ኢትዮጵያ በዓለም የስፖርት መድረኮች ለረጅም ዘመናት ውጤታማነትን ያጎናፀፋት የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ለዚህ ደግሞ በየዘመኑ በትውልድ ቅብብሎሽ ብቅ የሚሉ የብርቅየ አትሌቶች የማይነጥፍ ድል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ከእንቁዎቹ አትሌቶች ጀርባም ያልተዘመረላቸው አያሌ አሰልጣኞች የታሪካዊ ድሎች ዋና ተዋናይ በመሆን ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ ተፈሪና ስመገናና እንድትሆን አስችለዋል።
አትሌቶችን ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‹‹ዜሮ ቱ ሂሮ›› ከምንም ተነስተው ወደ ጀግንነት እንዲሸጋገሩ የኋላ ደጀን የሆኑ አሰልጣኞች የሥራቸውን ያህል ክብርና እውቅና ሲያገኙ አይታይም። ለዚህ በዘመናችን በተለይም በተወዳጁ ማራቶን የአትሌቲክስ አብሪ ኮኮቦች ፈጣሪ አንዱ የሆነው አሰልጣኝ ሐጂ አዲሎ አንዱ ማሳያ ነው።
አሰልጣኝ ሐጂ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በመምራት በበርካታ የዓለም መድረኮች መገኘት ችሏል። ሰውየው በኢትዮጵያ ካሉት ጥቂት የማራቶን ውጤታማ አሰልጣኞች አንዱ ነው። በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ በማራቶን የሚሳተፉ አትሌቶች ውጤታማ ለመሆን አብሮ ለመሥራት የሚመኙት ሰው ነው። ከፍተኛ ስምና ዝና አላቸው የሚባሉት አትሌቶች እንኳን የሱን ቡድን መቀላቀልና መሥራት የተሻለ እንደሚያደርጋቸው ያምናሉ።
ታላቋ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ፊቷን ወደ ማራቶን ካዞረች ጀምሮ ከዚህ ውጤታማ ሰው ጋር መሥራት ጀምራለች። ከሷ በተጨማሪ ሌሊሳ ዴሲሳ፣ ፈይሳ ሌሊሳ፣ ማሬ ዲባባ፣ መሐመድ አማን፣ ሰለሞን ባረጋ፣ ሰንበሬ ተፈሪና ሳሙኤል ተፈራ በእሱ አሰልጣኝነት ስር ከሠሩት ታዋቂ ከዋክብት ተጠቃሽ ናቸው። ከኢትዮጵያውያን ውጭ ኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌና ኤርትራዊው አትሌት ዘረሰናይ ታደሰም አብሮ ከሰሩት ስመ ጥር ከዋክብት መካከል ናቸው።
ሐጂ አዲሎ ወደ አትሌቲክሱ አሰልጣኝነት ሙያ ከገባ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ሆኖታል። የተወለደው የብዙዎች ኢትዮጵያውያን ብርቅዬ አትሌቶች መፍለቂያ አርሲ ነው። ተማሪ በነበረበት ወቅት አትሌት ሆኖ ቢጀምርም ጉዳት በጊዜ ከአትሌትነት እንዲርቅ አስገድዶታል። የጉዳቱ መጠን ከፍተኛ በመሆኑ እአአ በ2000 እራሱን ከአትሌትነት ሊያገል ችሏል። ወደ አሰልጣኝነቱ እንዲገባ በአንድ ፈረንሳያዊ ሰው ምክር እንደተሰጠውና በሱ ምክንያት አዲስ ነገር ማለም እንደ ጀመረ ያወሳል። “ሰውየው ለአትሌቶች ማናጀር ሆኜ እንድሠራ አስቦ ነገረኝ፤ እኔ እንደ አትሌት የኔ ትውልድ ምንያክል ውድድሮችን አጥቶ እስከ ባሕር ማዶ እንደሚታገል እረዳ ስለነበር የመሥራት ፍላጎቱ ነበረኝ“ ይላል ሐጂ የአሰልጣኝነት ሕይወት ጅማሬውን ሲያስታውስ።
ፈረንሳዊው ሰውዬ ሐጂን አምስት አትሌቶችን እሱ ከሃገር ውጭ በሚያዘጋጀው ውድድር መርጦ እንዲወዳደሩ ጠየቀው፣ የመረጣቸው አትሌቶችም ውጤታማ መሆን ቻሉ። ይህም አዲሱን የአትሌቶች አሰልጣኝነት ሕይወቱን አንድ ብሎ የጀመረበት አጋጣሚ እንደነበር ሐጂ ያስታውሳል።
ሐጂ በአትሌትነት ዘመኑ ከጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር በትምህርት ቤት እያለ በመፎካከሩ ዛሬ ላይ ኩራት እንደሚሰማው ይናገራል። “ረጅም ጊዜ አሰልጥኛለሁ፤ በጣም ደስተኛ ነኝ የሚያዝናናኝ ነገር ነው። ይሄ ሕይወቴ ነው እኔ የማሰለጥናቸው አትሌቶች በተለያዩ ውድድሮች ጥሩ ሲሠሩና ሲያሸንፉ ስመለከት እደሰታለሁ” ሲል አሰልጣኝ ሐጂ አዲሎ ይናገራል። የስፖርቱ ስጋት የሆነው የአበረታች ንጥረነገር ተጠቃሚነት(ዶፒንግ) ጉዳይ አንዱ ፈተናው መሆኑንም ሐጂ አልሸሸገም።
“የብቃት ማሳደጊያ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ አትሌቶችን መሞገት እወዳለሁ ምክንያቱም ስፖርቱን ይጎዳሉ። እኛ ለመሮጥ ንጹሕና ጤናማ ስፖርትን እንጠቀማለን ነገርግን በየወሩ የሚታገዱትን አትሌቶች ስሰማ በጣም ያሳዝነኛልም” ሲል ይገልጻል።
አሰልጣኝ ሐጂ ውጤታማ እንዲሆን ካደረጉት ነገሮች መካከል የልምምድና የሥልጠና ማገባደጃ ላይ ስብሰባዎችን በማድረግ አትሌቶቹ ስለሥልጠና ፍላጎታቸው ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ በመጋበዝ እንዲደመጥ ማድረጉ እንደሆነ ይነገራል። “እኔ እንደማስበው በኔ አመራር ስር ብዙዎቹ አትሌቶች ውጤታማ ናቸው፣ ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ በፋይናንስ ሥራ ላይ ምክርና የራሴን የአትሌቲክስ የግል ተሞክሮ አካፍላቸዋለውም” ሲል በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየቱን ይሰጣል።
አሰልጣኝ ሐጂ አዲሎ በአሁን ወቅት ሥራው ከራሱ በላይ የሚያወራለት ሰው መሆን ችሏል። ባለፉት አስርተ ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ሙያ የማራቶን ሥልጠናን በበላይነት በመቆጣጠር እየመራ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት የአዋቂ ስፖርት ስልጠናን ጨምሮ የዓለም አቀፍ ስፖርት ተቋማትን ስልጠና በበላይነት ይመራል። ተቋማቱ ከ100 በላይ የመምና የሜዳ ተግባራት አትሌቶችን ከኢትዮጵያና ከጎረቤት ሃገራት አቅፈው የሚይዙ ናቸው። ተቋሙ ለቁንጮ አትሌቶች ከሃገር ውጪ ውድድሮችን በማዘጋጀት የፉክክር እድሎችን ያመቻቻሉ። ሐጂ እነዚህን አትሌቶች በማዘጋጀት በመጨረሻ አትሌቶቹ ከሚያገኙት ሽልማት አምስት በመቶ ያህሉን ብቻ የልፋቱን ዋጋ ያገኛል። ናይኪ ማራቶንን ከሁለት ሰዓት በታች ለመጨረስ በያዘው ፕሮጀክት አሰልጣኝ ሆኖ ሠርቷል። በሙያው ውስጥ ካሳካቸውና ከምን ጊዜውም በላይ ከሚኮራባቸው ነገሮች መካከልም ይህ አንዱ እንደሆኑ ይናገራል።
የሐጂ በአሰልጣኝነት ውጤታማ መሆን የውጭ አገራት ቁንጮ አትሌቶችን ልብ ሳይቀር እንዲገዛ አስችሎታል። ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ከቻይና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአሰልጥንልን ጥያቄ መጥቶለትም የቻይናን አትሌቶች ለኦሊምፒክ ማዘጋጀት ችሏል። ከራሱ ሃገር በተቃራኒ የሚወዳደሩ አትሌቶችን ማሰልጠን እንደማያስጨንቀው ግን ሐጂ ደብቆ አያውቅም። “ብዙ ተፎካካሪዎች መኖራቸው እኛን አያደክመንም። ይልቁንም ጥሩ እንድንሠራ ያነሳሳናል። እኛ በምንወደው ሙያችን ብዙ ተፎካካሪዎች መኖራቸው ለኛ ትልቅ እድል ነው። እንደ 10ሺ እና 5ሺ ሜትር ያሉ ውድድሮች ከሌሎች ሃገሮች የበለጠ ተፎካካሪዎችን ሲመለከቱ በመም ሊቆዩ ይችላሉ ”ሲልም ያክላል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም