አንድ አመት ያስቆጠረው የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት በርካታ ስኬቶችን እንዲሁም ፈተናዎችን አሳይቶናል፤ እያሳየንም ይገኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የተገኙት ውጤቶች ገሚሱ በስኬት ገሚሱን ደግሞ ተግዳሮት የበዛበት ነው። በእነዚህ ስኬቶችና ተግዳሮቶች ጎልቶ የሚነሳው የወጣቶች ሚና ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ለውጡ መጣ ተብሎ የሚታመነውም በወጣቶቹ በመሆኑ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት የሚበጀን ስኬቶቹን እያነሳን መነጋገራችን ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ መልኩን እየቀየረ የሚታየውን የሰላም እጦት ላይ ትኩረት ማድረጉን ወደድን።
በአንድ አመት የለውጥ ጊዜ ውስጥ በሁም ክልሎች ማለት ይቻላል መንገራገጭ ታይቷል። በሶማሌ እና ኦሮሚያ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ፤ በአማራ እና በትግራይ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኦሮሞ እና በአማራው መካከል የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠር ለዘመናት ተከባብረው የኖሩትን ህዝቦች በማጣላት፤ አለፍ ሲልም ደም በማቃባት ጭምር ታሪክ የማይዘነጋውን ስህተት በህዝቦቹ መካከል እየፈፀሙ ይገኛሉ።
በዚህ ሂደት ህዝቡ ድርጊቱን ቢኮንንም ሰሚ አጥቷል። አባቶችም ‹‹ሀይ›› ቢሉ አመራሮቹ አንገት ደፍተው ለህዝብ ሰላምና ደህንነት መቆም ላይ አሁንም ፈቅ ያለ ነገር እየተስተዋለባቸው አይደለም። በተለይ አንዳንድ አመራሮች ችግሩን በመምራት ጭምር የአንበሳውን ድርሻ ይዘው እናገኛቸዋለን። በህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ባለው ግጭት ውስጥ ከፍተኛውን ገፈት እየቀመሰ ያለው ወጣቱ ለመሆኑ እማኝ አያስፈልገውም።
በዚህ አጭር ፅሁፍ ለመዳሰስ የሚመረው ከበርካታ ወራት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በኦሮሚያ ክልል ህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት እንዘክራለን። ችግሩን ከማስታወስ ባለፈም በማስታወስ አሁን በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተደረሰው ሁኔታ ምን ይመስላል? በወቅቱ ወጣቶች የነበራቸው ሚና እና ችግሩ የተፈታበትን ሁኔታ ለመዳሰስ ተሞክሯል።
የችግሩ ስፋት
በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ባለፉት ወራት ተከስቶ በነበረው ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል። ንብረት ወድሟል። ሰዎች ወልደው ከብደው ከኖሩበት ቀያቸው ተፈናቅለው ለከፋ ጉዳት ተዳርገዋል። በፍቅር፣ በሰላም፣ በደም ተሳስረው በኖሩ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎችም በጋራ ባደረጉት ሰፊ ጥረት ግጭቱ ረግቦ ተፈናቅለው
በመጠለያና በተለያየ አካባቢ የነበሩ የሁለቱ ክልል ህዝቦች ወደ ቀያቸው መመለስ ጀምረዋል።
የሁለቱ ክልል ህዝቦች ወደ ቀድሞ ሰላም መመለስን አስመልክቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ሰሞኑን በተካሄደ የህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረስ ተገኝተን የሚመለከተውን ታዝበናል። በኮንፈረንሱ ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ከህብረተሰቡ የተውጣጡ የሁለቱም ክልል ህዝቦች ተሳትፈዋል።
የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በኮንፈረንሱ ላይ ለውይይጥ መነሻ ባቀረቡት አጭር ጽሁፍ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የአስተዳደር ሥርአት መከተል ባልጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ ክልል ህዝቦች በአንድነት ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ባህል፣ የሽምግልና ሥርአት የሚወራረሱ፣ አንዱ የሌላውን ቋንቋ የሚናገር፣የጋራ ጠላታቸውን በጋራ የሚመክቱ አንድ ህዝቦች መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱ ተናግረዋል። ዛሬ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ግጭት ዘላቂነት እንደማይኖረውም ዶክተሩ ተናግረዋል።
ኮንፈረንሱም ውጤታማ እንደነበር ተሳታፊዎች ይናገራሉ። ወጣቶች በሰላም ኮንፈረሱ ላይ ለግርግርና ሁከት መጠቀሚያ እየሆኑ እራሳቸውንና ህዝባቸውን ለጉዳት በሚዳርግ ድርጊት ላይ ተሳታፊ የመሆናቸው ጉዳይ እና ሥራ አጥነት በተሳታፊዎች አጽንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነበር።
ከተሳታፊዎቹ መካከልም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመተከል ዞን ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ድርቤ ጉማ፣ ወጣቶቹ የማህበራዊ ድረገጽ ጥገኛ መሆናቸውን፣ በማህበራዊ ድረገጾች በሚተላለፉ አሉባልታዎች በመገፋፋት የጥፋት ድርጊት ውስጥ መግባታቸውን አንስተዋል።
በዚህም ሁኔታ ወጣቶች ፣ቄሮ፣ፋኖ እና ሌላም ሌላም እየተባለ በየአካባቢው በሚወጡ ስያሜዎች ስር ሆነው ወጣቱ መጠቀሚያ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል። ወጣቶች ሥራ አጥ መሆናቸውም ችግር ውስጥ እንዲገቡ እያደረጋቸው እንደሆነም በመግለጽ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥ ወይዘሮ ድርቤ ጠይቀዋል።
በአሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሌላው ተሳታፊ አቶ አልሄድር መሐመድ እንዳስታወቁት፣ ብዙ ወጣቶች ለጫትና ለተለያየ አደንዛዥ ዕጽ ሱስ ተጋላጭ ሆነዋል። ‹‹በደባል ሱስ የተጠመዱ ወጣቶች አይነግዱም። አይሰሩም። ቤተሰብ እያስቸገሩ ይኖራሉ። ወላጁን፣ ጎረቤቱን የሚያከብር ትውልድም እያጣን ነው። አሁን በአመራር ላይ ያላችሁ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥታችሁ ከወዲሁ ካልሰራችሁ ተተኪ የሀገር መሪ ማፍራት ካልቻላችሁ ነገ ማን ይረከባችኋል?›› በማለት ስጋታቸውን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል።
ወጣቱ ምን ይቸግረዋል?
በሰላም ኮንፈረንሱ ላይ የተገኘው ሌላው ተሳታፊ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ከተማ ነዋሪው ወጣት አብዲ በቀለ ይገኝበታል። ባለፉት በርካታ ወራት በሁለቱ ክልል ህዝቦች መካከል ተከስቶ በነበረው ችግር የተፈጠረው ነገር የሚያሳዝንና ብዙዎችንም ለጉዳት የዳረገ መሆኑን ጠቅሷል። የሁለቱ ክልል አስተዳደሮች ሰላም እንዲወርድና ህዝቦች ወደቀድሞ ኑሮአቸው እንዲመለሱ የተደረገውን ጥረት አድንቋል። ቀድሞ የነበራቸው አንድነት ተመልሶ በሰላም እንዲኖሩም ተመኝቷል። ኮንፍረንሱ መካሄዱም ለሁለቱ ህዝቦች አንድነት መጠናከር መልካም እንደሆነም ተናግሯል።‹‹ሰላም ከአንድ ወገን ብቻ አይጠበቅም፤ ከእኔና አንቺም ይጠበቃል። ሰላም ለወጣቱ፣ ለአዛውንቱ ለሁሉም ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለሰላም ዘብ መቆም አለብን›› የሚለው ወጣት አብዲ አሁን የሚስተዋለው የሰላም ችግር ከስራ ማጣት ጋር እንደሚያያዝ ይናገራል። በሁለቱ ክልሎች ያሉ አንዳንድ ወጣቶች መተዳደሪያ የሌላቸው፤ ሥራ የማይሰራ ተስፋ የቆረጠ በብዛት አለ። ስለዚህ የማይሆን ድርጊት ውስጥ ለመግባት ይገፋፋል ብሏል።
‹‹እኔ ተምሬ ስራ ባለመስራቴ እበሳጫለሁ። እስከመቼ ነው ያለሥራ የምቀመጠው ብዬም አስባለሁ።›› የሚለው ወጣት አብዲ ስራ ማጣት ችግር ቢሆንም የከፋው ጉዳይ ግን ሰላም ማጣት በመሆኑ ለሰላም ቅድሚያ መስጠትና በትኩረት መስራት ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
ወጣት አብዲ በቀለ በ‹‹ኤዱኬሽናል ፕላኒንግ ኤንድ ማኔጅመንት›› የትምህርት ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በ2009 ዓ.ም ተመርቋል።እስካሁን ሥራ አላገኘሁም የሚለው ወጣቱ ካለማንም ድጋፍ በተማረው ሙያ ሥራ አግኝቶ ቢሰራ ደስተኛ መሆኑን ይናገራል። የወጣቶች ሥራ ማጣት ችግር ሀገራዊ ቢሆንም በኦሮሚያ ግን የከፋ እንደሆነ ጠቁሟል።
እንደ ወጣት አብዲ ከከፍተኛ ትምህርት ተመርቀው ሥራ አጥ ሆነው የተቀመጡ ወጣቶች በአካባቢው ብዙ እንደሆኑ ይገልጻል። ‹‹እኔ ባካባቢዬ የማስተውለው የወጣቱ ችግር የተለያየ ነው። አንዳንዱ ቤተሰብ የለውም፤ ቤተሰብ ያለውም ቢሆን ተገቢውን የቤተሰብ ድጋፍና ፍቅር የማያገኝም አለ።ተቀጥሮ ለመስራትም የሥራ ዕድል ባለመኖሩ ዲግሪ ይዘው ሥራ ፈት የሆኑ ጥቂት አይደሉም›› ሲል አስረድቷል።
የትምህርት ዕድል ያላገኙትም ቢሆኑ በአቅማቸው ሥራ መስራት አልቻሉም የሚለው አብዲ ወጣቱ ሥራ ቢኖረው አዕምሮው መልካም ነገር ያስባል፤ ምንም አይነት ሁከትና ግርግር ውስጥም አይሳተፍም፤ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለራሱም ለሀገሩም የተሻለ እድል ሊፈጥር ይችላል በማለት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ አስረድቷል።
ወጣቱ ለደባል ሱስ ተገዥ እንደሆነና የሥነምግባር ችግርም አለበት ተብሎ በህዝብ ለህዝብ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ለተሰጠው አስተያየት ወጣት አብዲ ሙሉ ለሙሉ አይስማማም። በተወሰነው ላይ ችግር ቢኖርም ሁሉንም በአንድ መነጽር ማየት ተገቢነት የለውም ብሎ ያምናል።
ወጣቱ ድጋፍ ሳያገኝ። ‹‹ምን ይቸግርሃል›› ተብሎ ሳይጠየቅ፣ በየአካባቢው ያለውን ችግር ሳይገነዘቡ የዚህና የዚያ አካባቢ የሥነምግባር ችግር አለበት ማለት ተገቢ አስተያየት እንዳልሆነ ይገልጻል። ብዙዎችም ወጣቶቹን ሳይቀርቧቸው ሀሳብ እንደሚሰጡ ነው የተናገረው። እርሱ በምን ሁኔታ ላይ እንደሆነ ቀርቦ የጠየቀው እንደሌለ የራሱን ተሞክሮ ለአብነት ጠቅሷል።
ወጣት አብዲ እንዲህ በማለትም ለወጣቶች መልዕክት አስተላልፏል።‹‹ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ ለማስረዳትም ሆነ ያላቸውን ጥያቄ ማቅረብ ያለባቸው በሥነምግባር መሆን አለበት። እኔም ወጣት ስለሆንኩ የማደርገውን ነገር ሁሉ በሥነምግባር ነው የምፈጽመው። ሥነምግባር ቢኖረን እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም። ወጣቶች ከብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በሰላምና በፍቅር እንደሚኖሩም ተስፋ አደርጋለሁ›› ብሏል።
ወላጆችም ይጠየቁ
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሐት ካሚል በተሳታፊዎች የተሰጠውን አስተያየት መሰረት አድርገው እንደተናገሩት ችግሩ የወጣቶች ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በስነምግባር የታነጸ ዜጋን ለማፍራት ወላጆች ትልቁን ሚና ይወጣሉ። በየደረጃው ደግሞ ጎረቤት፣ የአካባቢ ማህበረሰብና መንግሥት በአዕምሮውና በሥነልቦናም መልካም የሆነ ዜጋ በማፍራት የጋራ ኃላፊነት አለባቸው።
በአጠቃላይ ወጣቶችን ለችግር መንስኤ ናቸው ማለት ብቻውን የሚፈይደው ነገር የለም። በመሆኑም ዛሬ ወቅቱ፤ ለውጡም ጭምር የወጣቶች ነው ከተባለ ከቤተሰብ ጀምሮ የስራውም የስልጣኑም ባለቤትና ዋና ተዋናይ ማድረግ ተገቢ ነው። በመሆኑም ወጣቶች ለሰላም ሰላምም ለወጣቶች ብዙ ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
በለምለም መንግሥቱ