በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ያለፉትን 30 ዓመታት በታታሪነት ያገለገለው አንጋፋው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከትናንት በስቲያ በድንገት ሕይወቱ ማለፉ ይታወሳል። በትናንትናው ዕለትም የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አባላቶች፣ በርካታ የስፖርት ቤተሰቦችና የሙያ ባልደረቦቹ በተገኙበት ስርዓተ ቀብሩ በቀጨኔ መድኃኒዓለም ተፈፅሟል።
በስፖርት ጋዜጠኝነት ከ25 ዓመታት በላይ በማገልገል በስፖርት ቤተሰቡ ተወዳጅነትን ያተረፈው አንጋፋው ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ ከ1980ዎቹ ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት ጋዜጦች እና መፅሔቶች እንዲሁም የሬድዮ ዝግጅቶች ላይ በመሥራት የሚታወቅ ሲሆን፣ የአገራችን ስፖርት የሚዲያ ትኩረት እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት ካደረጉ ምስጉን ጋዜጠኞች ግንባር ቀደሙ ነበር።
ጋዜጠኛ መሸሻ በተለይም በህትመት ውጤቶች ላይ በሚያቀርባቸው ጽሑፎች ታዋቂ የነበረ ሲሆን፤ በሻምፒዮን፣ ማራቶን፣ ግሎባል፣ ይድነቃቸው፣ ካታንጋና፣ አዲስ ስፖርት፣ ካምቦሎጆ፣ ሊግ ስፖርት፣ ሀትሪክ ስፖርት (መፅሔት ጭምር) ጋዜጦች እና በቤስት ስፖርት መፅሔት እንዲሁም በኤፍ ኤም 90.7 (ዛሚ) እና 96.3 የራዲዮ ፕሮግራሞች ላይ በመሥራት ተወዳጅነት እና ከበሬታ ያተረፈ ምስጉን ጋዜጠኛ ነበር።
አዲስ ዘመን በአንጋፋው የስፖርት ጋዜጠኛ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ኀዘን እየገለፀ ለወዳጅ ዘመዶቹ እና አድናቂዎቹ መፅናናትን ይመኛል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም