ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከ12ኛ ሳምንት ጀምሮ ያሉትን መርሃግብሮች በድሬዳዋ ስቴድየም እንደሚያካሂድ ታውቀል:: ፕሪሚየር ሊጉ በመጪው ሳምንት መጨረሻም በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል በሚካሄደው ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀጥል መሆኑንም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አስታውቋል::
በአልጄሪያ አስተናጋጅነት የተካሄደውን የአፍሪካ አገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) ውድድር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተሳታፊ መሆኑን ተከትሎ ከሳምንታት አስቀድሞ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መቋረጡ የሚታወስ ነው:: የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከአልጄሪያ ጉዞው በመመለሱና ተጫዋቾችም ወደ ክለቦቻቸው በማቅናታቸው ከባለፈው ሳምንት (27/2015ዓ.ም) አንስቶ ሊጉን በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም ሊሳካ አልቻለም:: በመሆኑም ሊግ ካምፓኒው የቦታ ለውጥ ማድረጉን ትናንት በላከው መግለጫ አስታውቋል:: በዚህም መሰረት ፕሪሚየር ሊጉ ከተቋረጠበት ከ12ኛ ሳምንት ጀምሮ ያሉትን ጨዋታዎች በድሬዳዋ ስቴድየም እንዲቀጥል ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቀል::
ሊግ ካምፓኒው የፕሪሚየር ሊጉ የ11ኛ እና 12ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ጨምሮ ከ14ኛ ሳምንት በኋላ ያሉ መርሃግብሮችን ከመጪው ቅዳሜ የካቲት 04/2015ዓ.ም ጀምሮ ያካሂዳል:: ሊጉ ከተቋረጠበት የሸገር ደርቢ (ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ) የሚቀጥል ሲሆን፤ ከቀኑ 11ሰዓት በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስቴድየም እንደሚከናወንም አስታውቋል:: የስቴድየሙ ሜዳ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የከተማው ጸጥታ ክፍልም ውድድሩን ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውን በደብዳቤ እንዳረጋገጡ በመግለጫው ተጠቁሟል::
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የውድድር መርሃ ግብር ከ14ኛ እስከ 19ኛ ሳምንት ያሉ ጨዋታዎችን እንዲሁም ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎችን ለማካሄድ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከጸጥታ ክፍሉ ጋር በመነጋገር ከሶስት ወራት አስቀድሞ ከስምምነት ደርሶ ነበር:: በዚህም መሰረት አወዳዳሪው አካል፣ የሊጉ ክለቦች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት አስቀድመው ነበር ወደ ስፍራው የተጓዙት:: የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡናን ተስተካካይ ጨዋታም በመርሃ ግብሩ መሰረት ጥር 27/2015ዓም ሊካሄድ ነበር:: ይሁንና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ከላይ በተሰጣቸው አቅጣጫ መሰረት ውድድሩን ማካሄድ እንደማይችሉ በመግለጻቸው ውድድሩ ሊካሄድ እንዳልቻለ ይታወቃል::
ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያውን ከሚያደርግበት ጊዜ አስቀድሞ ሊጉን ማጠናቀቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም የአክሲዮን ማህበሩ ቦርድ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ ከውሳኔ ደርሷል:: ይኸውም ውድድሩን በመርሃ ግብሩ መሰረት በአዳማ ማስቀጠል ስለማይቻል የባህርዳር እና ድሬዳዋ ስቴድየሞችን በአማራጭነት በመያዝ፤ ሶስት ሶስት አባላት ያሉት ኮሚቴ በሁለቱ ሜዳዎች ላይ ግምገማ እንዲያደርጉ ከውሳኔ ደርሷል:: ኮሚቴዎቹም ከስራ አስፈጻሚ እንዲሁም ከውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ የተወጣጡ ሲሆኑ፤ ሜዳዎቹን እንዲሁም የከተሞቹን ሁኔታ ከሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ገምግመዋል::
በዚህም መሰረት የስራ አመራር ቦርዱ የኮሚቴዎቹን ሪፖርት በመመልከት ከውሳኔ ላይ ደርሷል:: የተስተካከለ ሜዳ ያለው የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስቴድየም ለተጨማሪ የግንባታ ስራ ኮንትራት የተሰጠ በመሆኑ ማስቆም እንደማይቻል በቃል ገልጸዋል:: የድሬዳዋ ስቴድየም በአንጻሩ ከሜዳው ሁኔታም ሆነ ከጸጥታው ጋር በተያያዘ ዝግጁ መሆኑን በመግለጹ ሊጉ በድጋሚ ወደ ከተማው መመለሱን በአክሲዮን ማህበሩ በኩል አስታውቋል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 1 ቀን 2015 ዓ.ም