ወይዘሮ ብርቄ ንጋቱ ይባላሉ:: ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዯቸውም ከትዳራቸው አምስት ልጆች አፍርተዋል:: አሁን ደግሞ የአምስት የልጅ ልጆች አያት መሆን ችለዋል:: ከልጆቻቸው አልፈው የልጅ ልጆቻቸውን በማስተማር ላይ ይገኛሉ:: ዛሬ ላይ ቀደም ሲል ይደርስ የነበረውን መገለል ተቋቁመው እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ሰርተው አምስቱንም ልጆቻቸውን በማስተማራቸው ልጆቻቸው የመንግስት ሠራተኞች ሆነውላቸዋል:: ወይዘሮ ብርቄ በስጋ ደዌ በሽታ የተጠቁት የስድስት ዓመት ልጅ ሆነው ነው:: ችግሩ የተከሰተው በልጅነት እድሜያቸው ስለነበር እንዴት እንደጀመራቸው አያስታውሱም:: ነገር ግን ቤተሰቦቻቸው ቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም ባለማድረሳቸው በሽታው እየተባባሰባቸው እንደመጣ ይናገራሉ::
‹‹……በወቅቱ ቤተሰቦቼም ቢሆኑ ስለ በሽታው ምንም ግንዛቤ አልነበራቸውና አካል ጉዳቱ ደረሰብኝ›› ሲሉም ሁኔታውን ያስታውሱታል:: በሽታው ጉዳት ያደረሰው እጅና እግራቸውን ጨምሮ በሁሉም የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ነው:: ሆኖም ደጋግመው ቢሆንም በፍፁም ከመሥራት እንዳላገዳቸው ያወሳሉ:: ወይዘሮ ብርቄ አካል ጉዳቱ ከደረሰባቸው በኋላ ነው ወደ አለርት ሆስፒታል ነው የሄዱት:: ምንም እንኳን ቶሎ ወደ ሆስፒታል ባለመሄዳቸው የሰውነት ክፍላቸው በበሽታው ቢጎዳም ሆስፒታል ከሄዱ በኋላ በተደረገላቸው ሕክምና የስጋ ደዌ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ ከውስጣቸው መወገድ በመቻሉ ከበሽታው ነፃ ሆነዋል::
‹‹ባክቴሪያው ከውስጤ በመጥፋቱና ከበሽታው ነፃ በመሆኔ በእጅጉ ተደስቻለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ ብርቄ ‹‹ ይህ መሆኑ ራሴን መቻል እንዳለብኝ እንዳውቅና የተስፋ ሕይወት እንዲኖረኝ አደረገኝ›› ሲሉም ከበሽታው ነፃ የመሆናቸውን ሁኔታ የፈጠረባቸውን ለስራ አነሳሽና አስደሳች ስሜት ያወሱታል:: ‹‹አሁን ከባክቴሪያው ነፃ ነኝ:: ምንም ዓይነት የሚሰማኝ ህመም የለም›› ሲሉም የውስጣዊ የሰውነት ጤንነታቸውን ሁኔታ ያስረዳሉ “::
‹‹እኛ እኮ የአካል ጉዳት ነው ያለብን እንጂ ጤነኞች ነን›› የሚሉት ወይዘሮ ብርቄ ሆኖም የአካል ጉዳቱ ከመስራት እንደማያግዳቸውም በራስ በመተማመን መንፈስ ይገልፃሉ:: በሌላ በኩልም የስጋ ደዌ በሽታን አምጪ የሆነው ባክቴሪያ ከአቅም በላይ የሥራ ጫና ስለማይስማማው እሳቸውም አቅማቸው የፈቀደውን ይሰራሉ:: በዚህም የተለያዩ የእደ ጥበብ ስራዎች ምርት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ::
ከዚህ የእጅ ጥበብ ሙያ ጥሩ ልምድ በማግኘትም ከሌሎች እንደሳቸው በበሽታው ከተጠቁ ሴቶች ጋር በማህበር በመደራጀት ቀጥታ ወደ ሥራ ለመሰማራት መቻላቸውን ያወሳሉ:: ይሄ ወይዘሮ ብርቄና ሌሎቹ የበሽታው ተጠቂዎች ወደ ሥራ የገቡበት ወቅት 2009 ዓ.ም ነበር:: በዚህ ወቅት 35 ሴቶች ሆነው ከአራት ወንድ አባላት ጋር ‹‹ክብነሽና ጓደኞቻቸው ዕደ ጥበብ ሥራ ሕብረት ሽርክና ማህበር›› የተሰኘውን ማህበራቸውን መሰረቱ:: ወይዘሮ ብርቄ የማህበሩ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እየሰሩ ሲሆን ማህበሩን መመስረትና በማህበሩ ውስጥ በዕደ ጥበብ ሥራ የመስራት ልምድ ያላቸው መሆኑ ሥራው እንዳይከብዳቸው አስተዋጽኦ አድርጎላቸዋል:: ዛሬ ከየኪሳቸው ባወጡት 900 ብር የመሰረቱት ማህበር ካፒታል 500 ሺህ ብር ደርሷል:: ለመንግስት ግብር በመክፈልም እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ለአገራቸው ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ::
ብዙዎቹ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ሕክምናውን በተከታታይ በማግኘታቸውና በማህበር ተደራጅተው በጋራ በመሥራታቸው ከልመና መላቀቃቸውንም ያነሳሉ:: በበሽታው ምክንያትና በገጠማቸው የኑሮ ጫና ምክንያት ከዚህ ቀደም ልጆቻቸውን እንኳን የማስተማር አቅም እንዳልነበራቸው ይገልፃሉ:: አሁን ራሳቸው በመሥራት አቅም ከመፍጠራቸው ውጪ ከልመና ወጥተው ልጆቻቸውን ማስተማር መቻላቸውንም ይናገራሉ::
ወይዘሮ ሰውነት አእምሮ ከነዚህ እናቶች መካከል አንዷ ናቸው:: ተወልደው ያደጉት ደብረ ማርቆስ ሲሆን በሥጋ ደዌ በሽታ የተጠቁት ገና የሰላሳ ዓመት ወጣት ሳሉ ነው:: ወይዘሮ ሰውነት በበሽታው የተያዙ ሰሞን ፈጥነው ሕክምና ባለማግኘታቸው በእጅና እግራቸው ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት በሕብረተሰቡ በእጅጉ ይገለሉ የነበረ ሲሆን በማህበር፤ በዕድር፤ በዕቁብ በለቅሶ እንዳይሳተፉም ሆነው ስለመቆየታቸው ይናገራሉ:: በዚህም ሳቢያ ቀደም ሲል ወደ ትውልድ አገራቸው ደብረ ማርቆስ የመመለስ ሀሳባቸውንም እዛም የባሰ መገለል ይደርስብኛል በሚል ፍራቻ ትተውት ከነጉዳታቸው አለርት ሆስፒታል አካባቢ መኖር ጀመሩ:: ወይዘሮ ሰውነት ዕድሜያቸውን በውል ባያውቁትም ቢያንስ ስልሳውን መድፈናቸውን ይናገራሉ:: የማህበሩ መሥራችና አባልም ናቸው::
በሽታው በእጅና በእግራቸው ላይ ከባድ ጉዳት አድርሶባቸው ቢያልፍም በአሁኑ ወቅት ሕክምና አግኝተው ከባክቴሪያው ነፃ ለመሆን ችለዋል:: ቁጭ ብለው ለዓይን የሚማርኩና የሚያስደስቱ የእጅ ጥበብ ሥራዎችን በሚያስደንቅ ሁኔታ ይሰራሉ:: ሦስት ልጆቻቸውንም ማሳደግና ለቁም ነገር ማብቃት ችለዋል:: አሁን ልጆቻቸው ከራሳቸው አልፈው እሳቸውን መደገፍ ጀምረዋል:: ወይዘሮ ሰውነት በማህበሩ ታቅፈው በዚህ ዓይነቱ የእጅ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት ለረጅም ጊዜ ይተዳደሩ የነበረው በልመና ሥራ እንደነበር ይናገራሉ::
‹‹እኛ የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች መሥራትና መኖር የምንችል የሕብረተሰብ ክፍሎች ነን›› የሚሉት ሌላዋ የማህበሩ መሥራች አባል ወይዘሮ እታገኝ መለሰ አባላት ማህበሩን የመሰረቱት በዕድር፤ በእቁብ፤ በማህበርና በተለያዩ ሁኔታዎች ከሕብረተሰቡ እንዳይገለሉና መገለል የሚያደርስባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ተቋቁመው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ብሎም አገራቸውን ለመጥቀም በማሰብ ነው ይላሉ::
ወይዘሮ እታገኝ ትውልድና ዕድገታቸው ጎንደር ገጠር ከተማ ውስጥ ነው:: በበሽታው የተያዙት ገና የ11 ዓመት ልጅ ሆነው ሲሆን ለህክምና ወደ አዲስ አበባ ያመጧቸው የአባታቸው ወንድም ናቸው፤ በወቅቱም አለርት ሆስፒታል ህክምናቸውን ከመከታተላቸውም በላይ እስከ 11ኛ ክፍል ድረስም ትምህርት አስተምረዋቸዋል:: በትምህርት ላይ እያሉ ጭምር ከባድ የጉልበት ሥራዎችን በመሥራት ነበር እራሳቸውን የሚያስተዳድሩት:: ሥራው ከባድ በመሆኑና የበሽታው ሐኪሞች ከባድ ሥራ መሥራት በሽታውን እንደሚያባብሰው ሲናገሩ ሰምተናል የሚሉ ሰዎች ስላስፈራሯቸው ባክቴሪያውን በመቀስቀስ ዳግም በበሽታው እጠቃለሁ የሚል ስጋት ነበራቸው:: በማህበር ተደራጅተው መሥራታቸውና ከከባዱና ከሚያሰቃየው የጉልበት ሥራ መላቀቃቸው በጫናው ምክንያት ይደርስባቸው ከነበረው ስጋታቸው ገላግሏቸዋል:: ወይዘሮ እታገኝ አሁን ላይ በሰውነት ክፍላቸው ላይ ምንም ጉዳት ስለሌለ የበሸታው ተጠቂ ባይመስሉም በህክምና ባክቴሪያው እንዳለባቸው ስለተረጋገጠ ብሎም የአካባቢው ነዋሪዎች በሽታው እንዳለባቸው ስለሚያውቁ የማህበሩ መሥራች አባል ሆነው በመታቀፍ ስራዎችን እየሰሩ በየወሩ የአንድ ሺህ ብር ደሞዝ ተከፋይ ሆነዋል:: ማህበሩን እንዲያደራጁ ሁኔታዎችን ያመቻቹላቸውን የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ብሔራዊ ማህበርም ደጋግመው ያመሰግናሉ:: ‹‹በማህበር መደራጀት የቻልነው ብሄራዊ ማህበሩ በመኖሩና በእሱ ታቅፈን መንቀሳቀስ በመቻላችን ነው›› ሲሉ ሀሳባቸው ያሳርጋሉ::
አቶ ተስፋዬ ታደሰ የኢትዮጵያ ሥጋ ደዌ ብሔራዊ ማህበር ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ ማህበሩ በሰባት ክልል ከ70 ቅርንጫፍ ማህበራትን አደራጅቷል:: እንደ አገር ከ20 ሺ የስጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎችን አቅፏል:: በበሽታው ከተጠቁት ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ሴቶች መሆናቸው ደግሞ ማህበሩ ሁሉም ላይ ቢሰራም ሴቶች ላይ የበለጠ እንዲሰራ አድርጎታል ባይ ናቸው::
አብዛኞቹ አባላት ሴቶች ሊሆኑ የቻሉበት ምክንያት አንድም ሴቶች እንደወንዶቹ መረጃ የማግኘት ሰፊ ዕድል ስለሌላቸውና የበሽታውን ምንነት በውል ስለማያውቁት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በቤት ውስጥና በተለያየ ቦታ ባለባቸው የሥራ ጫና ምክንያት ቶሎ ወደ ሕክምና ስለማይሄዱ ነው:: ከሁሉም በላይ ደግሞ መረጃው ቢኖራቸውና መሄድ ቢፈልጉም ከትራንስፖርት ወጪ ጀምሮ ለሕክምናውና የሚያስፈልገውን ወጪ የሚሸፍን አቅም የላቸውም::
በሽታው የእግዚአብሔር ቁጣ ነው፤ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል ለሚለው የተዛባ አስተሳሰብ እንዳይጋለጡ ፈርተው ወደ ሕክምና የማይሄዱበት አጋጣሚም ቀላል አይደለም:: በዕቁብ፤ በዕድር፤ በማህበርና በለቅሶ መገለሉንም ስለሚፈሩት ራሳቸውን ይደብቃሉም:: በአጠቃላይ ወንድም ሆኑ ሴት የበሽታው ተጠቂዎች የሚደርስባቸውን መድሎና መገለል በመፍራት ለዘመናት ራሳቸውን ከሕብረተሰቡ አርቀው በቤተክርስቲያን ጥጋት፤ በየሥርቻው እንዲሁም ለመኖር በማይመቹና ለሰው ልጅ በማይገቡ ቆሻሻ ሥፍራዎች በልመና እና በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ በጉስቁልና በመኖር የከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ሰለባ ሆነው ቆይተዋል:: በተዛባ የሕብረተሰቡ አመለካከት ምክንያትም አሁን ድረስ ብዙዎቹ ራሳቸውን ከህብረተሰቡ በማግለል በከባድ የኑሮና ስነ ልቦና ጫና ውስጥ መሆናቸውንም አቶ ተስፋዬ ያነሳሉ::
ማህበሩ ይሄን ችግራቸውን ለመቅረፍ ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት በሥጋ ደዌ በሽታ የሚመጡ የአካል ጉዳቶችን በመቀነስ፤ በበሽታው ምክንያት የሚመጡትን አካላዊ፤ መንፈሳዊ፤ ማህበራዊ መገለሎችን ለማስቀረት እንዲሁም አዳዲስ የሥጋ ደዌ በሽታ እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ የሚደረግበት ግንዛቤ በመፍጠር ሲሰራ መቆየቱንም አቶ ተስፋዬ ይገልጻሉ::
ብሔራዊ ማህበሩ የወፍጮ ቤት፤ በዓመት እስከ ስድስት ሚሊዮን ብር የሚያስገኝ የሚከራይ ቤት፤ የከብት እርባታና የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በአዲስ አበባ በሀዋሳ፤ በኮምቦልቻ ፤ በባህር ዳር፤ በጎጃም ሸበል በረንታ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚገኙና በበሽታው ለተጠቁ አባላቱ በማህበራዊ ኑሯቸው ወደኋላ ለቀሩ ድጋፍ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ:: አብዛኞቹን በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀትም ወደ ሥራ አሸጋግሮ አምራች አድርጓቸዋል:: በዚህም ብዙ ሴቶች እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል ሰርተው መኖር፤ ቤተሰባቸውን ማስተዳደር በተለይም ደግሞ ልጆቻቸውን ማስተማር ችለዋል::
ተጠቂዎቹ በመገለላቸው ምክንያት ከወደቁበት ከቤተክርስቲያን መጠለያና ከአልባሌ ሥፍራዎች በማውጣት ቤት መሥሪያ ቦታ፤ እንዲሁም የቀበሌና የኪራይ ቤት ባለቤቶች በመሆን ከሕብረተሰቡ ተቀላቅለው በነፃነት እንዲኖሩ እንዲሁም ተከታታይ ሕክምና እንዲያገኙ መደረጉንም ይናገራሉ::
‹‹ማህበሩ ከመመስረቱ በፊት አካል ጉዳቱ ባስከተለባቸው ጫና ምክንያት ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ የማይችሉ ወላጆች ቁጥር ከፍተኛ ነበር›› የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ የሚያስችል አቅም ስለፈጠረላቸው ከትምህርት የመገለል ችግር ተቀርፎላቸዋል:: በዚህም ልጆቻቸው በኮሌጅና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ተምረው በመመረቅ ራሳቸውን ችለው እየኖሩና ቤተሰባቸውን እያገዙ ይገኛሉ::
በሴቶች ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች የአድቮካሲና መብት ጥበቃ ዴስክ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጥላሁን መሥሪያ ቤታቸው ለሥጋ ደዌ በሽታ ተጠቂዎችም እንደማንኛውም አካል ጉዳት የእኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት መብታቸው እንዲከበር በትኩረት እየሰራ ይገኛል:: ሥራውን ከማህበሩና ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራው ሲሆን ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበርም ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት ይሰራል:: በተለይ መገለልና መድሎ ቀርቶላቸው ከሕብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው በሚኖሩበት ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል:: እንደ መጠለያ፤ ምግብ ያሉና ሌሎች መሰረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟሉላቸው በየደረጃው ይሰራል:: ሕክምናውን ተከታትለው ከበሽታው ነፃ እንዲወጡም እየተደረገ ይገኛል ::
‹‹ሥጋ ደዌ ህክምና ካልተደረገለት አደገኛ እና ቋሚ የሆነ ጉዳት በቆዳ፣ በነርቭ እና በአይን፤ በአፍንጫ ላይ ሊያደርስ የሚችል ነው›› የሚሉት አቶ ሲሳይ በዚህ ምክንያት ሕክምና እንዲያገኙ ትኩረት እንደሚያደርግ ሁሉ በበሽታው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ከማህበሩና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የዊልቸርና የተለያዩ ለእንቅስቃሴ የሚያመቹ ድጋፎችም ይደረጋሉ:: በተለያዩ ማህበራት ተደራጅተው የኢኮኖሚ ችግራቸውን እንዲቀርፉም ይሰራል:: በተለይ መገለልና መድሎ ተወግዶላቸው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን በመፍታት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረጉ ረገድ በትኩረት እየተሰራ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ለውጥ ቢመጣም ገና ብዙ መሰራት የሚፈልግና የሚቀር ስራ መኖሩን ይናገራሉ::
የሥጋ ደዌ ከቀደምት የቻይና፣ የግብፅ እና የህንድ ሥልጣኔ ጀምሮ የነበረ ሲሆን የሥጋ ደዌ ተጠቂዎች ለዘመናት በሚኖሩበት ማህበረሰብና ቤተሰቦቻቸው የመገለል አደጋ ሲደርስባቸው ቆይቷል። የመጀመሪያው የሥጋ ደዌን የሚጠቅስ ጽሁፍ የተጻፈው 600 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የሥጋ ደዌ ህመምተኛ በመልቲ ድራግ ትሪትመንት ለስድስት ወራትና ለ12 ወራት ታክሞ መዳን ይችላል። ኤምዲቲ መውስድ ከጀመሩ በኋላ ህሙማን ሥጋ ደዌን ወደ ሌላ ሰው እንደማያስተላልፉ ከበሽታው ጋር ተያይዘው የወጡ ጽሑፎች ይጠቅሳሉ::
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም