የ2014 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት ከቀናት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል:: የትምህርት ሚኒስቴር በገለፀው መሰረት፣ ፈተናውን ከወሰዱ 899ሺ520 ተማሪዎች መካከል ከግማሽ በላይ ውጤት (ከ350 በላይ) ማስመዝገብ የቻሉት 29ሺ909 (3.3%) ብቻ ናቸው:: ከ50 በላይ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ አዲስ አሰራር ለመከተል መታቀዱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል::
በዚህ አሰራር ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ይሆናሉ፤ቀሪዎቹ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም መሰረት በማድረግ የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ተመርጠው ወደ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡ ይደረጋል፤ይሁን እንጂ እነዚህ ተማሪዎች በቀጥታ የአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አይሆኑም፤ተማሪዎቹ ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገቡባቸውን የትምህርት ዓይነቶች ለአንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተማሩ ከቆዩ በኋላ፣ በዓመቱ መጨረሻ ፈተና ተፈትነው ካለፉ በዩኒቨርሲቲዎች የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ሆነው ይቀጥላሉ::
ውጤቱ ይፋ ከተደረገ በኋላ ብዙ ዓይት አስተያየቶችን አስተናግዷል:: አንዳንዶች ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ የትምህርት ጥራት አለመኖሩን የሚያመለክት እንደሆነ ሲገልፁ፣ ሌሎች ደግሞ ‹‹የፈተና ስርዓቱ ኩረጃንና ሌሎች ህገ ወጥ የፈተና ተግባራትን ለማስቀረት ያስቻለ የአፈታተን ስርዓት ነው›› ብለውታል:: የሆነው ሆኖ፣ የፈተና ውጤቱ አስደንጋጭና አስገራሚ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም:: ከአጠቃላይ ተፈታኞች መካከል አራት በመቶ ያህሉ እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ‹‹ሀገር ተረካቢ ነው›› ስለሚባለው ትውልድ በእጅጉ እንድንጨነቅ ያስገድደናል::
የ2014 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና አፈታተን ከዚህ ቀደም ከነበሩት የፈተና ስርዓቶች የተለየ እንደነበር ይታወሳል:: ተፈታኞች ፈተናውን የወሰዱት በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ነበር፤ፈታኝ መምህራንም ፈተናውን እንዲፈትኑ የተደረገው መምህራኑ ያስተምሩባቸው ከነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ ነበር::
ይህ የአፈታተን ስርዓት ኩረጃንና መሰል ህገ ወጥ የፈተና ተግባራትን ለማስቀረት እንደሚያግዝ ሲነገርም ነበር:: የፈተናው ውጤት ሲገለፅ የታየውን እውነት (ከግማሽ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ማነስን) ይዘን ‹‹ይህ ዓይነት ውጤት የተመዘገበው ኩረጃ ስላልነበር ነው›› የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ ስናሰላስል፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት የተመዘገቡት ውጤቶች ካለፈው ዓመት የተሻሉ የሆኑት በኩረጃ ነበር ማለት ነው?›› ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን::
በሌላ በኩል የፈተናውን ውጤት በምን ዓይነት የትምህርት ስርዓት ውስጥ እያለፍን እንደምንገኝ በግልፅ አሳይቷል:: አራት ከመቶ ተፈታኞች እንኳ ከግማሽ በላይ ውጤት አለማስመዝገባቸው ትምህርትን እንዴት እየቀለድንበት እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ነው:: ይህ ደግሞ የሀገር ግንባታ ዋነኛ መሰረት የሆነው አምድና የሀገሪቱ ህልውና እጅግ አስደንጋጭ አደጋ ውስጥ እንደገባ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርትና ስልጠና ሥርዓት ለትምህርት ዘርፍ መሻሻልና የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት አዎንታዊ አስተዋፅዖዎችን እንዳበረከተ ባይካድም፣ ዓይነተ ብዙና ውስብስብ ችግሮችም አሉበት:: የትምህርትና ስልጠና ስርዓቱ በንድፈ ሀሳብ እንጂ የተግባር ክህሎትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ አይደለም። የምዘና ሥርዓቱም ለተግባራዊ እውቀት ትኩረት አልሰጠም። ስራ ፈላጊ እንጂ ስራ ፈጣሪ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም።
የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራው ጎልብቶ ኢኮኖሚውን በሚፈልገው መጠን እያገዘም አይደለም። በዚህ ምክንያት ህብረተሰቡ በትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱ የጥራትና የተገቢነት ጥያቄ እያነሳ ይገኛል። ከትምህርትና ስልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና የስራ ፈጣሪነት አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ ትውልዱ ዲግሪና ዲፕሎማ (ወረቀት) አምላኪ ሆኗል።
ኩረጃና መሰል ህገ ወጥ የትምህርትና ፈተና ተግባራት እየጎለበቱ በመምጣታቸው የትምህርት ስርዓቱ የሀገር ፍቅር፣ የብዝኃነት፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖርና ግብረገብነት እሴቶችን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት በተጨባጭ ማስረፅ ባለመቻሉ ግለኝነት እያየለ፣ የጎሳ ብሄርተኝነት እየገነነ፣ የሀገር ፍቅር እየደበዘዘ መጥቷል። ይህም ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል::
የአንድ ሀገር የትምህርት ስርዓት መበላሸት የሀገሪቱ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደገባ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል:: ሰላም የሰፈነባት፣ ማኅበራዊ መረጋጋት ያለባት፣ ምጣኔ ሀብቷ ያደገና ፖለቲካዊ የሰከነ ሀገር እውን ማድረግ የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ስርዓት በተገነባ ትውልድ ነው:: ጥራት በሌለውና በወደቀ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ያለፈ ትውልድ ለሀገር ህልውና ትልቅ አደጋ ይሆናል::
በስነ ምግባር ያልታነፀና ኩረጃን መሳሪያ ያደረገ ተማሪ የሀገር ሸክምና አደጋ እንጂ የሀገርና የሕዝብ መኩሪያና መመኪያ ሊሆን አይችልም:: ለዚህም ነው ‹‹አንድን ሀገር ለማፍረስ ጦር ማዝመት ሳያስፈልግ፣ የሀገሪቱን የትምህርት ስርዓት ማበላሸት በቂ ነው›› የሚባለውን ሃሳብ በተደጋጋሚ የምንሰማው::
በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብእናቸው የተገነባ ዜጎችን ማፍራት የሚቻለው ጥራት ባለው የትምህርት ስርዓት ነው።
አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው:: የሰው ኃይል መገንቢያው ዋነኛው መሳሪያ ደግሞ ትምህርት ነው:: አስተማማኝና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ብቸኛው መንገድ ጥራት ያለው የትምህርት ስርዓትን መዘርጋት ነው::
ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገው የ2014 ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ውጤት፣ የትምህርት ስርዓቱን ክፍተቶች አሳይቷል:: ውጤቱ የትምህርት ስርዓቱ መውደቅ ለሀገሪቱ ህልውና ትልቅ አደጋ እንደሆነም አመላክቷል:: ስለሆነም ከዚህ ችግር ለመውጣት የሚያስችሉ የመፍትሄ አማራጮችን በፍጥነት መመልከትና መተግበር ያስፈልጋል::
የትምህርት ጥራትን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተማሪዎችን ያማከለ ዘመናዊና አሳታፊ የመማር ማስተማር ሂደት መከተል፤ የመምህራን ጥራትና ተነሳሽነት ማጎልበት፤ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሂደትን መከተል፤ ተማሪዎችን ማነቃቃት፤ ጠንካራ የትምህርት ቤት አመራርን ማብቃት፤ ምቹና ጤናማ የትምህርት አካባቢ መፍጠር፤ የማስተማሪያ ግብዓቶች ማሟላት እንዲሁም የተማሪዎች ስነ ምግባርን ማሳደግ ይገባል።
ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚገባ የመከታተል፤ የመምህራን በጥራት የማስተማር፤ የትምህርት አመራር ስትራቴጂካዊ አመራር የመስጠት እንዲሁም የወላጆች ልጆቻቸውን በንቃት የመከታተልና የመደገፍ ተግባራት በቅንጅት ሊከናወኑ ይገባል።
በትምህርትና ስልጠና በቂ የሰው ኃይል ለማፍራት ባለፉት ዓመታት የትምህርትን ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራትን ለማጎልበት የተሰሩ ሥራዎች ያስገኙትን ውጤት መገምገምም ይገባል::
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲ በሥነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ፣ የሀገሪቱን ዕድገትና አንድነት በሚያስቀጥልና ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን በሚገባ መፈተሽና ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 30 ቀን 2015 ዓ.ም