ከ20 ዓመት በታች እድሜ ላይ የሚገኙ አትሌቶች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም በፉክክሮችና የእድሜ ተገቢነት ውዝግቦች ታጅቦ ነገ ይጠናቀቃል። ለአስራ አንደኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው ቻምፒዮና ዛሬ አምስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ባለፉት አራት ቀናት በርካታ የማጣሪያና የፍፃሜ ፉክክሮችን በተለያዩ ርቀቶች አተስተናግዷል።
ቻምፒዮናው በሶስተኛ ቀን ውሎው በ800 ሜትር ሴቶች ተጠባቂ የፍፃሜ ውድድር ያስተናገደ ሲሆን በጠንካራ ፉክክር በታጀበው ውድድር መርሃዊት ጽጋቡ ከኮልፌ ቀራኒዮ በ2:03″24 ሰዓት አሸናፊ መሆን ችላለች። እሷን ተከትላ አትሌት ሀብታም ገበየው ከአማራ ፖሊስ በ2:03″48 2ኛ ሆና በመጠናቀቅ የብር ሜዳለያ ስታጠልቅ፤ አትሌት ምጥን እምነቴ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በ2:03″68 ሰዓት በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። በተመሳሳይ ቀን በተካሄደው የወንዶች 800 ሜትር ፍጻሜ ጀነራል ብራኑ ከኦሮሚያ ክልል 1:49″98 በሆነ ሰዓት አንደኛ፣ ብርሃኑ ጋሮምሳ በተመሳሳይ ከኦሮሚያ ክልል 1:49″12 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ እንዲሁም ሳሙኤል ቡቼ ከሲዳማ ክልል ሶስተኛ ሆኖ ማጠናቀቅ ችሏል።
በወንዶች አሎሎ ውርወራው ውድድር አትሌት ጨቀሳ ጉርጌ ከመቻል ስፖርት ክለብ 15.25 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሲሆን ፣ በልስቲ እሼቴ ከተመሳሳይ ክለብ 15.16 ሜትር በመወርወር የብር ሜዳለያ ባለቤት ሆኗል። አትሌት በቀንዳ ፉርሳ ደግሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 15.12 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳለያውን ወስዷል። በሴቶች ዲስከስ ውርወራ የኔሰው ያረጋል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 37.80 ሜትር በመወርወር ቀዳሚ ስቶን፣ ማሪቱ አለባቸው ከአማራ ክልል 34.04 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ሴና አብደታ ደግሞ 32.93 በመወርወር ሶስተኛ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች።
ውድድሩ ትናንትና ቀጥሎ ሲውልም አራት የፍጻሜና አምስት የማጣሪያ ውድድሮች ተካሂደዋል። ከነዚህም መካከል ትኩረትን የሳበው የሴቶች 5ሺ ሜትር ፍጻሜ ውድድር ተደርጓል። ከፍተኛ ፉክክር በታየበትና ተመልካቹን ቁጭ ብድግ ባደረገው ውድድር ውብርስት አስቻለ ከአማራ ፖሊስ 16:20″51 በሆነ ሰዓት ቀዳሚሆና ስታጠናቅቅ፣ አይናዲስ መብራት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 16:25″49 በሆነ ሰዓት የሁለተኝነቱን ደረጃ ይዛ ፈጽማለች። አሳየች አይቸው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ሶስተኛ ሆና ጨርሳለች። በተመሳሳይ እለት የወንዶች መዶሻ ውርወራ ውድድር ፍጻሜ ያገኘ ሲሆን በልስቲ እሼቴ ከመቻል 40.66 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳለያ ባለቤት መሆን ችሏል። ይበልጣል ላቀ ከአማራ ክልል 38.04 ሜትር በመወርወር የብር ሜዳለያን ሲያጠልቅ፣ ሙሉቀን ሱዩም ከተመሳሳይ ክልል 30.15 ሜትር በመወርወር በሶስተኝነት የነሐስ ሜዳለያ ተሸላሚ መሆን ችሏል።
ቻምፒዮናው በግልጽ በሚታዩ የዕድሜ ማጭበርበር ችግሮች ቢፈተንም በፉክክር ቀጥሎ ሊጠናቀቅ የአንድ ቀን ዕድሜ ብቻ ቀርቶታል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ እነዚህን የእድሜ ማጭበርበር ችግሮች ለመቅርፍ አስተማሪ እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥልጠና ምርምር ዳይሬክተርና የውድድሩ ማናጀር እንስትራክተር ሳሙኤል ብርሃኑ፣ በየእድሜ ተገቢነት ጥያቄ ዛሬ የተጀመረ እንዳልሆነና ከዚህ በፊት በነበሩት ውድድሮችም የነበረ ችግር መሆኑን ገልጸዋል። እነዚህን ጥያቄዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ከቦርድ እስከ ፕሮፌሽናል ባለሙያ ድረስ ከዚህ በኋላ እድሜን ባማከለ መልኩ ውድድሮች መደረግ እንዳለባቸው ስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ዕድሜን ያጭበረበሩ ሁለት መቶ ሃምሳ የሚደርሱ አትሌቶች መቀነሳቸውንም ተናግረዋል። ተገቢ ሆኖ ያልተገኙትን የመቀነሱ ስራ እስከመጨረሻ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል። ክልሎች፣ክለቦችና ማሰልጠኛ ተቋማትም የመመልመያ ዜዴያቸውን መቀየር እንዳለባቸው አብራርተዋል። ይህ ውሳኔ የዘገየው በክለቦች ችግር እንደሆነ የገለጹት ኢንስትራክተር ሳሙኤል ውድድሩ ሊጀመር ሁለት ቀን እስኪቀረው የአትሌቶችን ዝርዝር እንኳ ያላስገቡ ክለቦች በመኖራቸው ውሳኔው ሊዘገይ መቻሉን ጠቅሰዋል። ጠንካራና አስተማሪ የሆነ እርምጃን በመውሰድ ሞራላቸው የተጎዳውን ታዳጊዎች ተገቢውን እድል መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል። ስራው የፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ክለቦችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ሊረባረቡ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ አስልጣኝ የሆነው ጌታቸው ሙሉጌታ በበኩሉ፣ ውድድሩ አስደሳች መሆኑን ገልጸው ፌዴሬሽኑ የወሰደው እርምጃ ተገቢ እንደሆነ አስረድተዋል። አሰልጣኙ አያይዞውም የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ተገቢ ቢሆንም መዘግየቱን ጠቁመዋል። ወደ ውድድር ሳይገባ ርምጃው ተወስዶ ቢሆን የተሻለ እንደነበርም አክለዋል። በቻምፒዮናው የዕድሜ ጉዳይ መነጋገርያ ሆኖ ቢቀጥልም አንዳንድ ተስፋ ሰጪ ነገሮችም ታይተዋል። ከነዚህም እንደተሞክሮ ሊወሰድና ለሌሎችም አርአያ ሊሆን የሚችለው ከጥሩነሽ ዲባባ ማሰልጣኛ የመጡ ተወዳዳሪዎች በተሻለ የእድሜ ተገቢነት ጠንካራ ፉክክር በማድረግ በበርካታ ውድድሮች አሸናፊ መሆናቸው ነው። ከወጣት አትሌቶች ማሰልጠኛ ተቋማት የመጡት አብዛኞቹ አትሌቶች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ መቻላቸውም ሌላው ተስፋ ሰጪ ምክንያት ነው።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም