በአገሪቱ ተጠናክሮ በቀጠለው ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ›› ጉልህ ድርሻ ካላቸው ተዋንያን መካከል አምራች ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሾች ናቸው። ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ለሚለው ንቅናቄ የጀርባ አጥንት የሆኑት እነዚሁ አምራች ኢንዱስትሪዎችም በጥራት በማምረት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ይታመናል። በተለይም ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ በማምረት አገሪቷ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማቃለል ከተጣለባቸው ኃላፊነቶች አንዱና ዋነኛው ነው።
መንግሥት ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› በሚለው ንቅናቄ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፤ በጥራትና በብዛት ለማምረትና ከአገር ውስጥ ገበያ ባለፈ በውጭ ገበያ ጭምር ተወዳዳሪ መሆንን በማሰብ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። ይህን ሀገራዊ ተልዕኮ ዕውን በማድረግ ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን እየተወጡ ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከልም በአዳማ ከተማ የሚገኘው ‹‹ሎዛ ጋርመንት›› አንዱ ነው። በዛሬው የ‹‹ስኬት›› አምዳችን የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴን እንቃኛለን።
የተለያዩ አልባሳትን በማምረት ለገበያ እያቀረበ የሚገኘው ‹‹ሎዛ ጋርመንት››፣ በአሁን ወቅት መንግሥት አጠናክሮ የቀጠለውን ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄን ለማሳካት በብዙ እየተጋ ያለ ድርጅት ነው። የድርጅቱ መስራችና ባለቤት አቶ ብሩኬ ጥላሁን ሎዛ ጋርመንትን ለዛሬ ከማድረሱ አስቀድሞ የስፌት ሥራን ከወላጅ አባቱና ከታላቅ ወንድሙ እግር በእግር ተከታትሎ ተምሯል።
በስፌት ሥራ ከተሰማሩ ወላጅ አባትና የግብርና ሥራ ከሚሠሩ እናት የተገኘው የሎዛ ጋርመንት መሥራችና ባለቤት አቶ ብሩኬ ጥላሁን፣ እትብቱ ከተቀበረበት ምንጃር ሸንኮራ ወልቃ ጅሎ አሞራ ቤት ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ተነስቶ ዛሬ ላይ ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። የልብስ ስፌት ሥራን ከወላጅ አባቱ ተረክቦ ለአቶ ብሩኬ ያቀበለው ታላቅ ወንድሙ ቢሆንም ቅሉ አቶ ብሩኬ ለስፌት ሥራ ከፍተኛ የሆነ ውስጣዊ መሻት እንደነበረው ያስታውሳል።
ፍላጎትና ጥረት ካለ ማንኛውም ነገር ከትንሽ ወደ ትልቅ ማደግ እንደሚችል የሚያምነው አቶ ብሩኬ፤ ቁልፍ የመትከል፣ የመተኮስ፣ የመዘምዘምና ሌሎች ሥራዎችንም በመሥራት ሂደት ውስጥ የስፌት ዕውቀትን መቅሰም ችሏል። ከትምህርት ቤት መልስ በስፌት ሥራ የተሠማሩ ወላጅ አባቱን እንዲሁም ታላቅ ወንድሙን ከውስጥ በመነጨ ጥልቅ ፍላጎት ያግዝ ነበር። በመሆኑም የውስጥ መሻቱ የነበረውን የስፌት ሥራ በቀላሉ መቀላቀል ችሏል። ለስፌት ሥራው ካለው ጥልቅ ፍላጎት የተነሳም በአንድ ወቅት ታላቅ ወንድሙ ቆርጦ ያዘጋጀውን ልብስ ለመስፋት ባደረገው ሙከራ ልብሱን እንዳበላሸና የደረሰበትን ቁጣ የማይረሳው መሆኑን አጫውቶናል።
