ያለፉት የሳምንቱ የዕረፍት ቀናት ከአውሮፓ እስከ አሜሪካ፣ ከኤሽያ እስከ አፍሪካ የአትሌቲክሱ ዓለም በውድድሮች ሥራ በዝቶባቸው አልፈዋል። በቤት ውስጥ፣ በጎዳና ላይ፣ በማራቶንና አገር አቋራጭ ውድድሮች በርካታ የዓለማችን ከተሞች በሳምንቱ የዕረፍት ቀናት ፉክክሮችን ያስተናገዱ ሲሆን ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም በብዙዎቹ ድል ቀንቷቸዋል።
ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በድል ከደመቁባቸው ውድድሮች አንዱ በጀርመን ካርልሹ የተካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ የዙር ውድድር ነው። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ3 ሺ ሜትር በሁለቱም ጾታ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
በሴቶች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ አምስት ተከታትለው በመግባት ውድድሩን በበላይነት አጠናቀዋል፡፡ አትሌት ለምለም ኃይሉ 8:37: 55 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና ስታጠናቅቅ፣ የ3ሺ ሜትር መሰናክል የዓለም ቻምፒዮና የብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ አትሌት ወርቅውሃ ጌታቸው 8:37:98 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆናለች። አትሌት ዳዊት ስዩም 8:39:20 ርቀቱን በማጠናቀቅ ሦስተኛ ሆና ጨርሳለች። አትሌት ሚዛን ዓለም እና አትሌት ዘርፌ ወንድማገኝ አራተኛና አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ በወንዶች 3 ሺ ሜትር ውድድር አትሌት አብዲሳ ፈይሳ በ7:40:35 አሸናፊ ሲሆን የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር ነው። ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት አዲሱ ግርማ 7:41:53 በመግባት ሦስተኛ ደረጃን ይዞ እንዳጠናቀቀ የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመለክታል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ሌላኛው ተጠባቂ ውድድር በጃፓን ኦሳካ የተካሄደው የሴቶች ብቻ ማራቶን ሲሆን የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሄቨን ኃይሉ ድል ቀንቷታል። ሄቨን ውድድሩን ስታሸንፍ 2:21:13 ሰዓት ያስመዘገበች ሲሆን፣ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መሠረት ጎላ በ2:22:12 ሰዓት ሁለተኛ ሆና አጠናቃለች። ጃፓናዊቷ ዩካ አንዶ 2:22:59 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆና ውድድሩን የፈጸመች አትሌት ሆናለች።
ተጠባቂ በነበረው የሞሮኮ ማራኬሽ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም በወንዶች ድል ባይቀናቸውም በሴቶች ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ጠጅነሽ ገቢሳ 2:27:46 በማጠናቀቅ ሁለተኛ የሆነች አትሌት ናት። ውብአለም አየለ በ2:29:01 እና ትንቢት ግደይ በ2:30:09 ሦስተኛና አራተኛ ሆነው ውድድሩን ያጠናቀቁ አትሌቶች ናቸው።
በታይላንድ የተካሄደውን የኮን ኬይን ማራቶን በወንዶች ኬንያዊው አትሌት ፖል ኢያኔ በ2:15:24 ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ከሁለት እስከ ስድስት ያለውን ደረጃ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተቆጣጥረውታል። በዚህም ኤቢሳ ታከለ 2:15:27፣ደጀኔ ኃይሌ 2:15:48፣ ወንድወሰን ጥላሁን 2:16:19፣ተሾመ ጌታቸው 2:17:21 ተከታትለው የገቡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሆነዋል።
በተመሳሳይ የሴቶች ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ዝናሽወርቅ የኔው 2:49:04 በሆነ ሰዓት ድል የቀናት አትሌት ስትሆን ሩሲያዊቷ አትሌት አሌግዛንድራ ሞሮዞቫ 2:49:15 በማጠናቀቅ ሁለተኛ ሆናለች። ሌሊሴ ቢሮና አለምፀሐይ አድባሩ ሦስተኛና አራተኛ ሆነው ያጠናቀቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በስፔን ሲቪያ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ውድድር ደግሞ ኢትዮጵያዊው አትሌት አምደወርቅ ዋለልኝ 1:00:28 በሆነ ሰዓት አሸናፊ ሲሆን በሴቶች ኢትዮጵያውያን የሜዳሊያ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ አልቻሉም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም