አልወደቅንም ብለን አንዋሽም፤
የዘንድሮው የልጆቻችን የአሥራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ውጤት ላለፉት ረጅም ዓመታት አውቆ የተጨፈነው የሀገሪቱ ዓይን እንዲበራ፣ሆን ተብሎ የተደፈነው ጆሮዋ እንዲከፈትና እውነቱን ይፋ ላለመግለጥ የተሸበበው አንደበቷም እንዲፈታ የትምህርቱን ዘርፍ ከሚመራው ሚኒስቴር መ/ቤት ፍርጥርጥ ተደርጎ የቀረበው ሪፖርት “ለሀገራዊ ፈውሳችን” መልካም አጋጣሚ የፈጠረ ይመስለናል። “አለባብሰን አርሰን ዳግም በአረም እንዳንመለስም” የማንቂያ ደውሉ በግልጽነት ተደውሎልናልና ትምህርት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታችን ሆይ! “አሹ!” በማለት እናመሰግናለን።
መቼም ትዝታ አያረጅምና፡- “ወንድሜ ያዕቆብ ተኛህ ወይ! ደውል ተደወለ ተነሳ!” እያልን በልጅነታችን እየዘመርን ወደ ትምህርት ቤታችን እንገሰግስበት የነበረውን ጥንታዊ የተውሶ መዝሙር በትዝታ መለስ ብለን እናስታውስ። ይህንን መዝሙር እኛ ወላጆች እንደገና አድሰነው (የሙዚቃ ባለሙያዎቹ Remix እንዲሉ) የያዕቆብን ስም በኢትዮጵያ ስም እየለወጥን “ደውል ተደወለ ተነሱ!” እንድንባባል ጊዜው ግድ ያለን ይመስላል። በልጆቻችን የፈተና ውጤት ምክንያት ከተደናገጥንበትና በኃዘን ካቀረቀርንበት ቀና በማለት የሰለለውን ድምጻችንን በአንድ አስተባብረን ለኅብረ ዝማሬ አብረን ብንሰለፍ ልጆቻችንም በማጀቡ ሳያግዙን አይቀሩም።
“የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም፤ የሞተም አይመለስም” እንዲሉ ጎፈነነም ጎመዘዘ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሆን ተብሎ ለዓመታት የተዘራው “እንክርዳድ” ፍሬ አፍርቶ እነሆ ነዶውን ለመታቀፍ ግድ ብሎናልና ተደናግጠን ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። ለሀገራዊ ፈውሳችን ሊረዳን ስለሚችልም የውጤቱን ሪፖርት በአሜንታ መቀበሉ ሳይሻል አይቀርም። ነፍሰ ኄሩ ደራሲያችን ከበደ ሚካኤል “መርዝም መድኃኒት ነው ሲሆን በጠብታ” እንዳሉት መሆኑን ልብ ይሏል።
ጉዳዩን በጥልቅ እንመርምረው ካልን በብሔራዊው ፈተና “በገፍ” የወደቁት ተማሪዎቻችን ብቻም አይደሉም። ሀገርም ልክ እንደ ተማሪ ልጆቿ በአስደንጋጩ ውጤት ሸብረክ ብላ እንደተደነቃቀፈች ቢመርም ልትውጠው፣ ቢያንገሸግሽም ልትጎነጨው ይገባል። መንግሥትም ሆነ ዜጎች ከትምህርት ሥርዓታችን ጋር አልወደቅንም ብለን አንዋሽም፤ እንደወደቅን እንቀራለን ብለንም ተስፋ አንቆርጥም። የሚሻለው ውድቀታችንን አምነንና ውጤቱን በፀጋ ተቀብለን ከገባንበት አረንቋ ለመውጣት መተባበር ብቻ ነው።
ይህንን ጠነን ያለ አስተያየት በድፍረት ለመሰንዘር የተዳፈርኩት ከመማር ማስተማሩ ጋር በተያያዘ የግል ተሞክሮዬ ግድ ስለሚለኝ ብቻም ሳይሆን እንደማንም ወላጅና ዜጋ የትምህርታችን ውድቀት በሁለንተናዊ መልኩ የሀገርም ውድቀት እንደሆነ ስለሚያሳስበኝና ስለሚያስቆዝመኝ ጭምር መሆኑን አስቀድሜ በትሑት መንፈስ ለመግለጽ እወዳለሁ።
ምን ማለቴ ነው?፡- ይህ ጸሐፊ የዕውቀት አቅሙ የፈቀደውን ያህል በሀገሪቱ የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የጠብታ ያህልም ቢሆን አሻራውን ለማሳረፍ ተደጋጋሚ እድል አጋጥሞታል። ከዘመነ የኮሌጅ ተማሪነቱ ጀምሮ በአንጋፋው የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የአንድ ዓመት የማስተማር ልምምድ አድርጓል። አሜሪካን ሚሽን እየተባለ ይጠራ በነበረው የልጃገረዶች ት/ቤት፣ በጄኔራል ዊንጌት የኮንስትራክሽን ኮሌጅና በአንዳንድ ኮሌጆች ውስጥ በትርፍ ሰዓት (Part Time) መምህርነት ለበርካታ ዓመታት ያህል አገልግሏል።
አደራውን በሚገባ መወጣት አለመወጣቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ከትምህርት ሚኒስቴር የፈተናዎች ኤጀንሲ “የፀረ ኩረጃ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር” የሚል “እቅደ ቢስ” ማዕረግ ተሰጥቶት ለተወሰኑ ጊዜያት ተፍ ተፍ ለማለት ሙከራ ማድረጉ አልቀረም። “አደራህን በሚገባ አልተወጣህም” የሚባል ከሆነም ሰበቡን ወደ ጎን ትቶ ኃላፊነቱን በግሉ ለመውሰድ አያመካኝም።
ልጆቻችን ከ5ኛ – 8ኛ ክፍሎች እየተማሩባቸው ባሉት የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መጻሕፍት ዝግጅት ላይም ከአዘጋጆቹ አንዱ በመሆን አስተዋፅዖ አድርጓል። መጻሕፍቱ በልጆቻችን ሕይወት ውስጥ ይህ ነው የሚባል የበጎ ሰብዕና ለውጥ ያለማምጣታቸውን ሲያስብም በተደረገው ፍሬ አልባ ድካምና ጥረት መጸጸቱ አይቀርም።
አገልግሎት እየሰጡ ላሉት እጅግ በርካታ የተማሪዎችና የመምህሩ መምሪያ መደበኛ መጻሕፍት ላዘጋጀው የሀገር ውስጥ የግል ኩባንያም የፕሮጀክቱ አስተባባሪና በመጻሕፍት አዘጋጅነትም የአቅሙን ድርሻ ተወጥቷል። የዚህም ድካም ፍሬ ያስከተለው ለውጥ የሚጠበቀውን ያህል ባለመሆኑ ሳያስተክዘው አልቀረም።
በግሉም በርከት ያሉ የተማሪ መርጃ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል። በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይም ቀደም ባሉት ዓመታት የትምህርት ሥርዓታችንን እየፈተኑ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ የግሉን አስተያየት ደጋግሞ ለማንጸባረቅ ሞክሯል። ስለዚህም ድምጸቱ ይጠንክርም ይላላ በዚህ ርእሰ ጉዳይ ላይ አስተያየት ለመስጠት የሞራል ድጋፍ የሆነው የዘረዘራቸው ውሱን ተሞክሮዎቹ ናቸው።
የዚህ ዓመቱ የብሔራዊ ፈተና ውጤት በዝርዝር በቀረበበት መልኩ ከአሁን ቀደም በግልጽነት ሪፖርት ቀርቦ ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደለሁም። “ቢሆን ኖሮ ግን” የዛሬው ውደቀታችንን ጥቂትም ቢሆን ባለዘበልን ነበር። አጠቃላዩን የውጤቱን ይዘት ለአብነት እናስታውስ።
በመላው ሀገሪቱ ለፈተናው ይቀመጣሉ ተብለው ከተገመቱት 908,256 ተማሪዎች መካከል በሥነ ምግባር ጥሰት፣ ባልተገመቱ ልዩ ልዩ ምክንያቶችና በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሚቀነሱት ተቀንሰው በአጠቃላይ ወደ 896,500 ያህል ተፈታኞች ለፈተና መቀመጣቸው ከእነ ዝርዝር ውጤቱ ለሕዝብ ተብራርቶ መቅረቡ ይታወሳል።
ከእነዚህ ተፈታኞች መካከል በለስ ቀንቷቸው 50% እና ከዚያ በላይ የድካማቸውን ውጤት ያገኙት ተማሪዎች ቁጥር 29,909 ወይንም (3.3%) ብቻ መሆኑ ምን ያህል እንዳስደነገጠ ሀገር ምስክር ነው። አንድም ተማሪ ያላሳለፉ ትምህርት ቤቶችን ጉዳይ በተመለከተም በ“ዝም አይነቅዝም” ይሉኝታ የተላለፈ ቢመስልም ውሎ አድሮ ጉዳቱ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። “ስም ይወጣል ከቤት፤ ይከተላል ከጎረቤት” ይባል የለ።
የአኃዛዊ ትንተናው እንደተጠበቀና “ኃላፊነቱን ማን ይውሰድ?” የሚለው መጠቋቆም እንዳለ ሆኖ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ዜጎች ሥነ ልቦና ላይ ያደረሰው ጉዳት ይህ ልኩ የሚባል ዓይነት አይደለም። ጉዳዩን ጥቂት እናፍታታው፡- ውጤት ሳይቀናቸው ቀርቶ የስሜት ስብራት በደረሰባቸው ተፈታኝ ልጆቻችን ቁጥር ላይ የወላጆቻቸውን፣ የእህት፣ የወንድም፣ የአክስት፣ የአጎት፣ የቤተዘመድ፣ የጓደኞቻቸውን ወዘተ. አኃዝ ስንደማምር ሚሊዮን ቁጥሩ ምን ያህል ወደ ላይ እንደሚያሻቅብ መገመት አያዳግትም።
ይህ ሁሉ ዜጋ ተሳቋል፣ ተሸማቋል። ውጤት አልባ ሆነው አንድም ሆነ ጥቂት ተማሪዎችን ለማሳለፍ የተሳናቸውና እንደነገሩ ተፍገምግመው አንድና ጥቂት ልጆቻቸውን ለኮሌጅ ያበቁ የየትምህርት ቤቱ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የልብ ኃዘን ሲታከልበትማ ቁጥሩ የትዬለሌ ሊሆን እንደሚችል አይታበልም።
ከሥነ ልቦና ጉዳቱ ጎን ለጎን በኢኮኖሚው ላይ የደረሰው ክስረትም በቸልታ የሚታለፍ አይደለም። ሀገር የራሷን ድርሻ በጅታ፣ ቤተሰብ ከኑሮው ውጣ ውረድ እየታገለ ልጆቹን ያስተማረበት ወጭ፣ ዓለም አቀፎቹ የተራድኦና አበዳሪ ተቋማት ለኢትዮጵያ የትምህርት ድጋፍ ሆጨጭ አድርገው የዘረገፉት ሀብት በስሌቱ ውስጥ ቢታከል ከአንድም ሁለት፣ ከሁለትም ሦስት ምናልባትም ከዚያ በላይ የህዳሴን ያህል ግድቦች የሚያሠራ ገንዘብ እንደፈሰሰ ማሰቡ አይከብድም። ምንም አንኳን የጸሐፊው ግምት በሙያ የተደገፈ ባይሆንም።
“የእኛስ የቤት ጉድ ነው፤ መዘዙ የባዕዳን ነው” እንዲል ብሂላችን፤ ከትክክለኛ ምንጭ የሚጠቀስ አንድ ዘለላ አብነት ብቻ ላስታውስ። የኢትዮጵያን አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓት ጥራት ለማስጠበቅ በዓለም ባንክ ዋና አስተባባሪነት IDA-International Development Association, FTI-CF – The Fast Track Initiative Catalytic Fund, The Netherlands, DFID, Italian Development Cooperation and Finland etc., ከተባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት በሁለት ዙሮች General Education Quality Improvement Program, GEQIP በሚል ፕሮግራም የተደረገው የገንዘብ ድጋፍ (ምናልባትም ከፊሉ ብድር ሊሆን ይችላል) በቢሊዮን ዶላር የሚሰላ ነው።
