ውበት ምንድነው? ስለ ውበት ስናስብ በቅጽበት ወደ አዕምሯችን የሚከሰተው ምስልስ ምን ይመስል ይሆን? ስልክክ ያለ አፍንጫ?፣ ጎላጎላ ያሉ አይኖች?፣ ወይንስ እንደ በረዶ የነጡ ጥርሶች ከተንዠረገገ ፀጉር ጋር? በርግጥ በብዙዎች አዕምሮ እና ሥነ ልቦና ውስጥ ውበት የተሳለችው እንደዚህ ነው። ነገር ግን ከዚያ አልፈን የውበትን ዳርቻ እያሰፋን ስንሄድ ደግሞ ውበት እንደ ባህልና እምነት ሆኖ እናገኘዋለን።
በዓለማችን ላይ ውበትን የምንገልጽበት መንገድ በብዛት ተመሳሳይ ቢሆንም፤ በራሳቸው የባህልና ውበት ፍልስፍና ውስጥ የሚኖሩ ጥቂት ጎሳዎች ይገኛሉ። የኛው አገር ሙርሲዎች ለዚህ አንድ ምሳሌ ናቸው። ባህላዊ ቁሶችንና አልባሳትን የሚጠቀሙት ቱባ ባህሎች በየዘመናቱ የሥልጣኔ አብዮት እየገረሰሳቸው አሁን ከተረፉት በጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ጎሳዎች መሃል ሙርሲዎች ተጠቃሽ ናቸው። ሙርሲዎች ምናልባትም እርቃናቸውን ለመሸፈን ያህል ከወገባቸው ላይ እራፊ ጨርቅ ጣል አድርገው ያለመተፋፈር ሲሄዱ፣ ከዘመናዊው ዓለም መዘውር ውጭ የሆኑ መስሎ ይሰማን ይሆናል። እውነታው ግን ይህ አይደለም፣ ከዚህም ከዚያም የተለየ ነው። እነርሱ በውበት አድማስና ደሴት የሚኖሩ የተለዩ ናቸው።
በሰውነታችን ላይ አንዲት ቁስል እንዳታርፍ በዘመናዊ ኬሚካሎች ቆዳችንን በምንፈትግበት በዚህ አርቴፊሻል ዘመን እነርሱ ግን ከንፈሮቻቸውን ተልትለው ሸክላ ያንጠለጥሉበታል፤ ጆሮዎቻችንን በስተን ወርቃማ አሊያም ብራማ ጉትቻ በምናንጠለጥልበት በዚህ የብልጭልጭ ዓለም፣ እነርሱ ግን ጆሮዎቻቸውን እስከ ትከሻቸው ዘርጥጠው ክብ ሸክላ ይወጥሩበታል። ይህንንም ስናይ ኋላ ቀር እብደት እያበዱ እንደሆነ ከማሰባችን በተጨማሪ በነገሩ ስቅቅ ልንልም እንችላለን። እነርሱ ግን ደስታና እርካታ የሚያገኙት በዚህ ነው።
የሙርሲዎች ልዩ የባህል ውበት መገለጫ ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ የሴቶች የከንፈር ላይ የሚንጠለጠል ሸክላ ነው። አንዲት የሙርሲ ሴት ይህን የከንፈር ላይ ሸክላ ስታንጠለጥል የራሱ የሆነ ምክንያትና ትርጉም አለው። በሙርሲዎች ባህል አንዲት ሴት እድሜዋ ወደ 16 ሲጠጋና ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ ከንፈሯን የመተልተልና ሸክላ የማንጠልጠል ሥርዓት ታከናውናለች። በአብዛኛው ይህን ሃላፊነት የምትወስደው የልጅቷ እናት ስትሆን የሚተለተለው ከንፈር የሚለጠጥበት ስፋት የሚወሰነው ግን በልጅቷ ፍላጎት ነው፡፡
በዚህ መልኩም ሂደቱ ይጀመራል። በመጀመሪያ ከንፈሯን የማለስለስና የመለጠጥ ስራ ይሰራል። ልጅቷ የምትፈልገው የከንፈር መጠን ላይ እስኪደርስም እለት እለት በተለያዩ ዜዴዎች እንዲሰፋ ይደረጋል። ከዚህ በኋላ የልጅቷ የፊት ጥርስ ይነቀላል። ምክንያቱ ደግሞ ጥርሷ ለሸክላው ምቾትን እንዳይነሳው ሲባል ነው። በመቀጠልም በክብ ቅርጽ የተሰራ ሸክላ ይዘጋጃል።
በአብዛኛው ሸክላው የሚዘጋጀው ከእንጨት እና ከአፈር ነው። የከንፈሯ ቅርጽና መጠን በሚፈለገው ልክ ሲሆን ልጅቷ የሙርሲ ቆንጆ ስለመሆኗ ምልክት የሆነውን ክብ ሸክላ በከንፈሯ ላይ እንዲንጠለጠል ይደረጋል። ይህንን ሁሉ ሂደት አልፋ ሸክላውን ለማንጠልጠል በርካታ ወራትን ሊፈጅባትም ይችላል።
ይህ የሙርሲ ሴቶች በከንፈራቸው ላይ የሚያንጠለጥሉት ክብ ሸክላ ከውበት መገለጫነት አልፎ በርካታ ትርጉሞች አሉት። ለምሳሌ ሴቶቹ ካገቡ በኋላ ለባሎቻቸው ምግብ በሚያቀርቡበት ሰዓት ይህንን ሸክላ በከንፈራቸው ላይ በማንጠልጠል ነው፤ ትርጉሙ ደግሞ ለባሏ ትልቅ ፍቅርና ክብር ከሙሉ ቁርጠኝነት ጋር እንዳላት ያንጸባርቃል።
ሴቷ ድንገት ባሏ በሞት የተለያት እንደሆን የዚህች ሴት ውጫዊ ውበቷ ከባሏ ጋር አብሮ ወደመቃብር ወርዷል ተብሎ ይታመናል። ውበቷም ረግፏል ተብሎ ስለሚታሰብ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሸክላውን ማድረግ ታቆማለች። ከዚህ ውጭ ግን በገበያም ሆነ በየትኛውም ስፍራ በምትንቀሳቀስበት ሁሉ አድርጋው ትሄዳለች። ምናልባት ይሄን የማታደርግ ሴት የሙርሲ ጎሳ አባል እንዳልሆነች ተደርጋ ልትቆጠርም ትችላለች።
ሌላው የሙርሲ ሴቶች የከንፈር ላይ ሸክላ አስገራሚው ነገር፤ የሸክላው መጠን በጨመረ ቁጥር የልጅቷ ተፈላጊነትም የሚጨምር መሆኑ ነው። ወንዱ በሚያገባት ሰዓት ለቤተሰቦቿ የሚሰጠውን የከብት ጥሎሽ በዚያው መጠን ከፍ ያደርገዋል። እሷም ለቤተሰቦቿ የሀብትና የክብር ምንጭ ትሆናለች። ትልቅ ሸክላ ያደረገችን ሴት ቤተሰቦቿ ብቻ ሳይሆኑ ማህበረሰቡም እንደ እንቁላል ይንከባከባታል። ይህን ግርማ ሞገስና የበላይነትን ለማግኘትም እርስ በእርሳቸው ይፎካከራሉ።
በፈረንጆቹ 2014ዓ.ም አብርሃም ጆፍ የተባለ አውስትራሊያዊ የፊልም ሰሪ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ካነሳቸው ፎቶግራፎች መሃከል አንድ ለየት ያለ ፎቶግራፍ በማህበራዊ ሚዲያዎች አሰራጨ። በዚህ ፎቶ ግራፍ ላይ የነበረችው አጣዬ ኢሊጊዳኜ የተባለች ሴት ስትሆን በከንፈሯ ላይ ትልቅ ሸክላ አንጠልጥላ ትታያለች። ሸክላው 15.9 ሴ.ሜ ሲሆን በክብረ ወሰን ተይዞላት ነበር።
ታዲያ በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ አልፋ የመጣችን የሙርሲን ሴት ማንኛውም ወንድ ዝም ብሎ አያገባትም። ወንዱም ሌላ ፈተና ይጠብቀዋል። የሙርሲ ወንዶች ወንድነታቸውን የሚያስመሰክሩት በዶንጋ ሥርዓት ወይንም በዱላ ፍልሚያ ሲሆን ውበታቸውን የሚገልጹት ደግሞ ከፊታቸው ላይ ነጭ ቀለም በመቀባት ነው። ያቺን ቆንጆ ሴት ለማግባትም ወንዱ እነዚህን ሁለት ነገሮች ከሌሎች በተሻለ መንገድ መከወን ይኖርበታል። ፈተና፣
እምነት፣ ጽናት በመጨረሻም አሸናፊነት የሙርሲዎች መለያ ነው። ያልተበረዘና ያልተመረዘ ንጹህ ባህላቸውን ውበትና ጌጣቸው አድርገውት ዓለምን ሁሉ አጃኢብ አሰኝተውታል። ለዚህም ማሳያ ብዙ ብሮችን እየቀፈቀፉ ወደ አገራችን የሚፈሱት ቱሪስቶች የሙርሲዎችን መንደር ሳይጎበኙ አይሄዱም። በሚያዩት ነገር ሁሉም ሳይገረሙና ሳያደንቁ አያልፉም።
እዚያ መንደር ላይ እውነተኛ ውበት ስለመኖሩም ይመሰክራሉ። እኛስ? እንዴት ይሆን የምንቀበለው፣ አሁንም ውበት ማለት ጥቁር ሀር መሳይ ጸጉር፣ ሰልካካ አፍንጫ፣ ተረከዘ ሎሚ ብቻ ነው፤ እያልን ከገደብነው አንበሳ ለምን ስጋ ብቻ ይበላል የሚል ጥያቄ እንደማንሳት ይሆንብናል። ተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ውስጥ ያደረ፣ የሚታይ ነገር ግን እኛ የማንረዳው ልዩ ምርጫ መኖሩን መዘንጋት የለብንም። የሙርሲዎች ውበት የእነርሱ ብቻ ሳይሆን የኛም ጭምር መሆን በመቻሉ ባንከተለውም ልናደንቅና ልንጠብቅ የግድ ይለናል።
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም