በአልጄሪያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው 7ኛው የአፍሪካ ሻምፒዮን ሺፕ (ቻን) ተሳታፊ ከሆኑ ቡድኖች መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መሆኑ ይታወሳል:: በምድብ አንድ የተደለደሉት ዋልያዎቹ አንድ ነጥብ አስመዝግበው ከምድቡ የመጨረሻውን ደረጃ በመያዝ በጊዜ ተሰናብተዋል። ይህንንም ተከትሎ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ የስፖርት ቤተሰቡን ይቅርታ ጠይቀዋል::
በፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ አቶ ባሕሩ ጥላሁን እና በዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ መግለጫው ሲሰጥ የዋልያዎቹ አለቃ ባቀረቡት ማብራሪያ ላይ በተመዘገበው ውጤት ማዘናቸውን እና ለዚህም ኃላፊነቱን በመውሰድ ይቅርታ እንደሚጠይቁ በይፋ ተናግረዋል።
በሃገር ውስጥ ሊጎች ብቻ የሚጫወቱ ተጫዋቾች የሚካፈሉበት ይህ ውድድር እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ዋናውን ቡድናቸውን ይዘው ስለሚካፈሉ ለውጤታማነት የተሻለ ዕድል እንደሚኖራቸው ተጠብቆ ነበር። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ቡድኑ በርካታ ተጫዋቾቹን በጉዳት ምክንያት ሳያካትት እና ከ10 በላይ የሚሆኑ ወጣት ተጫዋቾችን በመያዝ ነበር ወደ አልጀርስ ያመራው:: በመጀመሪያዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ላይ መልካም እንቅስቃሴ በማሳየቱ በሊቢያው ጨዋታ ሶስት ነጥብ ለማስመዝገብ ነበር ወደ ሜዳ የገባው:: ይሁንና በጥቃቅን ጉድለቶች ሽንፈትን አስተናግዷል፤ ለዚህም ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ነው አሰልጣኙ የገለጹት:: የተጠበቀው ውጤት ባለመገኘቱም የስፖርት ቤተሰቡን ይቅርታ ጠይቀዋል::
ቡድን መገንባት ቀላል ሥራ ባይሆንም ተጠባቂ ቡድን መገንባታቸውን የጠቆሙት አሰልጣኙ፤ የግብ ዕድል በመፍጠር ረገድም ቡድኑ እየተሻሻለ መምጣቱንም ነው ያስገነዘቡት:: አሰልጣኙ እንዳብራሩት፣ በርካታ ወጣት ተጫዋቾች የውድድር ዕድል ባገኙበት በዚህ ውድድር ላይ የተሳተፈው ቡድን በአጭር ጊዜ የተገነባ ቢሆንም ከፍተኛ ተነሳሽነት ነበረው:: ስለዚህ የቡድኑን አባላት መንቀፍና ሞራላቸውን መንካት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።፡ ቡድኑን ወደ መምራት ከመጡ በኋላ በሃገራቸው አራት ጨዋታዎችን ብቻ ማድረጋቸውን ያስታወሱት አሰልጣኙ፤ የተቀሩትን ጨዋታዎች ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች አለመኖር ምክንያት ከሃገር ውጪ በማከናወን ላይ ይገኛሉ:: በመሆኑም ይህም ለውጥ መሆኑን በማመን ቡድኑን ቢያበረታና በቅርቡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከጊኒ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታም ሕዝቡ ከጎኑ ቢቆም መልካም መሆኑንም አመላክተዋል::
ዋና ፀሐፊው አቶ ባሕሩ ከውድድሩ ጋር በተገናኘ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ እንደገለጹት፣ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ሞሮኮ ለዝግጅት ተጉዞ ሁለት የልምምድ ጨዋታዎችን ያደረገው በአልጄሪያ ያለው ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ተጠንቶ ነው። ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ከምድብ ይወድቃል በሚል ጨለምተኛ ምክንያት ወደ ሀገር ቤት መመለሻው ትኬት በጊዜ አለመቆረጡን ጠቅሰውም ቡድኑ ከምድብ ከወደቀ በኋላ ግን የአውሮፕላን ትኬት ለማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁመዋል። በዚህም ልዑካን ቡድኑን በአስገዳጅ ሁኔታ በሦስት ዙር ወደ አገሩ ለመመለስ መገደዱን አመላክተዋል።
አቶ ባሕሩ አክለውም፣ ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ወቅት የመለያ እጥረት አጋጥሞት ነበር የተባለው ጉዳይ “ብሔራዊ ቡድኑ ከሞሮኮ ተነስቶ ወደ አልጀርስ ሲሄድ የትራንዚት ቆይታ ስለነበረው ሻንጣዎች ካዛብላንካ ላይ ነው የተጫኑት ፤ ሻንጣዎቹ የሚጠበቁት ደግሞ አልጀርስ ነው። በዚህ ሂደት የአራት ተጫዋቾች ሻንጣ እና ቡድኑ ከያዘው ቁሳቁስ መካከል አንድ ሻንጣ በትራንዚት ምክንያት አልመጣም። ይሄ ተለዋጭ ማሊያ ነው። እንደተወራው ፌዴሬሽኑ ያላዋቂዎች እና የሰነፎች ጥርቅም አይደለም። ቢያንስ ምክንያታዊ ሆነን ብንነጋገር ጥሩ ነበር። ይህ የተፈጠረው በትራንዚት ምክንያት ነው። ግን ቡድኑ ማሊያውን አርጎ ሲጫወት ነበር።” ብለዋል። አቶ ባሕሩ አያይዘው በተመዘገበው ውጤት እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳዘኑ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ የውድድር መድረክ ላይ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ ተካፋይ መሆኗ ይታወቃል:: ይሁንና ተሳትፎዎቿ ከምድብ ያለፉ በውጤትም የታጀቡ ሊሆኑ አልቻሉም:: በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው በዚህ ውድድር ላይም ዋልያዎቹ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የተሻለ ውጤት የማስመዝገብ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር። ለዚህም ሲባል በሃገር ውስጥ እንዲሁም የውድድሩ አዘጋጅ ከሆነችው አልጄሪያ ጋር ተቀራራቢ የአየር ሁኔታ ባላት ሞሮኮ ዝግጅት ተደርጓል። ቡድኑ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር በነበረው የልምምድ ቆይታ ከሞሮኮ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አከናውኗል። ይሁን እንጂ በውድድሩ ባከናወናቸው ጨዋታዎች ከሞዛምቢክ ጋር ያለ ግብ በመለያየት እንዲሁም በአልጄሪያ እና ሊቢያ ተሸንፎ አንድ ግብ እና አንድ ነጥብ ብቻ በማስመዝገብ በጊዜ ወደ ሃገሩ ለመመለስ ተገዷል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2015