በኖቬምበር 2013 (Project ID P129828) 529.76 ሚሊዮን ዶላር እና በዲሴምበር 2017 (Project ID P163050) 582.50 ሚሊዮን ዶላር በድምሩ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ለትምህርቱ ሥርዓት ማሻሻያ እንደተገኘ ይታመናል። በእነዚህ አኃዞች ላይ ለምናልባቱ ልዩነት ካለና የሚታረም ሃሳብና ቁጥር ካለ የትምህርት ሚኒስቴር ተገቢውን ማረሚያ ሊያክልበት ይችላል። መረጃው የተገኘው ከዓለም ባንክ ኦፊሴላዊ ሳይት ላይ መሆኑን ማሳወቁም አግባብ ነው።
ይህ ጸሐፊ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከረው የተማሪዎች ቴክስት መጻሕፍትና የመምህራኑ መምሪያ በሀገር ውስጥ ተዘጋጅቶ በውጭ ሀገር ሊታተም የቻለው ከዚሁ የዓለም ባንክ በተገኘው የፕሮጀክት ገንዘብ አማካይነት ነበር። ከአሁን በፊት በሌላ ጽሑፌ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ለሕትመት ወደ ውጭ የፈሰሰው የዶላር መጠን የሀገር ውስጥ አሳታሚዎችን አቅም አጎልብቶ ገንዘቡ እዚሁ እንዲቀር ቢደረግ ኖሮ ጥቅሙ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” ይሉት ብጤ ይሆን ነበር።
ያለመታደል ሆኖ ግን ከዚሁ በልመናና በተማጽኖ ከተገኘው ሀብት ላይ ምን ያህሉ በትክክል ሥራ ላይ ውሏል? ምን ያህሉ ባክኗል? እጃቸው ባደፈ ሕሊና ቢስ የፕሮግራሙ አስተባባሪዎች ምን ያህል ገንዘብ ተዘርፏል? ባክኗል? ወዘተ. ፍርድ ቤት ድረስ ያጓተቱ አንዳንድ ጉዳዮች እንዳሉ ስለሚታወቅ ግልጽ ሪፖርት ቢቀርብልን እውነቱ አፍጦ ይገለጥ ነበር።
የሆነውስ ሆነና ለወደፊቱ ምን ይደረግ? ምላሽ ማግኘት የሚገባው ይህ መሠረታዊ ጥያቄ በትምህርት ሥርዓቱ ባለድርሻ አካላት አጥብቆ ሊጠየቅ ይገባል። በዚህ ጸሐፊ እምነት ከ50% በታች ያገኙት የተወሰኑ ተማሪዎች በየዩኒቨርስቲው ተመድበው ለአንድ ዓመት በልዩ ፕሮግራም የማጠናከሪያ ትምህርት እንዲሰጣቸውና ፈተናውን ካለፉ አቅማቸውን አበርትተው በቀጣዩ ዓመት ባስተማራቸው ዩኒቨርስቲ ውስጥ በመጀመሪያ ዓመት ተማሪነት እንዲቀጥሉ መታቀዱ ትልቅ እፎይታ ይሰጣል።
ይህንን “የጭንቅ ቀን መፍትሔ” አመንጭቶ የብዙዎች ተስፋ እንዲለመልም በማድረጉ ረገድ ትምህርት ሚኒስቴርን ደግመን ማመስገኑ ተገቢነት ይኖረዋል። ውጤቱን በተለመከተ ግን እንዲህ ነው ብሎ ከመተንበይ ይልቅ ለወደፊቱ በይደር ማስተላለፉ ይበጃል።
ይህ የታሰበው የዩኒቨርስቲ መሸጋገሪያ የትምህርት ፕሮግራም የቀድሞ የልዑል በእደ ማርያምን የላቦራቶሪ ትምህርት ቤት ያስታውሰኛል። ልዩነቱ የልዑል በእደ ማርያም ተማሪዎች ከየክፍለ ሀገሩ በጉብዝናቸው እንደ ከዋክብት ደምቀው በከፍተኛ ውጤታቸው ለተመረጡ ጎበዞች የተዘጋጀ ፕሮግራም ሲሆን (ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቁ በቀጥታ ወደ ማስተማር ሙያ መመደባቸው ሳይዘነጋ)፤ ለእኛዎቹ ለዛሬ ልጆቻችን ግን ይህ ፕሮግራም የሚዘጋጅላቸው በትምህርታቸው ደክመው የጎበጡትን ለማቅናት ታስቦ ነው። ገበያው ፊት ነስቶት አልሸጥ ብሎ ቅቤውን ወደ ቤት ይዞ የተመለሰ ባለ ሀገር “ችግር በቅቤ ያስበላል!” ብሎ እንደተረተው መሆኑ ነው።
የትምህርት ሥርዓቱ ከተዘፈቀበት አረንቋ እንዴት መውጣት እንደሚገባው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሚገባ እንዳሰቡበት ይገባኛል። የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም እንደሚተገበሩ አይጠፋኝም። ቢሆንም ግን አንዳንድ ሃሳቦችን ልፈነጣጥቅ።
በሌሎች ሀገራት እንደተለመደው የትምህርት ሥርዓቱን እግር በእግር እየተከታተሉ የሚያበረታቱ፣ የሚሄሱ፣ አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የሚያግዙ፣ ምክረ ሃሳቦችን የሚያቀርቡ ከፖለቲካና ከመሳሰሉ ፍረጃዎች ነጻ የሆኑ ምሑራን የሚሰባሰቡባቸውና የሚመካከሩባቸው የቲንክ ታንክ ቡድኖች እንዲቋቋሙ መንግሥት ሊያበረታታና ሊደግፍ ወቅቱ ግድ እያለ ነው።
ከዚህ ዓመቱ የፈተና ውጤት ለማየት እንደተቻለው የተሻለ ውጤት ያመጡት ት/ቤቶች አብዛኞቹ ተማሪዎችን በአዳሪነት ተቀብለው የሚያስተምሩ ወይንም በየዩኒቨርስቲው ሥር የተቋቋሙ የኮሚዩኒቲና ሞዴል የሚባሉ ት/ቤቶች እንደሆኑ ከሪፖርቱ መገንዘብ ተችሏል። ይህ ስትራቴጂ አበረታች ከሆነ ተጠናክሮ እንዲስፋፋ ልዩ ትኩረትና ክትትል ሊደረግበት ይገባል።
ቀደም ባሉት ዘመናት ሲተገበር እንደነበረው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ተማሪዎች ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተውጣጥተው እንዲወዳደሩና እንዲፎካከሩ ማድረጉ የተማሪውን ሞራል ከፍ የማድረግ አቅም ስላለው ታስቦበት ቢተገበር አይከፋም። ከዚሁ ጎን ለጎንም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እንጂ የፖለቲካ ጣጣ ውስጥ እንዲዘፈቁ ማስገደድና ማባበል ጉዳቱን በተለያየ መልኩ ስላየነው ፖለቲከኞች እጃቸውን እንዲሰበስቡና መምህራንም ከማስተማር ዋነኛ ተግባራቸው የሚያዘናጋ የፖለቲካ ጣጣ ውስጥ ገብተው ማስተማሩን ቸል እንዳይሉ አጥብቆ መከታተል ያስፈልጋል።
ከገጠር እስከ ከተማ ለቀበሌም ሆነ ለማንኛውም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ፈጥኖ ዐይን የሚጣልባቸው መምህራን ናቸው። የግል የፖለቲካ መብታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ከዋናው ተልዕኳቸው እንዳያዘናጋቸው ግን መጠንቀቅ ይገባል። ሀገሪቱን ዛሬም ቢሆን በከፍተኛ ሥልጣን እየመሩ ያሉት ከመምህርነት ሙያ የወጡ መሆናቸውን ዘንግቼ አይደለም። ገደብ ይበጅለት፣ ከመጠን አልባ መጎተትም መምህራኑ ይረፉ የጸሐፊው ጽኑ ሃሳብ ነው።
የወላጆች ኃላፊነትም መጠኑ ከ እስከ ተብሎ ገደብ እንደማይበጅለት ሊታወቅ ይገባል። ልጅን ትምህርት ቤት ልኮ እንደፍጥርጥሩ ይሁን ብሎ መሰላቸት ጉዳቱ በግልጽ ስለታየ ሊደገም አይገባም። በተለይም ወላጆች ልጆቻቸው ምርኮኛ ለሆኑለት የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ተገቢውን ክትትል በማድረግ ሊታደጓቸው ይገባል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ዳግም ለመመለስ ቀጠሮ ይዣለሁ። ሰላም ለሕዝባችን፤ ለዜጎችም በጎ ፈቃድ።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም