በፈረንጆቹ የጥቅምት ወር መጀመሪያ ከሚካሄዱ የግማሽ ማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ በስፔን የሚካሄደው የግራኖለር ግማሽ ማራቶን ሩጫ ነው። በስፔኗ ባርሴሎና አስተናጋጅነት የሚካሄደው ይህ የሩጫ ውድድር መነሻውን እአአ በ1987 የሚያደርግ ሲሆን፤ በየዓመቱ እየተከናወነ ከዚህ ደርሷል። ኢትዮጵያዊያን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ አትሌቶችን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር በወንዶች ኢትዮጵያዊው ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እአአ በ2005 እና 2006 በተከታታይ አሸናፊ በመሆኑ በተለየ መልኩ ይታወሳል። በሴቶች በኩልም እአአ በ2006 አንጋፋዋ አትሌት ጌጤ ዋሚ አሸናፊ ከመሆኗ ባለፈ በወቅቱ ያስመዘገበችው 1:10:24.2 የሆነ ሰዓት እስካሁንም ድረስ ሊደፈር ያልቻለ የቦታው ክብረወሰን በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል።
በዚህ ውድድር ያለፉትን ዓመታት በተለይ ኬንያዊያን አትሌቶች የበላይ ሆነው ቢቆዩም ከትናንት በስቲያ በተካሄደው ውድድር ላይ ግን የበላይነቱ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መመለሱ ተረጋግጧል። 10ሺ ሯጮች የተካፈሉበት ይህ ውድድር በወንዶች በኩል ኢትዮጵያዊው አትሌት ሃጎስ ገብረህይወት የስፍራውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፏል። በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ይዘው በመፈጸም የበላይነቱን መውሰዳቸውን ማይ ቤስት ራንስ የተሰኘው ድረገጽ አስነብቧል።
በዚህ የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ከተካፈሉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል አንዱ ኬንያዊው ሳሙኤል ዋንጂሩ ነው። ይህ አትሌት እአአ በ2008 እና 2009 የዚህ ውድድር አሸናፊ ሲሆን፤ በመጀመሪያ ተሳትፎው ርቀቱን 59ደቂቃ ከ26 ሰከንዶች በመሸፈን ነበር በስፍራው አዲስ ሰዓት ያስመዘገበው። ይህም ክብረወሰን ለ15 ዓመታት የሚያሻሽለው አትሌት ሳይገኝ ቆይቷል። በዘንድሮው ውድድር ግን ኢትዮጵያዊው አትሌት ሃጎስ በአንድ ደቂቃ ፈጥኖ በመግባት የስፍራውን ክብረወሰን የግሉ ማድረግ ችሏል። በሪዮ ኦሊምፒክ በ5ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው ሃጎስ ከጉዳት ጋር በተያያዘ ባለፉት ዓመታት በውድድሮች እምብዛም ሳይታይ ቆይቷል።
በሞስኮ እና ቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ላይ በሚታወቅበት ርቀት የብር እና የነሃስ ሜዳሊያዎችን የግሉ ማድረግ የቻለው ሃጎስ፤ በተለይ የሚታወቀው በመም ሩጫዎች ላይ ነበር። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ በጎዳና ላይ ሩጫ ዳግም በአዲስ ብቃት ወደ ውድድር መመለሱን ያስመሰከረው አትሌቱ ሩጫውን በአሸናፊነት አጠናቋል። የስፍራውን ክብረወሰንም ያሻሻለው 58ደቂቃ ከ55 ሰከንዶች በመግባት ነው። ይህም አትሌቱን በውድድሩ ታሪክ ከ1ሰዓት በታች በመግባት ሁለተኛው አትሌት ያደርገዋል። አትሌቱን ኬንያውያን ተከትለውት የገቡ ሲሆን፤ ኤድመንድ ኪፕኔጌቲች እና ነሂሚሃ ኪፕዬጎን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ሆነዋል። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርሃኑ ታርቶ ደግሞ በአራተኝነት ውድድሩን ሊፈጽም ችሏል።
በሴቶች በኩልም በተመሳሳይ ውድድሩ በፈጣን ሰዓት ተደምድሟል። ውድድሩ ሶስት ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ተከታትለው የገቡበት ሲሆን፤ በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት እጅ የነበረው ክብረወሰን የተሰበረበትም ነበር። ሩጫውን አጠናቃ በቀዳሚነት የገባቸው አትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ 1:06:40 የሆነ ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች። አትሌቷ በሃገሯ ልጅ ከተያዘው ሰዓትም አራት ደቂቃ ፈጥና በመግባት አስደናቂ ብቃቷን አስመስክራለች።
በጠባብ ደቂቃዎች ልዩነት ትዕግስትን ተከትለው የገቡት የሃገሯ ልጆችም ያስመዘገቡት ሰዓት በተመሳሳይ ፈጣን በመሆኑ ከዚህ በኋላ በስፍራው ሰዓት ማሻሻልን አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችልም የሚገመት ነው። በሁለት ደቂቃ ዘግይታ በመግባት ሁለተኛ የሆነችው አትሌት ቤተልሄም አፈንጉስ ስትሆን፤ ሩጫዋን የፈጸመችበት ሰዓትም 1:08:08 ሆኗል። በግማሽ ማራቶን ሩጫዎች ልምድ ያላት ይህች አትሌት ባለፈው ዓመት የማድሪድ ግማሽ ማራቶን ውድድርን በሶስተኝነት ደረጃ ነበር ያጠናቀቀችው። ሌላኛዋ አትሌት አዲሴ አንዷለም ደግሞ 1:09:34 በሆነ ሰዓት በመግባት የሶስተኝነት ደረጃን መያዝ ችላለች።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም