ከ20 አመት በታች እድሜ ላይ የሚገኙ አትሌቶች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በአሰላ አረንጓዴው ስቴድየም እየተካሄደ ይገኛል። ለአስራ አንደኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው ቻምፒዮና ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ባለፉት ሁለት ቀናት በርካታ የማጣሪያና የፍፃሜ ፉክክሮችን በተለያዩ ርቀቶች አስተናግዷል።
ቻምፒዮናው በመጀመሪያ ቀን ውሎው በ10ሺ ሜትር ወንዶች ተጠባቂ የፍፃሜ ውድድር ያስተናገደ ሲሆን በጠንካራ ፉክክር በታጀበው ውድድር ዘነበ አየለ ከፌደራል ማረምያ በ29:21:93 በሆነ ሰዓት አሸናፊ መሆን ችሏል። እሱን ተከትሎም አትሌት አልፎም ተስፋዬ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በ29:24:01 2ኛ ሆኖ በመጠናቀቅ የብር ሜዳለያ ሲያጠልቅ፤ አትሌት ዕድሜዓለም ታደሰ ከአማራ ፖሊስ በ29:24:54 ሰዓት በማጠናቀቅ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
በተመሳሳይ ዕለት በሴቶች አሎሎ ውርወራና በወንዶች ዲስከስ ውርወራ የፍፃሜ ውድድሮች ተካሂደዋል። በአሎሎ ውርወራው ውድድር አትሌት አማረች አለምነህ ከመቻል ስፖርት ክለብ 11.62 ሜትር በመወርወር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ስትሆን ፣ ስምረት አበበ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 10.96 ሜትር በመወርወር የብር ሜዳለያ ባለቤት ሆናለች። አትሌት ማሽላ ሙሉነህ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል 10.96 ሜትር በመወርወር የነሐስ ሜዳለያውን ወስዳለች። በወንዶች ዲስከስ ውርወራም ኢብሳ ገመቹ ከኦሮሚያ ክልል 44.96 ሜትር በመወርወር ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ በልስቲ እሼቴ ከመቻል ስፖርት ክለብ 43.74 ሜትር በመወርወር ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው የመቻል አትሌት ሀይሌ ጌትነት ደግሞ 43.12 በመወርወር ሶስተኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል።
በዲስከስ ውርወራ የውድድሩ ቻምፒዮን የሆነው አትሌት ኢብሳ ገመቹ ከውድድሩ በኋላ ለአዲስ ዘመን በሰጠው አስተያየት፣ ያስመዘገበው ውጤት በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ላይ ያለውን ጥሩ ያልሆነ አመለካከት ቀይሮ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ተግቶ እንዲሰራ እንደሚያነሳሳ ተናግሯል። አትሌት ኢብሳ ውድድሩን ለማድረግ ብዙ ጫናዎች ቢኖሩበትም ተቋቁሞ ለውጤት እንደበቃና በዚህም ደስተኛ እንደሆነ ገልጿል። “ኬንያና ዩጋንዳን የመሰሉ አገራት በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ጠንክረው በመስራት ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ፣ እኛም ትኩረት ሰጥተን ከሰራን ውጤት ማምጣት እንችላለን” የሚለው ወጣቱ አትሌት ኢብሳ ባለፈው ዓመት ታንዛንያ በተደረገ ውድድር መሳተፉንና ሁለተኛ ሆኖ ማጠናቀቁን አስታውሶ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለውድድሩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግሯል። ይህ ወጣት አትሌት ለኦሊምፒክ ሚኒማ ለማሟላት ጥቂት ሜትሮች ብቻ እንደሚቀሩትና በደንብ ከተሰራም ማሳካት እንደሚቻል አስረድቷል።
ዉድድሩ ትላናትና ቀጥሎ ሲውልም የተለያዩ የማጣሪያና የፍጻሜ ፉክክሮች ተካሂደዋል። ከነዚህም መካከል ትኩረትን በሳበው የሴቶች ሙርኩዝ ዝላይ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ውድድር ተደርጓል። ባለፈዉ ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ በዚህ ውድድር ሃዋሳ ላይ ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ በተገኙ ሁለት አትሌቶች መካከል ብቻ ነበር ውድድሩ የተካሄደው። በዘንድሮ ግን በውድድሩ ሶስት ክለቦች ስድስት ተወዳዳሪዎችን ማሳተፍ ችለዋል። ይህም ከፍተኛ ፉክክር እንዲስተናገድ ያደረገ ሲሆን፣ ሲፋን ሰለሞን ከጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ 2.40 ሜትር በመዝለል አንደኛ ሆና ማጠናቀቅ ችላለች። ደራርቱ ታምሩ ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በተመሳሳይ 2.40 ሜትር በመዝለል ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀች አትሌት ሆናለች። ሜቲ ቤካማ ደግሞ በተመሳሳይ ከጥሩነሽ አካዳሚ ሶስተኛ ሆና ውድድሩን ጨርሳለች። ትናንት በሁለቱም ጾታ ፍጻሜውን ባገኘው የ100 ሜትር ውድድር በሴቶች መቻል 1ኛ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2ኛና ኢትዮ ኤሌክትሪክ 3ኛ በመሆን ማጠናቀቅ ችለዋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ደኜ፣ የውድድሩ ዓላማ በክልሎች፣በከተማ አስተዳደሮችና በክለቦች ውስጥ የሚገኙት ወጣት አትሌቶችና አሰልጣኞች ውድድር በማድረግ ልምድ እንዲያገኙና ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል። ታዳጊ አትሌቶች ወደ ወጣት ደረጃ አድገው ውጤታቸው የሚታይበት መሆኑንም የውድድሩ ዳይሬክተር አስረድተዋል። ውድድሩ ከዕድሜ ተገቢነት አኳያ ካለፉት ውድድሮች የተሻለ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በዚህም አትሌቶችን በትክክለኛ ዕድሜ ለማሳተፍ በህክምና የታገዘ ልየታና ዶክመንቶችን የማጣራት ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። ይህ ማለት ግን የዕድሜ ማጭበርበር የለም ማለት ሳይሆን ከዚህ በፊት ከነበሩት ውድድሮች አኳያ የዘንድሮው የተሻለ መሆኑን ነው የገለጹት።
በዚህ ቻምፒዮና አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከወራት በኋላ በዛምቢያ ሉሳካ ከማዝያ 29 እስከ ግንቦት 3/2023 በሚካሄደው የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ወጣቶች ቻምፕዮና ላይ ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
በአጭር፣ መካከለኛ፣ረጅም ርቀቶች፣ እንዲሁም በሜዳ ተግባራት ውድድሮች ዘጠኝ ክልሎች፣ ሃያ አራት የአትሌቲክስ ክለቦችና አንድ ከተማ አስተዳደር በቻምፒዮናው እየተሳተፉ ይገኛሉ።በውድድሩ በአጠቃላይ 1ሺ ዘጠና አምስት ወጣት አትሌቶች ተሳታፊ ሲሆኑ፣ 635 ወንዶችና 460 ሴት አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች ተፎካካሪ ናቸው።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015