የዛሬው አነሳስ በጉዳዩ ላይ ሳያሰልሱ አብዝተውና አምርረው የሄዱበት ድምፃዊያንን (የሀሳብ ተካፋይ ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር) ሚና ለመሻማት አይደለም። እንደ ጥንታዊያኑ የግሪክ ፈላስፎችም “የፍቅር አይነቶች”ን “ስምንት” ብሎ በመዘርዘር ለማብራራት፤ አብራርቶም ተመራምሮ ለማመራመርም አይደለም። ምናልባት (እሱም ከሆነ ነው) የፀጋዬን “ፍቅር ፈራን . . . / መውደድ ፈራን . . .”ን ወደ አንባቢያን ለማጋባት፤ በማጋባት ስነስርዓቱ ሂደትም ከዚሁ፣ ከአፍንጫችን ስር መረጃና ማስረጃዎችን በመጥቀስ አንዳች “ኪናዊ ፋይዳ” ለመፍጠር ነው።
ከሁሉም ከሁሉም በላይ፣ እዚህ አምድ ላይ፣ ለማለት የተፈለገው በታላላቆቹ የእምነት መጻሕፍት ውስጥ ተገቢው ስፍራ ተሰጥቶት፣ ይሁነኝ ተብሎና የሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ የሕይወት መመሪያ ይሆን ዘንድ የሰፈረውን “ፍቅር” በቀጥታ ማብራራት አይደለም። በእነዚሁ መጻህፍት ውስጥ በተደጋጋሚ ስለሚነገረው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰውን መውደድ የሚገባ “አንኮንዲሽናል ላቭ” የሚባለው ስለ መሆኑ እዚህ በቀጥታ ለመድገም አይደለም። እዚህ የተፈለገው፣ እላይ በርእሳችን እንደገለጽነው “ፍቅር እንደ ዋዛ” ከእጅ እየወጣ፣ በድንገትም እየተንሸራተተ . . . ወዴት እየሄደ እንደ ሆነ “አቅጣጫ ለመስጠት” ነው። (ይህች “እንደ አቅጣጫ ከላይ የወረደ . . .” የምትለው ክልሼ ከየት መጣች ደግሞ?።)
ነገሩ እንደ አቅጣጫ ወረደም አልወረደ . . . ከመወያያ ርእስነት አያግደውምና “ፍቅር እንደ ዋዛ” እያመለጠ፤ ከነበረበት ሰገነት እየወረደ . . . ፣ እየተሰደደ . . .፣ እየዘቀጠ . . . መሆኑን ከመነጋገሪያ ርእስነት አያግደውም፤ አያድነውምና እዳው ገብስ ነው። ስለሆነም ከመቀጠልና መተረክ የሚያግደን ነገር የለም። እዚህ ላይ ግን “እንደ አቅጣጫ ከላይ የወረደ . . .” ከላይ “ከሰማየ ሰማያት የመጣ” በማለት “አቅጣጫ ለመስጠት” እንዳልሆነ ከወዲሁ ማሳሰብ እየወደድን “ፍቅር እንደ ዋዛ” እያሸለበ መሆኑን ግን ከስሩ አስምረንበት ወደ ውይይታችን እንቀጥል።
“ፍቅር እንደ ዋዛ” ሲያሸልብ፤ “ፍቅር እንደ ዋዛ” ድፍት . . . ክንብል ሲል . . .፤ “ፍቅር እንደ ዋዛ” አድባርና ቀዬውን ጥሎ እብስስስስስስስ ሲል . . . ኢትዮጵያ የመጀመሪያው አይደለችም። “ፍቅር እንደ ዋዛ” የኋልዮሽ እየሳቀብን ርቆ ወደፊት ሲሄድ . . .፤ “ፍቅር እንደ ዋዛ” . . . ግብአተ መሬቱ ሲፈፀም . . . “ፍቅር እንደ ዋዛ” እንደ ጉም ሲተን . . . ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ምድር አይደለችምና ምንም የሚደንቅ ነገር የለውም።
በዚህ በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮችን ተረት እያደረገ ሲጓዝ የምንናየው፤ በ“ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” ሲስቅና ሲሳለቅ የሚታየው “ፍቅር እንደ ዋዛ”፣ በቅርቡ የሕዝብ ቁጥር ስምንት (8) ቢሊዮን ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው (አንዳንዶች “የሚፈራው” ይሉታል) ወቅት ሲደርስ ምን ሊሆን ነው እያሉ ከወዲሁ መጨነቅ፣ መጠበብ የጀመሩ (በየቤታቸው) በርካቶች ናቸው። ይህ በራሱ ባለቅኔው ዮሀንስ አድማሱ “ይህስ ያሁኑ ነው” መጪውን ደግሞ “ሳያጋይ አይቀርም . . .” በማለት አስቀድሞ የተቀኘውን ያስታውሰናልና እውነትም “ፍቅር እንደ ዋዛ” ከእጃችን እየሾለከ፤ እያፈተለከ ነው ማለት ነው።
በአሁኑ ዘመን ”ፍቅር”ን በተለይ መለያ አርማው ያደረገው ድምፃዊ “ፍቅር ያሸንፋል” ሲል አንድ ያልታየው ነገር አለ ማለት አይቻልም። ከወደፊቱ አንድ የታየው አስፈሪ ጉድ ነበር ማለት ይቻላል። የሚቻለው ግን ድምፃዊው ለራሱ የሰጠው መለያ (ከፈለግን “ብራንድ”፣ ወይም “ማንነት” ልንለው እንችላለን) እንደው ዝም ብሎ ከመሬት የታፈሰ፣ አቦ ሰጡኝ . . . እንዳልሆነና፣ እንደውም ስያሜው ከተሰጠበት ወቅት አጠቃላይ ይዞታ ጋር አስተሳስረን በአውዱ ስንረዳው ነውና፣ የመሸነፉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ “ፍቅር ያሸንፋል” የዋዛ አይደለም።
ባለፈው ጊዜ (እንደ ቀልድ “ጊዜ” እንበለውና)፣ ባሌ/ጎባ ከተማ ውስጥ በደረሰ እርስ በእርስ ግጭት የተነሳ አንደ አባት እያለቀሱ “እኛ እያለን ይህ ከሆነ፣ እኛ ከሞትን በኋላ ምን ሊሆን ነው?” በማለት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት የተናገሩት ለ“ፍቅር እንደ ዋዛ” ርእሳችን አንድ ራሱን የቻለ ማጠናከሪያ ነውና ሳይጠቀስ የሚታለፍ ሊሆን አይችልም።
ምንም እንኳን በዚህ ገጽና አምድ ላይ ስለ “ፍቅር እንደ ዋዛ” እንቆዝም ዘንድ እልፍ አእላፍ ምክንያቶች ያሉን ቢሆንም፣ ነገር ቢበዛ በአህያ አይጫንም ነውና ነገሩ፣ የተወሰኑትን ብቻ እንደ “ስራ ማስኬጃ” እየተጠቀምን እናዘግማለን። “መላ” ካለው ደግሞ ገፋ አድርገን እንሄድበታለን።
እዚህ ላይ “ፍቅር እንደ ዋዛ”ን እና “ፍቅር ያሸንፋል”ን እኩል ሚዛን ላይ አስቀምጠን ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ ለመግባት እቅዱም፣ ፍላጎቱም የለንም። ያለን አንድ ጉዳይ ቢኖር “ፍቅር እያሸነፈ ነው፣ ወይስ እንደ ዋዛ ከእጅ እያመለጠ?” የሚለው ላይ መብሰልሰል (ወይም፣ እኛ ሰሞኑን ድምፃቸው ከፍ ብሎ የሚሰማው አዛውንት እንዳሉት መብሰክሰክ) ነው። ከመብሰክሰካችንና ወንፊት ከመሆናችን በፊት ግን ሁላችንም ለሁላችን ይሆን ዘንድ አንድ ምክንያታዊ ጥያቄ ማቅረብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ እሱም “ለምን?” የሚለው ነው። ለምን???
የክራሯ ንግስት ድምፃዊት አስናቀች ወርቁ አስቀድማ፡-
ፍቅር ፍቅር አሉት፣
ስሙን አሳንሰው፤
ከድንጋይ ይከብዳል፣
ለተሸከመው ሰው።
ማለቷን እናስታውሳለን። በወቅቱም ብዙዎቻችን ከተለመደው እሽኮለሌ ነጥለን አላየነውም (አልተረዳነውም፤ ማጠየቅም አልፈለግንም) ነበር። በሂደት ግን፣ ፍቅር የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ እምብርት፣ የፍጠራን ሁሉ መሽከርከሪያ ኦርቢት፤ ሀገር እንደ ሀገር፣ ህዝብ እንደ ህዝብ የማስቀጠያ ቁልፍ መሳሪያ፤ በሰውና በፈጣሪው መካከል አገናኝ ድልድይ መሆኑን
ተገነዘብን። በመገንዘባችንም አስናቀች ከድንጋይ ይከብዳል” እንዳለችው ሁሉ ክብደቱን ተረዳነው። ተረዳነው እንበል እንጂ የተረዳነው (መልእክቱ እንደ ወረደ ማለታችን ነው) ክብደቱ ለተሸከመው (መሸከም መሰጠትን እንደሚሻ ያስታውሷል) እንጂ ለሌላው ምኑም አለመሆኑን ነው።
አስናቀች በግልፅ ቋንቋ “ለተሸከመው ሰው።” ስትል ምን ማለቷ ነው? ብሎ የሚጠይቅ ሰው ቢኖር፣ በዛው ልክ የሚስቅበት አይኖርም ማለት አይደለም። ያልገባው ባልገባው ልክ ይስቃልና ለእሱ እዚህ ጋ ቦታ የለም!!!
ለጊዜው ምን ታይቷት እንደሆነ ባናውቅም፣ አስናቀች “ለተሸከመው ሰው።” ትበል እንጂ ያልተሸከመውንም ጨምሮ ዛሬ “ፍቅር እንደ ዋዛ” እያልን የምናላግጥበት ፍቅር ከእጃችን (እየተሙለጨለጨ እንኳን ሳይሆን) ዱብ ብሎ በመውደቅ እያመለጠን ነው።
እዚህ ላይ አስናቀችን አነሳን እንጂ “እኔ ወድሃለሁ / በሶስት አማርኛ፣ ስበላም ስጠጣ / ታምሜም ስተኛ” ያለችውንም ድምፀ መረዋ አካትተን (“ሶስቱ አማርኛ” የተባለውን) ፍቅርን ብንመረምረው፣ የፍቅር ጠላት የሆነው ሰይጣን አይስማን እንጂ፣ ስንትና ስንት ውብና የተቀደሱ ነገሮችን ባወጣንለት ነበር።
በርእሳችን “ፍቅር እንደ ዋዛ” ብለን ስንነሳ አንዳንድ አንባቢያን “ምን እንደ አዲስ ነገር ይሄንን ይነግረናል ….፣ ገና ድሮ እብስ ያለውን ጉዳይ . . .” ሊሉን ይችላሉ፤ እውነታቸውን አይደለም ማለት አይቻልም። “አብሮ ከሚበላ . . . / አብሮ ከሚጠጣ” ህዝብ መካከል “ፍቅር እንደ ዋዛ” ፈትለክ ሲልና ሰዎች ከምድረ በዳው ጋር ሲፋጠጡ አይተው ይህንን ቢሉ፤ እንኳን ሊደንቅ አይገርምምና ልክ ናቸው።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን “ምነው እመብርሃን ቀኝ እጅሽን ረሳሻት . . .” ሲል ከሙሉ ፍቅር ገበታ ላይ ተነስቶ፣ አብሮ የመብላትና አብሮ የመጠጣት ወኔ ቆስቁሶት አለመሆኑን ለማወቅ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም። ለዚህ፣ ለተማፅኖ ማቅረብ ድረስ ያበቃው (ባለ ሶስቱ አማርኛ) ፍቅር እንደ ዋዛ ከእጃቸው ያመለጠ ሰዎች በዙሪያው መኖራቸውን አይቶ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ለግጥሙ መቀስቅስ ምክንያቱ ሐዘን እንጂ ደስታ አይደለም፤ ሽብር እንጂ ሰላም አይሆንም . . .፤ እንዲህ እንዲህ እያልን መቀጠል እንችላለን። ቴዲ አፍሮም “ፍቅር ያሸንፋል” ሲል የታየውን፣ ከፊቱ የተደቀነውን አስከፊ ወቅትና ጊዜ ከወዲሁ ለማክሸፍ ነበርና ተሳክቶለታል ወይም አልተሳካለትም ለማለት አንባቢ የሚዳኘው ይሆናል። (እዚሁ ጋ የሬጌው ንጉስ (ቦብ) አብዝቶ ሊወደድ ከቻለባቸው ስራዎቹ አንዱ One Love መሆኑን በቅንፍ አስቀምጦ ማለፍ ያስፈልጋል።)
የዚህ የፍቅር እንደ ዋዛ ሹልክ ብሎ መውጣትና መሰወር በእኛ ብቻ አይደለም የተከሰተው፤ በተለያየ መልኩ አስቀድመው ከፈጣሪያቸው የተቀያየሙ ሀገራት ሁሉ የተጎነጩት የዲያቢሎስ ፅዋ መሆኑን ውስጥ አዋቂያን ተናግረዋል።
በሱዳናውያን መካከል የነበረው ፍቅር እንዲህ እንደ ዋዛ ሹልክ ብሎ ከእጃቸው ሊወጣ የቻለው በውስጣቸው ባለው አተካራ ምክንያት መሆኑ ሲጠቀስ፤ ፍቅር ከሊቢያ እንደ ዋዛ አፈትልኮ ለመውጣቱ እንደመንስኤ የሚነገረው ሙሉ ለሙሉ የውጭ ጣልቃ ገብነት ስለመሆኑ ይገለፃል:: ሊቢያዊያንን ለዚህ የዳረጋቸው ድንበር ተሻግሮ የመጣባቸው “ዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ” የሚሉት “ርእዮት” መሳይ ዲያቢሎስ ነው። የሶሪያዊያንም እንደዛው።
በዩክሬን ላይ እየወረደ ያለው ውርጅብኝ መንስኤው እሷ ሳትሆን በእርሷ እና ሩሲያ መካከል የገባው ተኩላ ነው፤ በሁለቱ መካከል ያለውን ፍቅር እንደ ዋዛ አፈትልኮ እንዲወጣ ያደረገው የሚሉ (የኮንስፒራሲ ቲየሪ አራማጆች ይሁኑ/አይሁኑ ባይታወቅም) ቁጥራቸው በየጊዜው እየጨመረ እንጂ ሲቀንስ አይታይም። እነዚህንና ሌሎችንም ሁሉ በማየት ነው እንግዲህ ፍቅር እንደ ዋዛ እያፈተለከ፤ ሰውም ከፈጣሪው እየተጣላ . . . ያለው:፡ ይህ እዚህ ብቻ ሳይሆን እዚህም እዛም ነው እንል ዘንድ የልብ ልብ የሰጠንም ይኸው ነው።
የዚህ የ“ፍቅር እንደ ዋዛ” ጉዳይ በእጅጉ ያሳሰባቸውና ጉዳዩንም በቅርብ የሚከታተሉና የሚያውቁ አዛውንቶች እንደሚሉት “ፍቅር እንደ ዋዛ” ከሀገራችን ሊያፈተልክና ሊወጣ የመሆኑ ምልክት መታየት የጀመረው ዛሬ ሳይሆን ሰነባብቷል። ለእዚህ ደግሞ የነበረው የመሪዎች አያያዝ፣ የአመራር “ጥበብ”፤ እንዲሁም የገሚሱ በተቀደደለት ቦይ የመሄዱ ጉዳይ ነበርና የዛሬው እዚህ መድረሳችን ሊገርም አይገባም።
እንደ እነዚሁ አዛውንት ታዛቢዎች ትዝብት ከሆነ “ፍቅር እንደ ዋዛ” ሽል (ሹልክ ቢል፣ ሳይታይና ሳይዳሰስ) ማለት የጀመረው በሰገሌ ጊዜ ሳይሆን በእነ እንቶኔ ጊዜ ነው። የእነሱ ተቃራኒዎች ደግሞ ጉዳዩን ወደ ኋላ በክፍለ ዘመናት ያስፈነጥሩት በእነ እንቶኔ ጊዜ ነው ይባባላሉ። በዚህ መሀል ነው አሉ “ፍቅር እንደ ዋዛ” የተባለው ሰማያዊ ፀጋ በምድራዊው ኃይል ምክንያት ከቤታችን፣ ከአድባርና ቀያችን ፈትለክ ብሎ በመውጣት ስፍራውን ለዲያብሎስ ያስረከበው።
ዛሬ ፍቅር እንደ ዋዛ ከእጃቸው እየወጣ ያሉ ሀገራት በአብዛኛው ትናንት ፍቅር በፍቅር የነበሩ ሲሆን፣ በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ውሃ ይጠጣል? እንዲሉ፣ ጠብ ያለሽ በዳቦ እያሉ ፍቅርን ከጉያቸው እያስወጡት፤ በአብሮነት ድርቅ እየተመቱ፤ በልዩነት ጎርፍ እየተጠረጉ፤ ባለመግባባት አንደበት እየተጠዛጠዙ ይገኛሉ።
እድሜ ለካጋሜ እንጂ ሩዋንዳ እንደ ዋዛ አምልጧት የነበረውን ፍቅር ስናስታውስ ዛሬ በዓለም ካርታ ላይ ባልኖረችም ነበር። (“በጥባጭ ካለ . . .” ያልነውን ያህል ለካ መሲህም አለ።)
ሶማሊያ ፍቅር ከእጇ ሊያፈተልክ ቋፍ ላይ ስትሆን፣ የእለት ተእለት ዜናው የሚነግረን ግን እሷ ራሷ በ“አለች” እና “የለችም” መካከል ላይ መሆኗን ነው ። (ከአጠቃላይ ሀገሪቱ ከ80 በመቶ በላይ በአልሻባብ እጅ መኖሩን ልብ ይሏል።)
Multiple state-based conflicts in Africa are related to the rise and expansion of the Islamic State (IS). እንዲል ኖቬምበር 2022 ለአደባባይ የበቃው ጥናት፣ በዚህ ምክንያት ብቻ በ2021 ዘጠኝ የአፍሪካ ሀገራት በከፋ ትርምስ ውስጥ ሆነው ነበር። አሁን ከዚህ ትርጉም የለሽ ግጭት ወጥተዋል/አልወጡም የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ በአፍሪካ ፍቅር ወጣ/ገባ መጫወት ከጀመረ ሰነባብቷል። (ካስፈለገ “Conflict Trends in Africa, 1989-2021” የሚለውን ጥናት እያንገሸገሸም ቢሆን መኮምኮም ይቻላል።)
የእነ ኮንጎ (DRC)፣ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሩን፣ ሴንተራል አፍሪካን ሪፐብሊክ (CAR)፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ሱዳን . . . አዳርና ውሎ ያው የምናውቀው ሲሆን፤ ደቡብ ሱዳን . . . ዝም ነው።
“ፍቅር ኮበለለ” (ወይም እየኮበለለ ነው) ለማለት ያህል እነዚህን እንጥቀስ እንጂ፣ ዓለም በአጠቃላይ ፍቅርን እየነቀለች ጥላቻን እየተከለች ነው። አፍሪካ ውስጥ የቱ ጋ ግጭት እንዳለ ከመፈለግ የቱ ጋ ፍቅር እንደሌለ መፈለጉ ይቀላል። በዘመን አመጣሹ ማህበራዊ ሚዲያ እየተዘራ ያለው ምን እንደሆነ የማያውቀው ጥቂት ነው። በዓለም ካርታ ላይ የፍቅር ድርሻ እየጠበበ፤ የጥላቻ ወሰን እየሰፋ በመምጣት ላይ ስለመሆኑ ለማወቅ ምንም መታተር ሳያስፈልግ በአንድ “ክሊክ” መረዳት ይቻላልና ወደ እዛ አንገባም።
የዚህ ጽሑፍ የመጨረሻ ጥያቄ “እዚህስ?” ሲሆን፣ መልስ ይሆናል/አይሆንምን ትተን ስናጠቃልለው፡-
እህ ዛዲያማ
እህ ዛዲያማ
ምን ልበላችሁ፣
ታውቁት የለም ወይ በየቤታችሁ።
***************
“አገር እግር አለው
ይሄዳል እንደ ሰው፣
በየ ጎራው፣ በየ ወንዙ ሆኖ
ጀግና ካልመለሰው።” (የዚህን ግጥም ባለቤት ያገኘ ይሸለማል።)
ቸር እንሰንብት!!!
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን የካቲት 2/2015