‹‹የሚሠራ ሰው ይሳሳታል›› እንደሚባለው አቶ ብሩኬ ሲሠራ ተሳስቶ፤ ሲያጠፋ ታርሞ እራሱን በማብቃት ዛሬ የራሱ ድርጅት የሆነውን ‹‹ሎዛ ጋርመንት››ን ማቋቋም ችሏል። በጋርመንት ሥራውም የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ የሴት፣ የወንድና የሕጻናት አልባሳትን በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ከአልባሳት በተጨማሪም የቆዳ ውጤት የሆኑ የተለያዩ የሴት እና የወንድ ቦርሳዎችንም ያመርታል።
ቤተሰቡ በአንድና በሁለት የስፌት መኪና ጥቂት ቁጥር ያላቸውን አልባሳት ያመርት እንደነበር ያነሳው አቶ ብሩኬ፤ ገና በልጅነት ዕድሜው የስፌት ሥራውን የማሳደግና የማስፋፋት ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው መሆኑን ያስታውሳል። ከልጅነት ጀምሮ የነበረው የአምራችነት ፍላጎቱ በውስጡ ሲንቀለቀል የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን ገታ በማድረግ በቤተሰብ ውስጥ ሆኖ በግሉ የስፌት ሥራውን ማሳለጥ ጀመረ።
የስፌት ሥራን ከቤተሰቡ በተለይም ከታላቅ ወንድሙ የወረሰው አቶ ብሩኬ፤ ከቀሰመው የስፌት ሥራ ዕውቀት በተጨማሪ በተፈጥሮው የተመለከተውን ነገር ደግሞ የመሥራት እንዲሁም የፈጠራ ሃሳብና ተሰጥዖም ነበረውና ለሥራው አጋዥ ሆኖለታል። በቤተሰቦቹ እቅፍ ውስጥ ሆኖ ሌባ የማይሰርቀውን የእጅ ሙያ የለመደው አቶ ብሩኬ፤ ሙያውን ገንዘቡ በማድረግ የስፌት ሥራውን ማቀላጠፍ የቻለውም ለዚሁ ነው። የስፌት ሥራውን በተፈጥሮ ከተቸረው የፈጠራ ችሎታ ጋር በማዋሃድ ዛሬ ላይ ደረጃውን የጠበቀ አልባሳትን ማምረት የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆኗል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የስፌት ሥራ የተዋሃደው አቶ ብሩኬ፤ እራሱን ችሎ የግል ሥራውን በጀመረበት ወቅት በወር 30 ብር የስፌት መኪና ከገበሬ ተከራይቶ እንደነበር ያስታውሳል። በወቅቱ ለሥራው ከነበረው ጉጉት የተነሳ ጠንክሮ በመሥራት በአንድ ዓመት ውስጥ 16 ሺ ብር ማትረፍ ችሏል። በወቅቱ አብዛኛው ማኅበረሰብ በተለይም አርሶ አደሩ የሚያዘወትረው ቁምጣ በመሆኑ ወንድሙን ጨምሮ ሌሎች ልብስ ሰፊዎችም በብዛት የሚሰፉት ቁምጣ ነበር። ቁምጣውን የሚሰፉትም ደንበኛው በመጣ ጊዜ ቁመትና ስፋቱን በመለካት እንደነበር ያስታውሳል።
የደንበኞችን መምጣት በመጠባበቅ ልክ ለክቶ የሚሠራው ሥራ ለአቶ ብሩኬ የሚዋጥለት አልሆነም። እናም ሌላ ዘዴ አማተረ፤ ወትሮም የአምራችነት ፍላጎት ይፈታተነው ነበርና በወር 30 ብር ኪራይ በሚከፍልበት በአንዲት የስፌት መኪና ከትዕዛዝ ውጭ ለማምረት አቅዶ በክረምት ወቅት ሲያመርት ሰነበተ። የክረምቱን ብርድና ጭጋግ በመቋቋም እንዲሁም ነገን ተስፋ በማድረግ ከትዕዛዝና ከልኬት ውጭ ከ60 እስከ 70 የሚደርሱ ቁምጣዎችን ሰፍቶ አዘጋጀ። ቁምጣዎቹን ያዘጋጀውም በወርሐ ታኅሣሥና ጥር ወደ ገበያ ይዞ ለመውጣት ቀጠሮ በመያዝ ነው። ወርሐ ታኅሣሥና ጥርን ለገበያ የማጨቱ ምክንያትም ጎተራው የሞላለት ብርቱ አርሶ አደር የዓመት ልብሱን በወርሐ ታኅሣሥ መግዛቱ የተለመደ በመሆኑ ነው።
አርሶ አደሩ ለመሬት አደራ የሰጠውን የዘር ፍሬ በሚሰበስብበትና የድካሙን ዋጋ በሚያገኝበት በወርሐ ታኅሣሥ የዓመት ልብሱን ሲሸምት አቶ ብሩኬ ያመረታቸውን ቁምጣዎች በሙሉ መሸጥ ቻለ። በዚህ ሥራው ከገመተው በላይ 16 ሺ ብር ከወጪ ቀሪ ማትረፍ የቻለው አቶ ብሩኬ፤ ደግሞ ደጋግሞ ለማምረትና ሥራውን ለማስፋት አላቅማማም።
እናም ዘርፉን ይበልጥ የማስፋትና የማሳደግ ሕልሙን በውስጡ እንደሸሸገ 16 ሺ ብሩን ይዞ ወደ መተሐራ ከተማ አቀና። ወደ ከተማ በቀረበ መጠን ሥራውን የማስፋፋት ዕድል የገጠመው አቶ ብሩኬ፤ እራሱን በዕውቀትና ልምድ ይበልጥ ማሳደግ ችሏል። ዘርፉን በጥልቀት ባወቀው ቁጥር ወደ አምራችነት የሚወስደውን መንገድ አመቻችቶለታል። የተሻለ ፍላጎት ወዳለበት ከተማ ተንቀሳቅሶ መሥራት ያለበት መሆኑን በማመንም መተሐራ ከተማ ጥቂት ከሠራ በኋላ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ወደ አዳማ ከተማ በማቅናት የጋርመንት ሥራውን ቀጥሏል።
አዳማ ከተማ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት ስለመኖሩ የተረዳው አቶ ብሩኬ፤ ወደ ከተማዋ ለመምጣት ሲያስብ አስፈላጊ የተባሉ የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን በማከናወንና በስፋት ለማምረት ራሱን ዝግጁ በማድረግ ነበር። ለአብነትም አምስት የተለያየ ተግባር ያላቸው የስፌት ማሽኖችን፣ ኦቨርሎክና ሌሎች ማሽኖችንም በማሟላት ወደ አዳማ ከተማ ገብቷል። በወቅቱ ወጣቶች የተለያየ ምርቶችን ለማምረት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱበት ወቅት በመሆኑ አቶ ብሩኬም እንደሌሎች ነዋሪዎች ሁሉ ተደራጅቶ የማምረቻ ቦታ ማግኘት ችሏል።
የዕውቀት፣ የክህሎት እና የመሥሪያ ማሽኖች ችግር ያልነበረበት አቶ ብሩኬ፤ ከመንግሥት ባገኘው 198 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የማምረቻ ቦታን ተረክቦ በቀላሉ ወደ ሥራው ለመግባት አላዳገተውም፤ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ባካበተው ልምድ አዳማ ከተማ ላይ ‹‹ሎዛ ጋርመንት››ን ማቋቋም የቻለውም በዚሁ መነሻ ነው። ከወላጅ አባቱና ከታላቅ ወንድሙ ጋር ሆኖ ሲዘመዝም፣ ሲተኩስና ቁልፍ ሲተክል ያደገው አቶ ብሩኬ፤ እራሱን የሚያወዳድረው ከውጭ አገር ከሚገቡ አልባሳት ጋር እንጂ በሀገር ውስጥ ከሚመረቱት ምርቶች ጋር እንዳልሆነ ነው የሚናገረው።
ከውጭ የሚገቡ አልባሳት ለምን በሀገር ውስጥ መመረት አይችሉም የሚል ጥያቄ የነበረው መሆኑን በማንሳትም ሁልጊዜ ከቻይና ከሚገቡ ምርቶች ጋር አወዳድሮ ለማምረት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። የሚያመርታቸውን ምርቶች እራሱ ዲዛይን የሚያደርግ ሲሆን፤ በዋናነት የወንድ ሸሚዞች፣ ቲሸርቶች፣ የሴቶች ቦዲ፣ ቀሚስ፣ ጉርዶችና የሴቶች ታይት ያመርታል። ከአልባሳት በተጨማሪም የወንድና የሴት የቆዳ ቦርሳዎችን በጥራትና በስፋት በማምረት ለገበያ ያቀርባል። ገበያው የሚፈልገውን በማጥናት የተለያዩ ምርቶችን አምርቶ ወደ ገበያ የማውጣት ፍላጎት ያለው መሆኑንም አጫውቶናል።
ድርጅቱ አጠቃላይ የስፌት ሥራዎችን የሚሠራ ሲሆን፤ከመደበኛ አልባሳት በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት ዩኒፎርም፣ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የጥበቃ ዩኒፎርሞችና ሌሎችንም ያመርታሉ። ወደ ‹‹ሎዛ ጋርመንት›› ለሥራ የሚመጡ ሠራተኞችን አስመልክቶም ሲናገር ‹‹ሁለት ዓይነት ናቸው። ልምድ ኖሯቸው በቀጥታ ወደ ስፌት ሥራው የሚገቡና ምንም ዓይነት ልምድ ሳይኖራቸው ነገር ግን ድርጅቱ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ ባለሙያ የሚሆኑ ናቸው›› ይላል። ለዚህም ምንም ዓይነት ዕውቀት ሳይኖራቸው ድርጅቱን የተቀላቀሉና ከቅንጨባና ከዝምዝም ተነስተው የስፌት ባለሙያ መሆን የቻሉና ድርጅቱን መምራት የሚችሉ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ሲናገር በልበ ሙሉነትና በኩራት ነው።
የማምረቻ ቦታን ብቻ ከመንግሥት አግኝቶ የተለያዩ አልባሳትን እና የቆዳ ውጤቶችን እያመረተ የሚገኘው ‹‹ሎዛ ጋርመንት›› በአሁኑ ወቅት 12 የስፌት ማሽኖች ያሉት ሲሆን፣ 15 ለሚደርሱ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። ድርጅቱ አሁን ባለው አቅም በቀን 100 ሸሚዞችንና እስከ 200 ቲሸርቶችን እያመረተ ይገኛል።
የገበያ መዳረሻቸውን አስመልክቶም በሀገር አቀፍ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ምርቶቻቸውን እየሸጡ መሆኑን የተናገረው አቶ ብሩኬ፤ ለአብነትም ደብረብርሃን፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴ፣ ጅማ፣ ባሌ ሮቤ፣ ዶዶላና በሌሎች ከተሞች ጭምር ምርቶቹ ሀገር አቀፍ በሆነ ባዛር ሁሉ ተደራሽ እየሆኑ ነው። የ‹‹ሎዛ ጋርመንት›› ምርቶች መደበኛ በሆነው ገበያ አዳማ ከተማን ጨምሮ በኦሮሚያ ክልል በስፋት ተደራሽና ተመራጭ መሆን ችለዋል።
ማኅበረሰቡ ለአገር ውስጥ ምርት ያለው አመለካከት ዝቅተኛ የነበረ መሆኑን በማስታወስ፤ ነገር ግን አሁን ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየታየ መሆኑን ያነሳው አቶ ብሩኬ፤ እሱም በድርጅቱ ውስጥ የሚያመርታቸው ምርቶች ደረጃቸውን የጠበቁና ከቻይና ከሚገቡ ምርቶች ጋር ተወዳዳሪ እንደሆኑ ነው የተናገረው። በቀጣይም የተሻለ ጥራት ጨምሮ በማምረት ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ መተካት የሚቻል እንደሆነ ያለውን እምነት ገልጿል። በተለይም ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› የሚለውን ራዕይ ለማሳካት በጥራትና በስፋት ማምረት የግድ በመሆኑ ለዚያም ዝግጁ እንደሆነ ነው የተናገረው።
ሌባ የማይሰርቀውን የእጅ ሙያ በቤቱ ውስጥ ከልጅነቱ የተማረው አቶ ብሩኬ፤ በተናጠል ከመስፋት አልፎ ዝቅተኛ በሆነ መነሻ ካፒታል ነገር ግን ከፍተኛ በሆነ ውስጣዊ ፍላጎት በስፋት ወደ ማምረቱ የገባ ሲሆን በአሁን ወቅትም ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ካፒታል መድረስ ችሏል።
‹‹በውስን ሃብት ዕውቀትን መፍጠር፤ ያገኘነውን ዕውቀት ደግሞ ወደ ገንዘብ መቀየር›› የሚለውን የካይዘን ፍልስፍና የተጠቀመበት መሆኑን ያነሳው አቶ ብሩኬ፤ በዘርፉ የተዘጋጁ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መሰልጠን እንዲቻል ለሚያደርጉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ትልቅ ምስጋና በማቅረብ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማሳደግ እያደረገ ባለው ከፍተኛ ጥረት ትርጉም ያለው ውጤት እየተመዘገበ እንደሆነም አስረድቷል። ወጣቶችም ይህን ዕድል ተጠቅመው ውጤታማ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ብሏል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም