የማዕድን ልማት ለማኅበረሰብ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ምርቱ ለዓለም ገበያ ቀርቦ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ከውጭ የሚገባውን የማዕድን ውጤት በአገር ውስጥ በመተካት የምንዛሪ ወጪን በማስቀረት በአገር የምጣኔ ሀብት እድገት ላቅ ያለ ሚና እንዲወጣ ይጠበቃል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እምቅ አቅም ያለውን ይህን ዘርፍ በማነቃቃት ያለውን አበርክቶ ለማጉላት የሚያስችሉ ሥራዎችም በመንግሥት በኩል ሲከናወኑ ቆይተዋል። በተለይም በያዝነው በጀት ዓመት በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ በፌዴራልና በክልሎች ጭምር የንቅናቄ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሀብትን በመለየት፣ ዘርፉን ከፍ ባለ ደረጃ ለመምራት የአደረጃጀትና የመመሪያ ማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ እንዲሁም ማዕድን ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር የተናበበ ሥራ ለመሥራትና ሁሉም የየድርሻውን እንዲወጣ በማድረግ ረገድ ከተከናወኑት ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው።
በዘርፉ ውጤት እንዲመዘገብ በበጀት አመቱ ከላይ የተነሱት ሥራዎች ቢከናወኑም ሕገወጥ ግብይትና የፀጥታ ስጋቶች ከፍተኛ ማነቆዎች ነበሩ። በተለይም ወደ ብሔራዊ ባንክ መግባት የነበረበት የወርቅ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለው በዚህ ወቅት እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ። በጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍም ቢሆን በተለይም በዋጋ ውድና በዓለም ገበያ ተፈላጊ በሆኑት ላይ ሕገወጥ ግብይቱ መስፋፋቱም በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል።
የዝግጅት ክፍላችን በዛሬው የምድር በረከት አምድ ላይ ሕገወጥ ግብይትንና የፀጥታ ስጋትን በመቋቋም እንደ ክልል እቅድን ለማሳካት ምን ተግባራት ተከናወኑ? ምንስ ውጤት ተገኘ? የሚለውን ርእሰ ጉዳይ ያነሳል። ዋንኛ ትኩረቱንም በኦሮሚያ ክልል ላይ አድርጎ ያለፉት 6 ወራትን የሥራ አፈፃፀም በመዳሰስ እንደሚከተለው አቅርበናል። መረጃውን ያደረሱን የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለሥልጣን ኃላፊ አቶ ተስፋዬ መገርሣ ናቸው።
እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ፤ የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን በበጀት አመቱ በእቅዱ ያስቀመጠው ዋና ግብ በአገራዊ ምጣኔ ሀብት ላይ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት አንዱ ሲሆን፣ ተኪ የማዕድን ውጤቶችን በማልማት የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማስቀረት ሌላው ተልዕኮው ነው። ሦስተኛው ደግሞ በዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ማድረግ ነው። እነዚህን ተልዕኮዎች ይዞ ባደረገው እንቅስቃሴ በግማሽ በጀት አመት በአንዳንድ ተግባራቱ ላይ የሚያበረታታ፣ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ደግሞ ዝቅተኛ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ተገዷል።
«በበጀት አመቱ የእቅድ ሥራ ውስጥ የፈቃድ አሰጣጥና አስተዳደር ሥራ ይገኝበታል» የሚሉት አቶ ተስፋዬ፤ የማዕድን ፈቃድ አዋጅን መሠረት በማድረግ በበጀት አመቱ በእቅድ የተያዘው ለ2ሺ115 አልሚዎች ፍቃድ ለመስጠት ነው። ባለሥልጣኑ በስድስት ወር የእቅድ ክንውንም ለ1ሺ155 አልሚዎች ፈቃድ ሰጥቷል። አፈፃፀሙም 54 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ባለሥልጣኑ የተሰጡ ፍቃዶችንም የማስተዳደር ኃላፊነት ስላለበት ፍቃድ የወሰዱ አልሚዎች በአግባቡ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን በመከታተል ውጤታማ የሆኑት ደግሞ እንዲቀጥሉ ያበረታታል። የፍቃድ እድሳትም ያከናውናል። በዚሁ መሠረትም የ144 አልሚዎችን ፈቃድ አድሷል። ምንም እንኳን ፍቃድ መሰረዝ በእቅድ የሚያዝ ተግባር ባይሆንም ወደ ልማቱ ያልገቡትን ፈቃዳቸውን በመሰረዝ ለቀጣይ ልማት ዝግጁ ማድረግ ግዴታ በመሆኑ ወደ እርምጃ ይገባል። ይህን ተግባር የሚወጣውም ለአልሚዎቹ ጊዜ ከሰጠ በኋላ ነው። በዚሁ መሠረትም በስድስት ወራት ጊዜ በባህላዊ የወርቅ ልማት የተሰማሩትን ጨምሮ በተለያየ የማዕድን ልማት ውስጥ የነበሩ 115 ፈቃዶችን ሰርዟል። ፍቃድ ከተሰረዘባቸው ውስጥ ሪፖርት ወይንም መረጃ የማያቀርቡ፣ እንዲሁም የከሰል ድንጋይ ልማት ላይ ለመሰማራት የጥናትና የምርት ፈቃድ ወስደው በስምምነታቸው መሠረት ወደ ሥራ ያልገቡ ይገኙበታል።
በማዕድን ልማቱ የተከናወኑትን ሥራዎችና የተገኘውን ገቢ በተመለከተ አቶ ተስፋዬ እንዳስረዱት፤ ባለሥልጣኑ በተለይም ለውጭ ገበያ በሚቀርቡ የማዕድን ዓይነቶች ላይ ተልዕኮዎችን (ግቦችን) ይዞ ነው ወደ ሥራ የገባው። በወርቅ ማዕድን፣ ከጌጣጌጥ ማዕድናት ደግሞ ታንታለም ይጠቀሳሉ። በበጀት አመቱ በማህበራትና በኩባንያዎች በሚከናወን የማዕድን ልማት 5ሺ685 ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት በእቅድ የያዘ ሲሆን፣ ከእቅዱ በስድስት ወር ውስጥ ተመርቶ ለብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን አንድ ሺ561 ኪሎግራም ነው። አጠቃላይ ክንውኑ 27 ነጥብ 5 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል። ይህ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበው ውጤት እጅግ የወረደ ሆኖ ነው የተገኘው። ዝቅተኛ አፈፃፀም ለመመዝገቡ ሕገወጥ ግብይትና ወርቅ አምራች በሆኑ የክልሉ አካባቢዎች እያጋጠመ ያለው የፀጥታ ችግሮች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ነው አቶ ተስፋዬ የሚያስረዱት። የክረምት ወቅት ለማዕድን ልማቱ ምቹ አለመሆንም ተጽእኖ እንዳለውና ይህም በጉጂ በሚከናወነው የደለል ወርቅ ልማት ሥራ እንደሚያጋጥም አመልክተዋል። በአሠራር የሚያጋጥሙ አንዳንድ ነገሮች (ቴክኒካል) በተመሳሳይ ጫና እንደሚያሳድር አስታውሰዋል።
መንግሥት ምንም እንኳን ባደረገው የ35 በመቶ የዋጋ ማሻሻያ መሠረት ከአልሚዎች ወርቅ እየገዛ ቢሆንም ወርቅ የሚቀበልበት ዋጋ ሕገወጥ ግብይትን ለመከላከል እንዳላስቻለው የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ፤ ወርቅን ማንኛውም ሰው በቀላሉ ይዞ ለመጓጓዝ ምቹ ሁኔታ መኖሩም ክትትልና ቁጥጥሩን ፈታኝ እንዳደረገው አመልክተዋል። በተለይም የፀጥታ ሁኔታን ተገን በማድረግ የሕገወጥነቱ አደገኛነት እየከፋ የመጣ ቢሆንም መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ሕገወጥነትን ለመከላከል ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉንም ገልጸዋል።
አቶ ተስፋዬ እንደሚያስረዱት፤ አምራቾች ምን ያህል እንደሚያመርቱ ከዚህ ቀደም እቅድ አልነበራቸውም። አመረትን ያሉትን ብቻ ነው ለብሔራዊ ባንክ ሲያቀርቡ የቆዩት። አሁን ላይ ግን በእቅድ እንዲመሩ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት በባለሥልጣኑ በኩል ተመቻችቷል። ባለስልጣኑ ይህን ሲያደርግም ለባህላዊ ወረቅ አምራቾች የሙያ ስልጠናና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን በማመቻቸት ነው። በዚህ መልኩ ምቹ ሁኔታ ከፈጠረ በኋላ በወር እስከ 200 ኪሎግራም ወርቅ ማምረት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ በመድረስ ነው በበጀት አመቱ ወደ ሥራ የተገባው። አፈጻጸሙ ከማህበራት ማህበራት የሚለያይ ቢሆንም በእቅድ መንቀሳቀሱ ግን ውጤታማ እንደሚያደርግ ታምኖበታል። ለወርቅ ልማቱ የሚያግዝ ዘመናዊ መሣሪያ (ማሽን) የሚጠቀሙ፣ ከባህላዊ የወርቅ አምራቾች በተሻለ የሚያመርቱና የምርት አቅማቸውም ከፍ ያለ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ወይንም ልዩ አነስተኛ ባለፈቃዶችን ደግሞ በተለየ ሁኔታ ልማቱን እንዲያከናውኑ አድርጓል። አልሚዎችን ሁለት ቦታ በመክፈል በወር ሦስት ኪሎግራም የሚያመርቱ ሁለተኛ ደረጃ፣ በወር ደግሞ ወደ አራት ነጥብ ስምንት ኪሎግራም ማምረት የሚጠበቅባቸውን ግልጽ በማድረግ መግባባት ላይ ተደርሶ ነው ወደ ሥራ የተገባው።
በማዕድን ልማት ሥራ የተደረገውን ጥረትና የተገኘውን ውጤት የገለጹልን አቶ ተስፋዬ፤ ከጌጣጌጥ ማዕድን ዘርፍ አንዱ የሆነው የታንታለም ማዕድንም ለሕገወጥ ገበያ የተጋለጠና በስፋትም ወደ ጎረቤት አገራት እንደሚሻገር በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ አንስተዋል። ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ የታንታለም ማዕድን ወደ ማእከላዊ ገበያ የሚመጣበት ዕድል እንዳልነበረም አስታውሰዋል። ማዕድኑ በዓለም ገበያ ተፈላጊና በዋጋም ውድ ሆኖ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ጥቅም ሳያስገኝ የቆየ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በዚህ በጀት አመት ግን በትኩረት ተሠርቶ ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ተደርጓል ብለዋል። እርሳቸው እንዳሉት ከአምራች ማህበራት ጋር በተሠራው ሥራ ከዚህ በኋላ የታንታለም ማዕድን ወደ ማዕከላዊ የሚመጣበት ሁኔታ ተመቻችቷል። በአሠራር ላይም ለውጥ ለማምጣት በተከናወነው ተግባር የታንታለም ማዕድን ጥራትን ለማረጋገጥ በግለሰብ ይከናወን የነበረውን ወደ ውጭ አገር የመላክ የአሠራር ሂደት ተሻሽሏል።
እንደ ክልል ለዓለም ገበያ ቀርበው ከተለዩ ማዕድኖች የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት በበጀት አመቱ በእቅድ ከተያዘው 394 ሚሊዮን ዶላር በስድስት ወር 127 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ በአገር ውስጥ በተከናወነ ግብይት ደግሞ ወደ 400 ሚሊዮን ብር (አራት መቶ ሚሊዮን ብር) ገቢ ለማግኘት ከተያዘው እቅድ ወደ 243 ሚሊዮን ብር በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ መሰብሰብ ተችሏል። በማዕድን ልማቱ በተለይም በወርቅ የተገኘው ውጤት ከፍ ያለ ባይሆንም በተለያየ ተግዳሮት ውስጥ አልፎ የተከናወነ በመሆኑ አበረታች እንደሆነም ተናግረዋል።
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ከውጭ ተገዝተው የሚገቡ ለግንባታና ለኢንዱስትሪ ግብአት የሚውሉ የማዕድን ውጤቶችን በአገር ውስጥ በመተካት ረገድ ተጠቃሽ ተግባር መከናወኑን አቶ ተስፋዬ አስረድተው፤ ለአብነትም ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ለኃይል ግብአትነት የሚውለውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማቅረብ እንዲቻል አልሚ ኩባንያዎች በዘርፉ እንዲሰማሩ በተሠራው ሥራ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ጭምር ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ መፍጠር መቻሉን አንስተዋል።
ባለሥልጣኑ በማዕድን ልማቱ ከ160ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ከያዘው አመታዊ እቅዱ፤ በስድስት ወራት ጊዜ ለ54ሺ760 የሥራ ዕድል መፍጠሩን አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል። ባለሥልጣኑ ከማዕድን ልማቱ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የአካባቢ ተጽእኖና ከልማቱ ቱርፋት የመጠቀም ሁኔታንም በእቅዱ ማካተቱንና በዚህ ረገድም የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አመልክተዋል።
እንደርሳቸው ማብራሪያ ለማዕድን ልማት ተብሎ ቁፋሮ የሚከናወንባቸው አካባቢዎችን መልሶ ማልማት አንዱ ተግባር በመሆኑ አንድ ማዕድን አልሚ ፍቃድ ከመውሰዱ በፊት የአካባቢና ማህበራዊ ተጽእኖዎች ላይ የሚሠራቸውን ሥራዎች በሰነድ አስደግፎ ማቅረብ እንዳለበት ቀድሞ እንዲያውቅ ይደረጋል። ከዚህ ቀደም ለማዕድን ልማት ተቆፍረው ያለሙ መኖራቸውንና በዚህ በጀት አመት 407 ሄክታር መሬት ለማልማት በባለስልጣኑ መታቀዱንና ከዚህ ውስጥም 189 ሄክታር በማልማት ወደነበረበት መመለስ መቻሉን ገልጸዋል። መሬቱን መልሶ ከማልማት በተጨማሪ ከአጠቃላይ ከማዕድን ፕሮጀክት ተሰብስቦ ለአካባቢው ማህበረሰብ ልማት የሚውል የማህበረሰብ ፈንድ አለ። የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶም ሕጋዊ ፈቃድ ወስዶ በልማቱ የተሰማራ አልሚ ከአጠቃላይ ልማቱ ከሚያገኘው ትርፍ ሁለት በመቶ ለልማቱ እንዲያውል እንደሚደረግ አስረድተዋል። በዚህ መንገድ ከአልሚው የተሰበሰበው የማህበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ልማት እንደሚከናወንበትም ተናግረዋል። እንዲህ ያለው አሠራር ከዚህ ቀደም የተለመደ እንዳልነበር ጠቅሰዋል።
እንደ አቶ ተስፋዬ፤ የማዕድን ልማት የአካባቢ ማህበረሰብ፣ የፀጥታ ኃይልና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያላሰለሰ ድጋፍና አጋርነት ይጠይቃል። ቅንጅታዊ አሠራሩ የሠመረ ሲሆን፣ የላቀ ውጤት ይመዘገባል። በዚህ መንገድ የሚከናወን የማዕድን ልማት በአልሚውና በአካባቢው ማህበረሰብ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል። መልካም ግንኙነቱ ደግሞ ማህበረሰቡ ልማቱን እንዲደግፍና ኃላፊነትም እንዲሰማው ያስችላል።
በስድስት ወር ውስጥ የታየው አፈፃፀም ለቀሪው ጊዜ ምን መሠረት ይጥላል? ወደ ልማት ያልገቡት አልሚዎችን ፍቃድ መሰረዝ ጉዳይ ተደጋግሞ የሚነሳ በመሆኑ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት ትክክለኛ አልሚ በመለየት ላይ ትኩረት መስጠት አይሻልም ወይ? በሚል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች አቶ ተስፋዬ ሲመልሱ፤ በስድስት ወር ክንውን ተንጠባጥበው የቀሩ ሥራዎችና በቀጣይ ስድስት ወራት ለመሥራት በእቅድ የተያዙትን ደምሮ መሥራት ይጠበቃል። ሥራዎችን በመፈተሽ በተሻለ ሁኔታ ለመንቀሳቀስ ነው ባለሥልጣኑ የተዘጋጀው። ከመንግሥትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋርም በቅንጅት በሚሠራው ላይም ትኩረት ይደረጋል። ከፍቃድ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ለተነሳውም አልሚው ፍላጎትና ገንዘብ ስላለው ብቻ ሳይሆን፣ በዘርፉ በቂ እውቀት እንዳለውም የሚያቀርበውን ሰነድ መነሻ በማድረግ በጥንቃቄ ማየትና ግንዛቤም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ካለፉ አሠራሮች ትምህርት በመውሰድ መሠራት እንዳለበትም ግንዛቤ በመያዙ በዚህ መንገድ በመሥራት ክፍተቱን ለመፍታት ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም