የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ አገልግሎቶችን ማዳረስ የተቋማት ትልቅ ፈተና መሆን ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከትራንስፖርት እና ከመኖሪያ ቤት ችግር በተጨማሪ የመጠጥ ውሃ የሚገኘው በሳምንት ለአንድ እና ለሁለት ቀን እንዲያውም አንዳንዴም ሳምንት እየዘለለ በ15 ቀን የሚዳረስ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። በተቃራኒው ማንም ሊክደው በማይችል መልኩ የከተማዋ የሕዝብ ቁጥር ጨምሮ ባለበት ሁኔታ ውስጥ የኤሌክትሪክ መቋረጥ ችግር እየተቃለለ ስለመሆኑ ነዋሪዎች በመግለፅ ላይ ናቸው።
ቀደም ሲል ግን የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ የተዳረሰ ነው ቢባልም የኃይል መቆራረጥና በተራ በሳምንት ለአንድ እና ለሁለት ቀን ኤሌክትሪክ ኃይል ሙሉ ለሙሉ የሚቋረጥባቸው ጊዜያት ነበሩ። በመላ አገሪቱ ከሚመረተው ኃይል ግማሽ ያህሉን የምትጠቀመው አዲስ አበባ ብዙ ትልልቅ ፋብሪካዎች እና ብዛት ያለው ኢንዱስትሪ የሚገኝባት እንደመሆኗ የኃይል መቆራረጥ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል አይሆንም። አሁን ላይ ይህ ችግር በከፍተኛ መጠን ተቃልሏል። ይህ ችግር እንዴት ተቃለለ? የተቃለለው በጊዜያዊነት ነው ወይስ ለዘለቄታው? በአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ክፍሌ የሚሉት አላቸው።
አቶ በቀለ እንደሚገልፁት፤ የአዲስ አበባ የኤሌክትሪክ ሽፋን መቶ በመቶ ከደረሰ ብዙ ዘመናት ተቆጥረዋል። አሁንም ማንኛውም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት እና ቆጣሪ ማስገባት የሚፈልግ ግለሰብ ማስገባት ይችላል። አሁን ላይ በኤሌክትሪክ አገልግሎት በኩል የከተማ ሕዝብ ቁጥር መጨመርም ሆነ የፍላጎት ማደግ ስጋት አይደለም። ምክንያቱም የሕዝቡን ፍላጎት ያማከለ ኔትወርክ መዘርጋት አስቀድሞ ታስቦበት ተሠርቷል።
በፊት ከማመንጫ ጀምሮ ማከፋፈያ ጣቢያ እና ስርጭቱም ላይ ችግር ነበር። ማመንጫ እና ማከፋፈያው በጥሩ ሁኔታ ተገንብቶም ስርጭቱ ላይ ግን ችግር ነበር። አሁን ግን ስርጭቱ ላይም በኮንክሪት ኬብል እየተዘረጋ የማሻሻል ሥራ በመሠራቱ የሚቆራረጥበት ሁኔታ ቀንሷል።
ሌላው አጋዥ ትራንስፎርመር በማስቀመጥ እና አቅሙን በማሳደግ ‹‹አገልግሎት እየተቆራረጠብን ነው›› የሚል የሕዝብን ቅሬታ ለመቀነስ ተችሏል ይላሉ ሥራ አስኪያጁ። ሙሉ ለሙሉ ችግሮች የሉም ማለት ባይቻልም የባሰውን ችግር ማቃለል የተቻለ መሆኑንም ይናገራሉ።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ማብራሪያ ኤሌክትሪክ የሚገዛው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ነው። እነርሱ ያመነጩትን ኃይል ሲሸጡ፤ የአገልግሎት ተቋሙ ደግሞ ገዝቶ ለኅብረተሰቡ ያደርሳል። በፊትም መቆራረጥ የነበረው በኃይል እጥረት ሳይሆን ስርጭቱ ላይ የኅብረተሰቡን የኃይል ፍላጎት ኔትወርኩ ሊሸከመው ባለመቻሉ ነው። ስለዚህ ከትልልቅ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ዲስትሪክቶች በራሳቸው ግንባታ ይሠራሉ። ዋናውን የመቆራረጥ ችግር ለማስቀረት በጥሩ ሁኔታ እየተሠራ ነው።
በዘለቄታው ችግር እንዳይኖር ማድረግን በተመለከተ ግን ፕሮጀክት ተቀርፆ እየተሠራ ሲሆን፤ ግፋ ቢል ከሦስት ዓመት በኋላ አዲስ አበባ ላይ ምንም ዓይነት መቆራረጥ የማያጋጥምበት ሁኔታ ይፈጠራል ይላሉ አቶ በቀለ። አሁን መካከለኛ ቮልቴጅ የሆኑትን በተደጋጋሚ ኃይል የሚቋረጥባቸው አካባቢዎች ላይ ቅድሚያ እየተሰጠ ያለው ለዚሁ ነው የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ዲስትሪክቶቹ በዚህ ላይ ያተኮሩት መፍትሔ ለማምጣት መሆኑንም ያብራራሉ።
አቶ በቀለ እንደሚያስረዱት፤ በሌላ በኩል ቀደም ሲል ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ የተቋረጠበትን መስመር መለየት በራሱ ትልቅ ችግር ነበር። አሁን ግን ኢንዲኬተር ስካዳር ሲስተም እየተሠራ ነው። በአዲሱ ፕሮጀክት ኤሌክትሪክ ሲቋረጥ የት ቦታ እንደተቋረጠ ወዲያው ቢሮ ላይ ይታወቃል፤ በሬዲዮ እዚህ ጋር ተቋርጧል ተብሎ ለጥገና ቡድኑ ይነገራል፤ ቡድኑ ሔዶ ይጠግናል። ስለዚህ በዋናነት ይህ ስካዳር ሲስተም ትልቅ መፍትሔ አስገኝቷል።
በተጨማሪ የቻይና እና የፈረንሳይ ካምፓኒዎች የገጠሟቸው ሲስተሞች አሉ፤ አራቱም ዲስትሪክቶች ላይ ያሉት የኦፕሬሽን ክፍሎች ሙሉ ብልሽት ካልሆነ በስተቀር፤ ኃይል ሲቋረጥ ለጥገና እንደበፊቱ ሙሉ መስመሩን ማቋረጥ የለም። የሚያቋርጡት የተወሰነውን ነው። ከዚያ ከጥገና በኋላ ወዲያው ያያይዙታል፤ ይህንን ሲስተም መጠቀሙ በራሱ መፍትሔ ያስገኘ መሆኑንም ያስረዳሉ።
ፍላጎት ሲጨምር በቂ ኃይል በመኖሩ በአካባቢው ያለውን ኔትወርክ የሚመጣውን ጭነት መሸከም እንዲችል ማድረግ ብቻ ነው። ከዚያ ውጪ እንደውም ኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ደንበኞች ቆጣሪ ማግኘት ትችላላችሁ እየተባሉ ደንበኞች እንዲበዙ በመሠራት ላይ መሆኑንም ያመለክታሉ።
በእርግጥ የኃይል ማመንጫ አካባቢ ችግር ሲመጣ አጠቃላይ መረበሽ ይኖራል። ባለፈው ሰበታ አካባቢ እንዳጋጠመው የትራንስፎርመር መቃጠል ሲያጋጥም፤ መስመር ላይ ችግር ይፈጥራል። ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ወደ ሌላ የማበዳደር ሥራ ሲሠራ ሰዎች ይቸገራሉ፤ ኃይል ይቋረጣል የሚሉት አቶ በቀለ፤ አንዳንዴ ከኃይል ሻጩ መስሪያ ቤት ጋር ባለ ችግርም ይቋረጥ እንደነበር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው እንደገለፁት፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መቋረጥ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ኅብረተሰቡን ሊያማርር እንደሚችል አያጠያይቅም። በዚህ በኩል ያለውን ችግር መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው? በሚል በመስሪያ ቤቱ ራሱን የቻለ ጥናት ተካሂዷል።
በጥናቱ የኃይል አምራች መስሪያ ቤቱ የሚያስተዳድራቸው አዲስ አበባ ላይ ያሉ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅማቸውን የማጥናት እና የመለየት ሥራ ተሠርቷል። ለምሳሌ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንዳንዶቹ የሞሉ እና ከዚያ በላይ ኃይል የማያስተናግዱ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ታውቀዋል። ስለዚህ እነዛን የማከፋፈያ ጣቢያዎች እቅማቸውን የማሳደግ፤ ትራንስፎርመር መጨመር እና መታደስ የሚፈልጉትን የማደስ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ተሠርቷል ይላሉ። በዚህ መሠረት አዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ያሉ ወደ ስምንት ትልልቅ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ትራንስፎርመር ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ኃይል ለማውጣት የወጪ መስመሮችን ብዛት የመጨመር ሥራም እንደተሠራ አስታውሰው፤ የወጪ መስመሩ ቁጥሩ ጨመረ ማለት በአንድ አካባቢ ላይ በሚሔደው መስመር የሚጠቀሙ ደንበኞች ያገኙ የነበረው ኃይል ወደ ሁለት እና ወደ ሦስት የተለያዩ መስመሮች በሚከፋፈልበት ጊዜ አንዱ መስመር ያለምንም ችግር አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
እነዚህ የማሻሻያ ሥራዎች የተሻለ ኃይል ማቅረብ እንዲቻል አግዘዋል። በተጨማሪ መስመሮቹን ወይም የማከፋፈያ ጣቢያዎቹን ዝግጁ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከማመንጨት ጀምሮ አጓጉዞ ማከፋፈያ ጣቢያ የማድረስ ሥራ የኃይል አምራች መስሪያ ቤቱ ሥራ ሲሆን ከማመንጨት ጀምሮ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ትኩረት ተደርጎ ተሠርቷል ይላሉ።
እንደአቶ ሞገስ ገለፃ፤ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ከፍተኛ ኃይል የሚፈልጉ መሆኑ ስለሚታወቅ፤ የሚፈለገውን ኃይል በእርግጥ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የአገሪቱ ከተሞች ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ኃይል ለማቅረብ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን አቅማቸው ከፍ እንዲል የማድረግ ሥራ ተሠርቷል።
ከተሠሩ ሥራዎች መካከል በብልሽትና በተለያዩ ምክንያቶች ቆመው የነበሩ ዩኒቶች ሥራ እንዲጀምሩ ማድረግ ተችሏል የሚሉት አቶ ሞገስ፤ ሥራ የጀመሩ ዩኒቶች የማመንጨት አቅም መጨመሩን፤ የማመንጨት አቅማቸውን ቀንሰው የነበሩ ዩኒቶች ተጨማሪ ኃይል ማመንጨት የሚችሉበት ዕድል መፈጠሩን፤ ይህም ወደ ግሪድ የሚገባውን የኃይል መጠን ከፍ እንዲል ማድረጉን፤ የሚመነጨው የኃይል መጠን ሲጨምርም እጥረት እንደሚቀንስ የተናገሩ ሲሆን፤ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አቅም ማደጋቸውና የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች መሠራታቸው ለችግሩ መቀረፍ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውንም አስረድተዋል።
በአገልግሎት ሰጪ መስሪያ ቤቱ የሚያጋጥመው ችግር ተመልሶ በኃይል ድርጅቱ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ችግር ፈጥሮ የአንድ ወጪ መስመር ችግር በአጠቃላይ ከኃይል ማከፋፈያው ላይ ኃይል የሚያገኙትን በሙሉ እንዳይጎዳ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች መወሰድ ስላለባቸው በዚያ መንገድ የተጀማመሩ ርምጃዎች መኖራቸውንም የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ሞገስ ያስረዳሉ።
በዌብ ሳይት ላይ ተመስርቶ ብልሽት ሲያጋጥም ለሚያጋጥመው ብልሽት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሶፍትዌር በልፅጓል። ለምሳሌ በሜክሲኮ ያለው የማከፋፈያ ጣቢያው ላይ ካሉት ወጪ መስመሮች አንደኛው ወጪ መስመር ቢበላሽ ሶፍት ዌሩ የተበላሸውን ለይቶ በዚህ ቦታ ላይ ይሔ ብልሽት ለዚህን ያህል ደቂቃ አጋጥሟል ይላል። ስለዚህ እንደዚህ ዓይነት ብልሽቶች ሲያጋጥሙ ሶፍት ዌሩ የሚያገለግለው ለኃይል አቅራቢው ብቻ ሳይሆን ለአገልግሎት ዘርፉም በመሆኑ በተደጋጋሚ ኃይል እንዳይቆረጥ በማድረግ የጠቀመ መሆኑንም ያስገነዝባሉ።
ሶፍትዌሩ ሁለቱ ድርጅቶች በሚኖራቸው ግንኙነት የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችልበትን ሁኔታ ለመፍጠር በመሆኑ፤ ተደጋጋሚ ችግር የሚያጋጥምበትን አካባቢ ለይተው መፍትሔ ማምጣት እንዲችሉ የማድረግ የእገዛ ሥራ የኃይል አቅራቢ መስሪያ ቤቱ መሥራቱን እና አሁን ላለው የተሻለ አገልግሎት የራሱን ሚና መጫወቱንም አብራርተዋል።
እንደአቶ ሞገስ ገለፃ፤ የሁለቱ ተቋማት በተለይ ኦፕሬሽኑን የሚመሩት በኃይል መስሪያ ቤቱ በኩል የማከፋፈያ እና የማስተላለፊያ ጣቢያዎች ኦፕሬተሮች ዘርፍ ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ የሥርጭት ዘርፍ ጋር በቅርበት ይሠራሉ። ይህም በበኩሉ በቅርበት መስራታቸው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት እና በጋራ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚያግዝ መሆኑ በራሱ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ከሁሉም በላይ ግን የትኛውም ሰው ሊያስተውለው በሚችል መልኩ በተለይም በበዓላት ሰሞን ከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ያለበት እና ኢንዱስትሪዎችም የኃይል ፍላጎታቸው ከነዋሪው ፍላጎት ጋር አብሮ የሚያድግበት ሁኔታ መኖሩን በማስታወስ፤ የኃይል አመንጪውም ከዚህም በላይ ፍላጎት ቢመጣ ሊያሟላ የሚችል ተጨማሪ መጠባበቂያ የመያዝ ሥራዎችን ከአገልግሎት ሰጪው መስሪያ ቤት ጋር እየተናበቡ ሲሠሩ ስለነበር ችግሮች ሊቀረፉ የቻሉት በእነዚህም ምክንያቶች ጭምር መሆኑንም ያብራራሉ።
በዋናነት አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ትልልቅ ከተሞች ያለው የኃይል ፍላጎት አዝማሚያው ተለይቷል። ወደ ፊትም በምን ያህል መጠን ሊያድግ ይችላል? ይሔን እያደገ ሊሔድ የሚችለውን ፍላጎት የምናሟላው እንዴት ነው? የሚሉ መረጃዎች ተሰብስበው ትንተና ተሠርቷል የሚሉት አቶ ሞገስ፤ በዚህ ትንተና መሠረት የከተማዋን ብቻ ሳይሆን የመላ አገሪቱን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ምን ያህል ኃይል ማመንጨት ይጠበቅብናል? ምን ያህል የማከፋፈያ ጣቢያዎች ሊኖሩን ይገባል? የማስተላለፊያ መስመሮቻችን አቅም ምን ያህል መሆን አለበት? የሚሉ ዝርዝር ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በዚያ መሠረት አብሮ ያደገ ሥራ ለመሥራት በተቻለ መጠን ጥረት እየተደረገ ነው የሚሉት ኃላፊው በአማካኝ በየዓመቱ 14 እና 15 በመቶ እያደገ የሚመጣ ፍላጎት መኖሩን እና ኢኮኖሚው እያደገ እና ሥራ የሚፈልገው ወጣት ቁጥር ደግሞ ሲጨምር በየጊዜው እያደገ የሚሔደውን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ሥራ ሳይቋረጥ መሠራት እንዳለበትም ተናግረዋል። ይህ ካልተደረገ፣ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እንደነበረው ወደ ፈረቃ ሥርዓት መግባት ግዴታ ይሆናል። ኢኮኖሚውን መደገፍ ሲገባ ለኢኮኖሚው የሚፈልገውን ኃይል ባለማቅረብ ችግሮች እንዲከሰቱ የማድረግ ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል ሲሉም ነው በዘርፉ ብዙ መሥራት የሚገባ መሆኑን የተናገሩት።
አቶ ሞገስ ይህ እንዳይሆን ያንን አስቀድሞ ሊፈታ የሚችል ተጓዳኝ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ በዚህ መንገድ ከተማዋን ጨምሮ በመላው አገሪቱ እያደገ የሚሔደውን ፍላጎት ለማቅረብ የማስተላለፊያ መስመር፤ በተለይ የኃይል አቅራቢ መስሪያ ቤቱን የሚመለከቱ የከፍተኛ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች አንዳንዶቹ ከዚህ በኋላ የሚመጣውንም ኃይል ለማስተናገድ በሚያስችል መንገድ ዝግጁ ሆነዋል ብለዋል። ምክንያቱም አስቀድሞ የማስፋፊያ እና የዓቅም ማሳደግ ሥራ የተሠራባቸው መሆኑንም አስታውሰዋል።
አሁንም አገልግሎት ሰጪው መስሪያ ቤት ያልተጠቀመባቸው ያለ ሥራ የተቀመጠ አቅም መኖሩን ከጠቆሙ በኋላ፤ ከዚህ በኋላም ለተወሰኑ ዓመታት የኃይል ፍላጎቱ እየጨመረ ቢሔድ ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም መኖሩን አመልክተዋል። ነገር ግን እነዚህ የማስተላለፊያ ጣቢያዎች እና ወጪ መስመሮች ዝግጁ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ ለዚህ ዝግጁ ለሆነው መስመር የሥርጭት መስመሩ ደግሞ በአገልግሎቱ በኩል መሟላት አለበት ብለዋል።
አገልግሎቱ ከዚህ ጋር አብሮ የሚሔድ የስርጭት መስመሮችን አቅም የማሳደግ እና የማስፋፋት ተጨማሪ ግንባታዎችን የማድረግ ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የማይሠራ ከሆነ ግን፣ ሁለቱ ተቋማት እየሠሩት ያለው ሥራ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል አይደለም። ስለዚህ አብሮ የሚሔድ ሥራ መሠራት አለበት ብሎ በማመን ንግግር እየተደረገ ነው። ሥራ ያልተሠራባቸው እና ያልተጠቀሙባቸው ጣቢያዎች ላይ እንዲሠሩ ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን፤ እነርሱም የሥርጭት መስመሮቻቸውን አቅም የማሳደግ እና የማስፋፋት ሥራ ይሠራሉ ተብሎ የሚጠበቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም