ከረጅም ርቀት የአትሌቲክስ ውድድር ጀግኖች መካከል ሀይሌ ገ/ስላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ እና ሌሎችም በእሱ ስር ሰልጥነው ነው ያለፉት። ከቅርብ ጊዜዎቹ ደግሞ ማሬ ዲባባ፣ ሰሎሞን ባረጋ፣ በሪሁ አረጋዊ፣ መቅደስ አበበ፣ ድርቤ ወልተጂ፣ ሰንበሬ ተፈሪ እና ሌሎችም የዚህ ሰው ስልጠና ተቋዳሽ በመሆን ላይ ከሚገኙት ምርጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል በጥቂቱ ተጠቃሾች ናቸው። ሰውዬው ዝነኛው የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ ነው።
የ56 ዓመቱ ጎልማሳ ወደ አትሌቲክስ አሰልጣኝነት ሙያ የገባው ከ30 ዓመታት በፊት ነው። የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን በስድስት የኦሊምፒክ እና በ25 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ በአሰልጣኝነት መርቷል። በስድስት የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ላይ ተካፍሏል። በበርካታ የቤት ውስጥ ውድድሮች ላይ አትሌቶቹን የመራ ሲሆን በ10 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ላይም ከፊት ሆኖ ቡድኑን መርቷል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በእሱ አሰልጣኝነት በታላላቅ ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ከ370 በላይ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች። ይህ አስገራሚ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚያስገርም ስኬት ነው። በዚህም የተነሳ ታላላቅ የውጭ አገር መገናኛ ብዙሃን “The Medals Predator” (“ሜዳሊያ አዳኙ”) የሚል ቅፅል ስም አውጥተውለታል።
“ወደ አትሌቲክስ አሰልጣኝነት የገባሁት ገና የ25 ዓመት ወጣት ሳለሁኝ ነው። ወደ ጦር ሰራዊት ቤት መግባቴ ከአትሌቲክስ ጋር እንድተዋወቅ መንገዱን ከፍቶልኛል። እስካሁንም ድረስ የማፈቅረውን ስራ እየሰራሁ በመኖሬ በጣም ደስተኛ ነኝ። በርካታ ታላላቅ አትሌቶች በእኔ ስር ያለፉ ናቸው። ዛሬ የደረሱበትን ቦታ ስመለከት በጣም ነው የምደሰተው” ይላል ከከዋክብት አትሌቶች ጀርባ የሚገኘው ብርቱ ሰው። “ከአትሌቲክስ የተሻለ ጓደኛ የለኝም። ስራዬን በጣም ነው የምወደው። በማንኛውም ሰዓት በልምምድ ሜዳ ላይ እገኛለሁ። አትሌቶቻችን እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ መርዳት ያስደስተኛል። ይህ የሕይወቴ አንዱ ክፍል ነው” ሲልም ሰሞኑን ኔሽን አፍሪካ ከተባለ ድረ ገፅ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ተናግሯል።
በኦሮሚያ ክልል አርሲ የተወለደው ሁሴን ሸቦ ራሱም ሯጭ ነበር። ነገር ግን ያ ሕይወቱ በጉዳት ምክንያት ያሰበውን ያህል እንዳይጓዝ ሆኖ ከሯጭነት ዓለም ተገለለ። ክለቡ ማረሚያ ቤቶች ወደ ስልጠናው እንዲገባ ቢፈልግም እሱ ግን ፍላጎት አልነበረውም። በመሆኑም ፊቱን ወደ ሌላ ሙያ ለማዞር ሁሉ ሞክሮ ነበር። ያንን ጊዜ እንደዚህ ያስታውሰዋል።
“የሯጭነት ዘመኔ ሲያከትም በጣም ነበር የተበሳጨሁት። ምክንያቱም አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎት አልነበረኝም። ራሴን ለስራው አላዘጋጀሁትም ነበር። እናም አዲስ አበባን ጥዬ ወደ ትውልድ ስፍራዬ አርሲ ገባሁ። ለሶስት ወራት ያህል ተምሬ መንጃ ፈቃድ አወጣሁኝና ሾፌር ለመሆን ሞከርኩኝ። ነገር ግን ጓደኞቼ የክለቤን ጥሪ እንድቀበል በመምከር ገና በ25 ዓመቴ ወደ አሰልጣኝነቱ ዓለም እንድገባ አደረጉኝ። ዛሬ ላይ ሳስበው ምክራቸውን ባልሰማ ኖሮ በሕይወቴ ሁሉ ስፀፀት እኖር እንደነበር አስባለሁ” ይላል።
አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ በዚህ ሁሉ ጉዞው በተለየ ሁኔታ የሚያስታውሰው የ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክን ነው። “ያንን ኦሊምፒክ ፈፅሞ አልረሳውም። በወቅቱ በ10 ሺህ ሜትር በማሸነፍ የመጀመሪያዋ ጥቁር አፍሪካዊት የሆነችው ጀማሪዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የቡድን አጋሯና አሰልጣኟ ነበርኩኝ። ነገር ግን ቡድኑ ወደ ስፍራው ሲጓዝ እኔ እንድሄድ አልተደረገም። ያ የማይረሳኝ ነው። ከዛ ውጭ ግን በስራ ዘመኔ ሁሉ መልካም ትዝታዎቼ ይገዝፋሉ” ሲል ሁኔታውን ያብራራዋል። ከድንቅ አትሌቶቻችን ጀርባ ያለው አሰልጣኝ ሁሴን ሸቦ በ2019 በአፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የዓመቱ የአፍሪካ ኮከብ አሰልጣኝ ሆኖ መመረጡ ይታወሳል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም