ከ44 ዓመት በፊት ጥር ወር ላይ የታተሙ ጋዜጦችን ለዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን መርጠናል። በወቅቱ በዘነበ ዝናብና በተከሰተ መብረቅ በተለያዩ አካባቢዎች በሰዎችና በእንስሳት ላይ ጉዳት ደርሶ ነበር። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በፊት ገጽ ላይ ብታምኑም ባታምኑም በሚል ዓመድ ሥር ባወጣው ዘገባም ፤አንድ ፈረንሳዊ በአፍላ ዕድሜው ታስሮ የዕድሜውን እጥፍ እስር ቤት ቆይቶ እንዲፈታ ተወሰነ፡፤ ሆኖም በወቅቱ በተከሰተ ጦርነት ተረስቶ በእስር ሊቆይ ተገደደ።በመጨረሻ ግን በእርጅና ዘመኑ ተፈታ ይለናል።ሌሎች ግርምትን የሚፈጥሩ የቆዩ ዘገባዎችንም ለትውስታ አካተን እንደሚከተለው አቅርበናል።
መብረቅ ጉዳት አደረሰ
አሰላ፤ (ኢ-ዜ-አ-) በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በጭላሉ አውራጃ በበቆጂ ወረዳ ፋሪቾ በተባለው ቀበሌ ባለፈው ሳምንት ውስጥ በጣለው ኃይለኛ ዝናብ የጣለው መብረቅ የሁለት ሴቶች ሕይወት አጠፋ ።
በዚሁ የመብረቅ አደጋ የሞቱት ሰዎች እመት ወርቂቱ ሰንበታና እመት ዲቦ ዋዩ የተባሉ ሴቶች ናቸው።
ጎሬ ፤(ኢ-ዜ-አ-) በኃሎ ሐሙማ ምክትል ወረዳ በተራ በተባለው ቀበሌ ሰሞኑን በዘነበው ዝናብ የጣለው መብረቅ የአቶ አየለ ቱራ ንብረት የሆኑትን ፪ የቀንድ ከብቶች ገደለ። በዚሁ የመብረቅ አደጋ በሰውና በለሌላ ንብረት ላይ አንዳች ጉዳት ያልደረሰ መሆኑን ምክትል ወረዳ ገዥው መምሬ ዓለማየሁ ኪዳነ ወልድ ገለጡ።የኃሎ ሐሙማ ወረዳ ግዛት የሚገኘው በኢሉባቡር ጠቅላይ ግዛት በጎሬ አውራጃ በዓሉ ወረዳ ነው። (ጥር 1 ቀን 1961 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ያለ ፈቃድ ቤት የሠሩ ፳፮ ሰዎች ፰፻ ብር ተቀጡ
(ከአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)፤
ያለ ማዘጋጃ ቤት ፈቃድ የከተማይቱን ፕላን ሳይጠብቁ እንደፈለጋቸው በአዲስ አበባ ከተማ ክልል ውስጥ ያለፈቃድ ቤት ሠርተው በመገኘታቸው ፤በፈጸሙት ወንጀል በማዘጋጃ ቤቱ ነገረፈጅ ከተከሰሱት ተከሳሾች ውስጥ ፳፮ቱ አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው ፤ላደረጉት ጉድለት ፰፻ ብር ተቀጥተው የሠሩት ቤት እንዲፈርስ የተፈረደባቸው መሆኑ ታውቋል።
የቤታቸው ግምት የሚጠይቁት መጀመሪያውኑ ቤቱ በሕጋዊ ፈቃድ የከተማውን ጠቅላላ አቀማመጥና ሥሪት ያወቀና በጠቅላላው በፈቃድ የሠራ ሆኖ ሲገኝ ነው። በአሁኑ ጊዜ ያለ ፈቃድ የሚሠሩ ቤቶች ያለግምት ከመፍረሳቸውም በላይ ፤ ባለንብረት በሕግ ፊት ቀርቦ ተገቢ መቀጫ ይቀጣል።
በድብቅ ተሠርቶ ሳይታይ ቢቆይ እንኳ ቤቱ የተሠራበትን ፈቃድ ካላቀረበ በቀር ፤ የወሀ መሥመር ከመከልከሉም ሌላ ፤ የሚሰጠውን አገልግሎት የሚያቋርጥ በመሆኑ ፤ ማናቸውም ቤተ ሠሪ ቤቱን ከመጀመሩ በፊት ሕጋዊ ፈቃድ እንዲኖረው ያስፈልጋል።
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚሠሩት ቤቶች ሁሉ ለከተማው ውበትና ለኗሪዎችም ምቾትና ጥቅም እንዲያስገኝ በማሰብ ቤቶችና አጥሮችም ጭምር በተደረገው ዘመናዊ ጥናት ተከትለው እንዲሠሩ ያደረገውና የሚያደርገውም በዚሁ ፕላን መሠረት ነው።በዚሁ ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ በ፲፱፻፶፭ ዓ-ም- እስከ ፲፱፻፷ ዓ-ም- ማለት በ፭ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፫ሺህ ፪፻፳፩ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ፩፻፳፰ ታላላቅ ፎቆች፤ ፫፻፯ የንግድ ሱቆች ፤ ፳፩ ኢንዱስትሪዎች ፤፲፪ ትምህርት ቤቶች ፤፲፮ የነዳጅ ማደያዎች ፤በጠቅላላው ለ፭ሺ ፰፻፷፩ ፈቃድ ጠያቂዎች ፈቃድ ተሰጥቷቸው ሲሠሩ ፤፩፻፸፫ ቤቶች በፈቃድ እንዲታደሱ ተደርገዋል።
ስለዚህ ያለ ፈቃድ የሚሠሩት ቤቶችና በየዓመቱ በሕጋዊ ፈቃድ የሚሠሩት ሲማዘን ፤በመቶ ሁለት በፈቃድ የሚሠሩት ይበልጣል። ይህም የሚያሳየው ቤትን በፕላን ፤ወይም በፈቃድ መሥራት ምን ዓይነት ጥቅም እንዳለው ቤተ ሠሪዎች እየተረዱት መሔዳቸውን ይገልጣል።
ቢሆንም ይህንን ያልተረዱት አንዳንድ ቢኖሩ ፤እንዲረዱልንና በራሳቸው ላይ የሚደርሰውን ኪሣራ ተገንዝበው ከዚሁ አጉል ተግባር እንዲርቁ አደራ እንላለን ሲል ከማዘጋጃ ቤት ፕሬስ ክፍል የተገኘው ዜና ያስረዳል። (ጥር 7 ቀን 1961 ከታተመው አዲስ ዘመን)
ብታምኑም ባታምኑም በእስር ቤት ስለተረሳው ሰው
ማርከስ ደ-ፒለር የተባለ ፈረንሳዊ ሰው በንግሥቲቱ አፏጭተሃል በመባል ተከስሶ በ፲፯፻፹፮ ዓ-ም- ወደ እስር ቤት ተላከ። ፒለር በዚያን ጊዜ ፤ ወደ አስር ቤት ሲላክ የ፳፪ ዓመት ወጣት ነበር። ፐሊር በአንድ ቦታ ፬ ዓመት ያህል በእግር ብረት ታስሮ ከቆየ በኋላ ፤ ወደ ሌላ እስር ቤት በምስጢር ተዛውሮ ፤ወዲያው የመንግሥታት ለውጥ ሆነና የአዲሱ መንግሥት ሕግ የፐሊርን መፈታትም፤ ሆነ መታሰር ሳይደግፈው ቀረና እንደገናም የርሱ ጉዳይ እስኪታይ ድረስ ፳፬ ዓመት ታሰረ። ከዚያም የናፖሊዮን ዘመነ መንግሥት መጣና የፐሊር ጉዳይ ታይቶ ወዲያው እንዲለቀቅ ሲታዘዝ ፤በመሐሉ ጦርነት ተነሳና የፐሊር ጉዳይ አሁንም ተረሳ ።ያፏጨባት ንግሥት ከሞተች ፵፫ ዓመቷ አልፏል።
በመጨረሻም በ፳፪ ዓመቱ እስር ቤት የገባው ወጣት፤ነገሥታት ሲፈራረቁ የምስኪኑም ጉዳይ እየተረሳ በእግር ብረት ታስሮ ከ፩ መቀመጫ ሳይነቃነቅ አምሳ ዓመት ሙሉ ከታሰረ በኋላ ፤እግዚአብሔር በቃህ ሲለው የ፸፪ ዓመት ሽማግሌ ሆኖ በ፲፰፻፴፮ ዓ-ም- ከእስር ቤት ዓለም ወጣ።
ሴኔጋልና ጊኒ ከዓለም ሁሉ ልዩና እንግዳ የሆነ የባልና ሚስት መፋታት ሕግ ነበራቸው ። እሱም መጀመሪያ ባልና ሚስት ሲጋቡ ፤ባል ለሚስት ፩/ ልብስ ይሰጣታል። ይህም ልብስ ሲያልቅ የባልና የሚስትነታቸው ዘመን ያበቃል ይላሉ። ኑሯቸው አስደሳች ከሆነ ሚስትየዋ የተሰጣትን ልብስ በጥንቃቄ እየያዘች ቶሎ እንዳያልቅ በማለት አንዳንድ ጊዜ እንድትለብሰው ይደረጋል። ለመፋታት ሀሳብ ያላቸው ግን ልብሱ ቶሎ እንዲያልቅና ተፋትተው እንዲያርፉ ያለ ቅያሬ ትለብሰዋለች ። ከዚያም የልብሱም ክር ከታየ ወዲያው ባልና ሚስት ይፋታሉ ይባላል። (ጥር 1 ቀን 1961 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም