በብዙ የጠቅላላ ዕውቀት የጥያቄና መልስ ውድድሮች ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ማን ናት?›› ተብሎ ሲጠየቅ እንሰማለን። የሴቶችን ተሳትፎ ታሪክ በሚዘክሩ መድረኮችና የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ስሟ ይነሳል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሳሁን።
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ከ51 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈውን ጋዜጠኛ ሮማነወርቅ ካሳሁንን እናስታውሳለን። የጋዜጠኛ ፍፁም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› መጽሐፍ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና የተለያዩ ድረ ገጾችን በዋቢነት ተጠቅመናል።
ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ተውኔት ሮማነወርቅ ካሳሁን ከአባታቸው ከአቶ ካሣሁን እንግዳሸት እና ከእናታቸው ከወይዘሮ አለሙሽ ዓለም በ1914 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም ቅድሥት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በመማር ዳዊት ደገሙ። ከዚያም ስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት በመግባት በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ዘመናዊ ትምህርት ተማሩ። በትምህርት ቤት ቆይታቸውም የወቅቱን ‹‹ሴት ለትምህርት አልተፃፈችም›› የሚለውን ልማድ በጥረታቸውና በትጋታቸው በመቋቋም በትምህርት ቤት ቆይታቸው የአንደኛነት ደረጃን በመያዝ በአውሮፓውያን አስተማሪዎቻቸው ይሸለሙ ነበር።
በወቅቱ በነበረው ልማድም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ትዳር ይዘው የአንዲት ሴት ልጅ እናት ሆነዋል።
ሮማነወርቅ በስዊድን ሚሲዮን ትምህርት ቤት ይማሩ በነበረበት ወቅት ከአውሮፓውያን መምህራን ያገኙት ዘመናዊ ትምህርት ከተፈጥሮ ችሎታቸው ጋር ተደምሮ በጥናትና ንባብ ያዳበሩትን እውቀታቸውን ወደ አደባባይ ማውጣት ስለፈለጉ በጥር ወር 1939 ዓ.ም በወቅቱ ‹‹የማስታወቂያና ፕሮፖጋንዳ ሚኒስቴር›› ተብሎ ይጠራ በነበረው መሥሪያ ቤት የመጀመሪያዋ ሴት ጋዜጠኛ በመሆን ተቀጠሩ።
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በተሰጣቸው በሬዲዮ ጋዜጠኝነት ሥራቸው የተለያዩ ጽሑፎችንና ዜናዎችን በማዘጋጀት በማራኪ አንደበታቸው ሲያንቆረቁሩት በዜና አቀራረባቸውና በፕሮግራም ዝግጅታቸው በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትንና አድናቆትን ለማግኘት ብዙም ጊዜ አልወሰደባቸውም ነበር።
በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ባገለገሉባቸው ጊዜያት በሬዲዮ ዜና አጠናቃሪነት፣ በዜና አንባቢነት፣ በሴቶች ፕሮግራም አዘጋጅነት ሠርተዋል። በወቅቱም ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው በዝግጅቶቻቸው ላይ የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ሥራዎችን በማቅረብ ሕዝቡን ሲያገለግሉ በትምህርት ገበታ ላይ ለነበሩት ሴቶች ልጆች እንደብርቅዬና የበጎ ተግባር ምሳሌ በመሆን ይታዩ ነበር። በዝግጅቶቻቸው የተለያዩ ወቅታዊ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት በወቅቱ በሴቶች ዘንድ ጫና የሚፈጥሩ አመለካከቶችን ለመፋቅ በመገናኛ ብዙኃን የራሳቸውንና የብዙ ሴቶችን ድምፅ አሰምተዋል።
የሴቶች ማኅበራዊ ሕይወት መሻሻል ላይ የሚያተኩሩ ጽሑፎችንም ይጽፉ ነበር። ከሥራዎቻቸው መካከል የበኩር ስራቸው የተጠናቀቀው በ1940 ዓ.ም ቢሆንም መጽሐፋቸውን ይዘው ወደ ሕትመት የሄዱት ግን ከሁለት ዓመታት በኋላ፣ በ1942 ዓ.ም ነበር። ይህንን ጉዳይ አስመልክተውም በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ በማለት ስለሕትመቱ ጉዳይ በትሕትና ገልፀዋል።
‹‹ … መጽሐፌን ጽፌ የጨረስኩት በ1940 ዓ.ም ነበር። ከዚያ ወዲህ ሁለት ዓመታት ቆይቼ ሳነበው ከእርሱ የተሻለ ለመፃፍ የምችል ሆኖ ተሰማኝ። በዚህ ምክንያት ተሳንፌ ማሳተሙን ለማቆየት ከቆረጥሁ በኋላ የሰው እውቀት የእድሜ ደረጃን ተከትሎ የሚሄድ እንጂ በአንድ ጊዜ አዋቂ አለመሆንን በማሰብ ዛሬ የተሻለ መስሎኝ ብሠራም ነገ መናቄ እንደማይቀር ተረዳሁት። ይህም የሰው አዕምሮ ያለማቋረጥ የሚሻሻል ለመሆኑ ዋና ማስረጃ ነው በማለት ይህን ሁሉ ካወጣሁና ካወረድሁ በኋላ ማመንታትን ትቼ አሳተምሁት። … ››
የመጀመሪያ ሥራቸውን ለአንባቢ ያቀረቡት ወይዘሮ ሮማነወርቅ ለመጽሐፋቸው የመረጡት ርዕስ ‹‹ትዳር በዘዴ›› የሚል ነበር። መጽሐፉ የገጠሩንና የከተማውን ትዳርና ኑሮ የሚያነፃፅር ሲሆን በውስጡም በገጠር ያለውን የሕይወት ውጣ ውረድ ዘርዝሮ ያቀርባል። ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉ ደራሲ ‹‹ለትዳር ፈላጊዎች ምክር አለኝ›› በማለት ስለትዳር የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። ሴቶች በማኅበራዊ ሕይወታቸው ውስጥ ያለባቸው ጫናም በመጽሐፉ ተዳስሷል። ከዚያ በኋላም በርካታ ጋዜጣ መጣጥፎችንና መጻሕፍትን ጽፈዋል። በሥራዎቻቸውም በርካታ ሽልማቶችን አግኝተዋል።
ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ፀሐፊ ትውኔት ሮማነወርቅ የጤና እክል አጋጥሟቸው በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ጥር 23 ቀን 1964 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግስቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሹማምንትና ሠራተኞች እንዲሁም እጅግ በርካታ ሕዝብ በተገኘበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በቀጨኔ መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
ጋዜጠኛዋ ሞት ቀደማቸው እንጂ ‹‹ሔዋን››፣ ‹‹መልካም እመቤት››፣ ‹‹የቤተሰብ አቋም››፣ ‹‹የባልትና ትምህርት››፣ ‹‹የሕፃናት ይዞታ››፣ ‹‹ዘመናዊ ኑሮ››፣ ‹‹የኑሮ መስታዎት››፣ ‹‹ጋብቻና ወጣቶች››፣ እና ‹‹የባልና የሚስት ጠብ›› በሚሉ ርዕሶች መጻሕፍትን አዘጋጅተው ለሕትመት ለማብቃት እየጠበቁ እንደነበር ታሪካቸው ያሳያል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም