በተለያዩ ዓለማት የጎዳና እና የመም ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአሸናፊነት ባለፈ ፈጣን ሰዓት ማስመዝገባቸው የተለመደ በመሆኑ በዚያው ልክ ውድድሮቻቸው በጉጉት ይጠበቃሉ። በዚህ ወቅት እየተካሄዱ ባሉት የቤት ውስጥ የዙር ውድድሮች ላይም በተመሳሳይ አዳዲስ ክብረወሰኖችን ያስመዘግባሉ በሚል የአትሌቲክስ ቤተሰቡ በቅርበት ይከታተላቸዋል።
ከነዚህ ውድድሮች መካከል ከትናንት በስቲያ ምሽት የተካሄደውና በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አስደናቂ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችለዋል።
በፖላንዷ ቱሪን በተለያዩ ርቀቶች ከተካሄዱት ውድድሮች መካከል አስቀድሞ ሰፊ ትኩረት ያገኘው የአንድ ማይል የሴቶች ፉክክር ነው። በዚህ ውድድር የዓለም ክብረወሰን ታሻሽላለች ተብላ ስትጠበቅ የነበረችው ገድሞ የዓለም ቻምፒዮና አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ ስትሆን በርቀቱ ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ማሸነፍ ችላለች። በዙር እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ ውድድር እአአ በ2021 በፈረንሳይ ሌቪን በ1ሺ500 ሜትር የተካፈለችው ይህቺ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት 3:53.09 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በማጠናቀቅ የዓለም ክብረወሰኑን መስበሯ የሚታወስ ነው። ባለፈው ዓመት በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ላይም በዚሁ ርቀት የተካፈለችው ጉዳፍ 3:57.19 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ማስመዝገቧ ይታወሳል።
በዚህ ውድድር ላይ ስትካፈልም በአንድ ማይል በሀገሯ ልጅ ገንዘቤ ዲባባ ለዓመታት ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን የግሏ ለማድረግ ነበር። ነገር ግን 4:24.98 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በማጠናቀቅ በሰከንዶች ልዩነት ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት ልታስመዘግብ ችላለች። የክብረወሰኑ ባለቤት የሆነችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ገንዘቤ ዲባባ ርቀቱን 4:13.31 የሆነ ሰዓት በመሮጥ ቀዳሚውን ሰዓት የያዘች ሲሆን፤ እአአ በ2016 ነበር ክብረወሰኑን በስማ ያስመዘገበችው። የ5ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮኗ እንዲሁም የ1ሺ500 ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ በዚህ ውድድር ላይ 400 ሜትሩን የሮጠችው በ1ደቂቃ ከ1 ሰከንድ ከ 1ማይክሮ ሰከንድ ነው። በድንቅ አሯሯጧ ዓለምን ያስደመመችው ጉዳፍ ተከትለዋት ከገቡት ተፎካካሪዎቿ ጋር የነበራት ልዩነትም ፈጣኑን ሰዓት ልታስመዘግብ ትችላለች በሚል እንድትጠበቅ አድርጋት ነበር። ያም ሆኖ በሽርፍራፊ ሰከንዶች በመዘግየቷ ዓለምን ለጥቂት ከእጃ ሊወጣ ችሏል።
ይህንን ተከትሎም የ26 ዓመቷ ወጣት አትሌት ‹‹ያቀድኩት የዓለም ክብረወሰንን ለመስበር ነበር፤ ሆኖም አትሌቲክስ እንዲህ ነው። በልምምድ ወቅት ጥሩ አቋም ላይ እንዳለህ ሊሰማህ ይችላል፤ ነገር ግን በውድድር የፈለከውን ማግኘት አትችልም። ቢሆንም አሁንም የማስበው ይህ ክብረወሰን አንድ ቀን የእኔ እንደሚሆን ነው›› ስትል መግለጿን የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ አስነብቧል። ጉዳፍን ተከትላ የገባቸው ፖላንዳዊቷ አትሌት ዌሮኒካ ሊዛኮውስካ 4:29.06 የሆነ ሰዓት ስታስመዘግብ፤ ጃማይካዊቷ አዴሌ ትሬሲ ደግሞ 4:30.17 በሆነ ሰዓት ውድድሩን በሶስተኝነት መፈጸም ችላለች።
ሌላው በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የ3ሺ ሜትር ሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አራት ያለውን ደረጃ በማስመዝገብ በፍፁም የበላይነት አጠናቀዋል። በዚህ ውድድር ሌላው አስደናቂ ነገር ደግሞ በአትሌቶቹ መካከል የነበረው የፉክክር ስሜት ነው። ርቀቱን በቀዳሚነት ያጠናቀቀችው አትሌት ፍሬወይኒ ኃይሉ ከ800 ሜትር አንስቶ አስደናቂ በሆነ ታክቲክ ሩጫውን መምራት የጀመረች ሲሆን፤ የሀገሯ ልጆችም ተከትለዋት በመግባት አስደሳቹን ድል አጣጥመዋል። ባለፈው ዓመት በሰርቢያዋ ቤልግሬድ አስተናጋጅነት በተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ ቻምፒዮና ለሀገሯ በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ያስመዘገበችው ፍሬወይኒ በ3ሺ ምትርም አስደናቂ ብቃቷን ለዓለም ልታሳይ ችላለች። ርቀቱን አጠናቃ የመጨረሻዋን መስመር ለመርገጥም የፈጀባት 8:46.92 የሆነ ሰዓት ነው።
በቤት ውስጥ ቻምፒዮናው በዚህ ርቀት የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው ሌላኛዋ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በአንድ ሰከንድ ብቻ በመዘግየት (8:47.81) ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ልታጠናቅቅ ችላለች። በቤልግሬዱ ቻምፒዮና የዚህ ርቀት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የነበረችው አትሌት ለምለም ኃይሉ፣ በዚህ ውድድር ሶስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የገባችበት ሰዓት 8:49.10 ሆኖ ተመዝግቧል። ይህም ሰዓት ቻምፒዮን ከሆነችበት በ8 ሰከንዶች የዘገየ ነው። በኦሪጎኑ የዓለም ቻምፒዮና በ3ሺ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳሊያ ያገኘቸው የወርቅውሃ ጌታቸው ደግሞ አራተኛዋ አትሌት በመሆን ውድድሩን ፈጽማለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም