የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የፈተና ውጤት እንደ ሀገር የትምህርት ውድቀታችንን አደባባይ ላይ ያሰጣ ሰሞነኛ መነጋገሪያችን ሆኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አዳዲስ አሠራሮችን መዘርጋቱን ተከትሎ ያለፉት የሁለት አስርተ ዓመታት የትምህርት ውድቀታችን ፍንትው ብሎ መታየት ጀምሯል። በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከተፈተኑት 896 ሺህ 520 ተማሪዎች ውስጥ 29 ሺህ 909 ያህሉ ወይም ሶስት ነጥብ ሶስት በመቶ ተፈታኞች ብቻ ማለፋቸው የትምህርት ውድቀቱ አንድ ማሳያ ነው።
በተጠቀሰው ዓመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ካስፈተኑ 2ሺህ 959 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 1 ሺህ 161 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ ሳያሳልፉ መቅረታቸው ደግሞ በኢትዮጵያ የትምህርት ታሪክ አይተን የማናውቀው አሳፋሪና አስደንጋጭ ዜና ሆኖብናል። እንዲህ አይነት ያልተለመደ ነገር ሲገጥመን ‹‹ለምን?›› ማለት ሰዋዊ ባህሪችን ስለሆነ ‹‹ለምን ይህን ያህል ተማሪ ወደቀ?›› ብለን ተብሰክስከናል።
መልሱ ግልጽ ነው። የተመዘገበው ውጤት ትንግርት መስሎ የታየን በተወሰነ መልኩ ከስርቆትና ከኩረጃ የጸዳ ፈተና ስለተሰጠ ነው። ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት አብላጫውን ትኩረቱን በትምህርት ጥራት ላይ ሳይሆን ሽፋን ላይ ያደረገ የትምህርት ፖሊሲ ስለነበረን እና ለስርቆትና ለኩረጃ የተመቻቸ የፈተና ሂደትን እንከተል ስለነበር ተማሪዎች በገፍ ያልፉ ነበር። የትምህርት ሥርዓታችን ልክ እንደ ጸጉራም ውሻ ያለ እየመሰለን የሞተው አሁን ሳይሆን ያኔ ነው።
የክልል ኮታን ታሳቢ በማድረግ ብቻ አስፈላጊነታቸው ሳይጠና በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችን እየገነባን እና ተማሪዎችን በገፍ እያሳለፍን ስናጉርባቸው እድገት እንጂ ውድቀት አልመሰለንም ነበር። ባለፉት ዓመታት ድል ያለ ድግስ ደግሶ ልጁን ከዩኒቨርሲቲ ያላስመረቀ ወላጅ አለ ከተባለ ልጅ ያላስተማረ ወይም የመደገስ አቅም የሌለው ብቻ ነው።
ብዙ ወላጆች ልጆቻቸውን አስመርቀዋል፤ ከተመረ ቁበት ሙያ ውጭ የተለያዩ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ከተመራቂዎች የሚጠበቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በተማሩት ሙያ ሥራ ላይ የተሰማሩት ግን ጥቂቶች ናቸው። ለዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው አብዛኛው ተማሪ ተሰጥዖውን እና ዝንባሌውን ፈልጎ ከማግኘት ይልቅ ዩኒቨርሲቲ መግባት የሚቀለው በመሆኑ ነው።
ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎችን የሚለየው የቀድሞው ዘርዛራው ወንፊት አሁን ቀዳዳው ጠበብ በማለቱ በርካቶችን አንጓሏቸዋል። ዛሬ ያጨድነው ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት የዘራነውን ነው። በግድ የለሽነት የተዘራውን በግድ የለሽነት ማጨድ እንጂ በጥንቃቄ ማጨድ አያስፈልግም ከተባለ ግን ነገ ሌላ ችግር አስከትሎ መምጣቱ የማይቀር ነው።
በጥንቃቄ ባይዘራም በጥንቃቄ እያጨዱና እየወቁ ምርቱን ከገለባው መለየት ጥቅም ሀገራዊ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም ። ያለፈውን አሠራር ትቶ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚከተለውን መንገድ መደገፍ ከዜጎች የሚጠበቅ ነው። ትምህርት ሚኒስቴርም ጥራት ያለው ዘር ዘርቶ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት ከታችኛው የክፍል ደረጃ ጀምሮ መሥራት እንደሚገባው የተማረበት ነው።
ከሰሞኑ ይፋ በሆነውና አጀብ ባስባለን ውጤት ዙሪያ አንዳንድ ግለሰቦች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቅ እያሉ የትምህርት ሚኒስቴርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይህ ተገቢ አይደለም። ተቋሙ ስርቆትና ኩረጃን ለማስቀረት የሄደበት ርቀት ሊያስመሰግነው እንጂ ሊያስወቅሰው አይገባም። ተማሪዎች የተፈተኑት ከተማሯቸው ይዘቶች የወጡ ጥያቄዎችን እስከሆነ ድረስ ለውጤታማነታቸውም ሆነ ለውድቀታቸው የመጀመሪያዎቹ ባለድርሻዎች ራሳቸው ናቸው።
የተመዘገበው ውጤት ትምህርት ሚኒስቴር ከስርቆትና ከኩረጃ የጸዳ የፈተና ሂደት ማካሄዱን የሚመሰክር እና የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ያደረገውን ጥረት የሚያሳይ ነው። በዚህ አሠራሩም ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ጎህ እየፈነጠቀ መሆኑን አሳይቶናል።
ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና እየተሰረቀ ፤የተወሰኑ ትምህርቶች እየተሰረዙ ፤ አልተሰረቁም በተባሉት ላይ ብቻ ተመሥርቶ የማለፍና የመውደቅ እድል ይወሰን እንደነበር እናስታውሳለን። በዚህ ውሳኔ ማለፍ የሚገባቸው ተማሪዎች ወድቀዋል፤ መውደቅ የሚገባቸውም አልፈዋል። ፈተና ሙሉ ለሙሉ ተሰርዞ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ዳግም ለማዘጋጀት የተገደደበት አጋጣሚ እንደነበርም መዘንጋት አያስፈልግም።
የትምህርት ሥርዓቱ ውድቀት ከተማሪው ውጤት ጋር ብቻ ሳይሆን ከሥነምግባርም ጋር የተያያዘ ነው። ዛሬ በየአካባቢው ተደራጅተው የሕዝብን ሰላም የሚያውኩትና የሀገር ስጋት የሆኑት ትናንት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ውሃ የማያነሱ ምክንያቶችን እየደረደሩ ግጭቶችን ሲለማመዱ የነበሩ የትምህርት ሥርዓቱ ያፈራቸው ትውልዶች ናቸው።
የትምህርት ሥርዓታችን በዕውቀት የታነጸ፣ በሥነምግባር የተኮተኮተ ትውልድን ከማፍራት አንጻር ከፍተት ያለበት መሆኑ ላለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት በምሑራን ሲተች የኖረ ጉዳይ ነው። የብዙዎቻችን ትዝብትም ከዚህ እውነታ የሚጋጭ አይሆንም። የአንድ አገር የትምህርት ፖሊሲ ሲቀረጽ መሠረት የሚያደርገው ሀገሪቱ የምትከተለውን የዕድገት መስመር ነው። ኢትዮጵያ ከሃያም ይሁን ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ያሠበችው የእድገት ግብ ላይ ለመድረስ ምን ዓይነት የተማረ ሰው ያስፈልጋታል የሚለው የትምህርት ፖሊሲያችን አስኳል ሊሆን ይገባል።
ሥርዓተ ትምህርት፣ መርሐ ትምህርት፣ የትምህርት ይዘቶች ፣የማስተማሪያ ቁሳቁስ የትምህርት ፖሊሲውን መሠረት አድርገው በተዋረድ የሚዘጋጁ ናቸው። ከዚህ በኋላ የመማር ማስተማሩ ሂደት ይከናወናል። ተማሪዎች እንዲያውቁ የተፈለገውን እውቀት መጨበጥ አለመጨበጣቸው በተከታታይ ምዘናዎች እየተፈተሸ እና ብቃታቸው እየተረጋገጠ ከክፍል ወደ ክፍል እንዲያልፉ ይደረጋል። በመጨረሻም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ይሰጣቸዋል። ይህ ሳይንሳዊ የትምህርት ሂደት ነው።
በትክክለኛው የትምህርት ዓለም ውስጥ ያለፉ ሰዎች የተሻለ አመለካከት፣ የተቃና ባሕሪ ፣ የሰላ አንደበት ፣ የመጠቀ አስተሳሰብ፣የረቀቀ አሠራር ፣ የዳበረ ክህሎት ወዘተ ይኖራቸዋል። አንድ ሰው የተማረ ነው የሚባለው በእያንዳንዱ ትምህርት ድምር ውጤት ሰብዕናው ሲለወጥ ነው። ኢትዮጵያ በአግባቡና በሥርዓቱ የተማረ ትውልድ አፍርታ የተሻለች ሀገር እንድትሆን ትክክለኛውን የትምህርት ሂደት መደገፍ ያስፈልጋል። የተገለጸልን የ12ኛ ክፍል ውጤት የትምህርት ሥርዓታችንን ሞት ያሳየን ነውና ለትንሳኤው እንትጋ፤ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥም በጋራ እንቁም።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም