ኪያው ሶኢኦ እና ዋ ሎኔ የተባሉት የሮይተርስ ጋዜጠኞች በማይናማር እስር ቤት እንዳሉ የክብር ሽልማት አሸናፊ መሆናቸውን ኒውስ ኤጀንሲ ዘገበ።
ጋዜጠኞቹ ለሽልማት የበቁት የማይናማር የጸጥታ ኃይሎች በሮሂንጋ ተወላጆች ላይ የፈጸሙትን የግድያ ወንጀል በቪዲዮ በተደገፈ ማስረጃ ይፋ በማድረጋቸውና የተጋረጠባቸውን አደጋ ሳይፈሩ ሙያዊ ግዴታቸውን በአግባቡ መወጣታቸውን ተከትሎ ነው።
እነዚህ ሁለት የሮይተርስ ኒውስ ኤጀንሲ ዘጋቢዎች በዋናነት ለሽልማት የበቁት በአንዲት የማይናማር መንደር የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በአስር ሰዎች ላይ የፈጸሙትን ጅምላ ግድያና መሰል ወንጀሎች ይፋ በማድረጋቸው ነው። ጋዜጠኞቹ ከአይን ምስክሮች፣ ከተጠቂ ቤተሰቦችና ወንጀሉን ፈጻሚዎች መረጃዎችን በመውስድ በስውር የተፈጸሙ የጅምላ መቃብሮችንም እያሰሱ መረጃዎችን አስተላልፈዋል።
‹‹የሮይተርስ ዋና ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ስቴቨን አድለር እንደሚያስረዳው ኪያው ሶኢኦ እና ዋ ሎኔ ባልተለመደ መንገድ ሙያዊ ግዴታቸውን ፈጽመው ለዚህ ክብር መብቃታቸው ትልቅ ደስታና
መነቃቃት ፈጥሮበታል። ለሙያ ባልደረቦቻቸውም ትልቅ አርአያ ሆነዋል። ሽልማቱም ይገባቸዋል። እንዲህ አይነት ጀግንነትን የፈፀሙ ታታሪ ጋዜጠኞች ዛሬም በእስር ቤት ከሚገጥማቸው መከራ ጋር እየተጋፈጡ መኖራቸውን ሳስብ ስቃያቸው ያስጨንቀኛል ይላል።› ሌሎችም ጓደኞቻቸው እንዲሁ ጋዜጠኞቹ በእስር ላይ በመሆናቸው ምክንያት ደስታቸውን ሙሉ ለሙሉ መግለጽ እንዳልቻሉና ከእስር ቤት ተፈትተው አጠገባቸው ቢሆኑ ኖሮ ግን ደስታውን የበለጠ ማጣጣም ይችሉ እንደነበር ተናግሯል
የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለውን ውድመትና ተከስቶ የነበረውን ረሀብና ወረርሽኝ ለዓለም ማሕበረሰብ ሲያስተላልፉ የነበሩ ጋዜጠኞችም ተመሳሳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በቱርክ ኢስታንቡል የሳዑዲ አረቢያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ጀማል ካሹጊ ለህይወቱ ሳይሳሳ የህዝብን በደል በማሰማት ለከፈለው መስዋዕትነትም የክብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆኗል።
ባለፈው ሰኞ የተካሄደው ዓለም ዓቀፍ የጋዜጠኞች የክብር ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ያበረቱ ሌሎች የሮይተርስ ጋዜጠኞችንም አካቷል። በሰበር ዜና፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት፣ በሀገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ ሪፖርተርነት፣ በፊቸር አጻጻፍ፣ በገንቢ አስተያየት ሰጪነት፣ በተቺነት፣ በርዕሰ አንቀጽ አጻጻፍና በሌሎችም ጉዳዮች ጥሩ ብቃት ላሳዩ ሙያተኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በሽልማቱ ልዩ ትኩረት ያገኙት ግን ቀደምሲል የተጠቀሱት ሁለቱ ጋዜጠኞች ነበሩ። ኪያው ሶኢኦ እና ዋ ሎኔ የማይናማር ዜግነት ያላቸው ሲሆን የሀገሪቱን ደህንነትን አደጋ ላይ ጥለዋል በሚል እ.አ.አ ታህሳስ 2017 እጃቸው ተይዞ አሁንም በማይናማር እስር ቤት ይገኛሉ። እስከ አሁንም አራት መቶ ዘጠና ቀናትን በአስር ቤት ያሳለፉ ናቸው።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
ኢያሱ መሰለ