሙባቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ለአንድና አራት ለዜሮ በሆነ ውጤት በማሸነፍ የበላይነት ነበራቸው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ባለፉት 12 ጨዋታዎች 7ቱን አሸንፎ 4 አቻ ወጥቶ በአንዱ ብቻ ነው የተሸነፈው። ኢትዮጵያ ቡና በአንፃሩ ካባለፉት 12 ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው 5ቱን ብቻ ሲሆን፤ በ5ቱ ጨዋታዎች ሽንፈት ገጥሞታል። ቀሪ ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ በ አቻ ውጤት ደምድሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ 25 ጊዜ መሳተፍ የቻሉት ፈረሰኞቹ አስራ አምስት ጊዜ የዋንጫ ድል በማሳካት ከሁሉም ከፍ ብሎ የሚነገር ታሪክ አላቸው። ዘንድሮም የፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ 2ኛ ሆነው ተቀምጠዋል።
ኢትዮጵያ ቡና በፕሪሚየር ሊጉ ሃያ ስድስት ጊዜ በመሳተፍ ከፈረሰኞቹ በአንድ የተሻለ ታሪክ ቢኖራቸውም የፕሪሚየር ሊጉን ድል አንድ ጊዜ ዋንጫ በማንሳት 2003 ላይ ብቻ ነው ማጣጣም የቻሉት። በዘንድሮው የውድድር ዓመትም በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ዘጠነኛ ላይ ተቀምጠው ነው የከተማ ተቀናቃኛቸውን የሚገጥሙት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 4 ቀን 2015 ዓ.ም