የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ለምክትል ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ እውቅና ሰጠ። ደራቱ እውቅናው የተሰጣት ለሰላም ላበረከተችው አስተዋጽኦ መሆኑም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዚዳንትነት እየመራች የምትገኘው አንጋፋዋ አትሌት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ በኢጋድ እውቅና የተሰጣት ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆና ነው። ደራርቱ እውቅናው የተሰጣት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) በኬንያ ሞምባሳ ዓመታዊ ሪፖርቱን ለሶስተኛ ጊዜ እየገመገመ ባለበት ወቅት ነው። በመድረኩ ላይ ከሚካሄዱ መርሃግብሮች መካከል አንዱ መልካም አበርክቶ ላላቸው ግለሰቦች እውቅና መስጠት ሲሆን፤ ከድርጅቱ አባል አገራት መስፈርቱን ላሟሉት ይሰጣል።
በመልካም ምግባሯ የምትታወቀው ደራርቱ ቱሉም እውቅናውን እንድታገኝ ምክንያት የሆነው በኢትዮጵያ የሰላም ድምጽ በመሆን ባበረከተችው አስተዋጽኦ ነው። በቀጠናው በአየር ንብረት ለውጥ፣ አደጋ መከላከል፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ሰብዓዊ እርዳታና በሌሎች ጉዳዮች የጎላ አበርክቶ የነበራቸው 21 ግለሰቦች እውቅናውን አግኝተዋል። ደራቱም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ሰላም እንዲሰፍን በተደጋጋሚ በተለያዩ መድረኮች ድምጽ በመሆን ባበረከተችው በጎ ተግባር እውቅናው ተበርክቶላታል። ደራርቱም በቦታው በአካል በመገኘት እውቅናውን ወስዳለች።
በመድረኩ ላይ ጀግናው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ እንዲሁም ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ እውቅናውን ያገኙ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ናቸው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም