የምንገኝበት የጥር ወር ማኅበራዊ ይዘት ያለው መንፈሳዊ በዓላትን ብቻ ሰይሆን የሠርግ ወቅትም ጭምር በመሆኑ አብሮነት፣መተጋገዝ፣መተሳሰብ በአጠቃላይ የሰዎች የእርስ በርስ ግንኙነት ይበልጥ የሚጠነክርበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይም ከክርስቶስ ልደት(ገና)በዓል ቀጥሎ የተከበረው ጥምቀት የአደባባይ በዓል(ፌስቲቫል)በመሆኑ ማኅበራዊ መስተጋብሩ ጎልቶ ይታያል፡፡
ከቤተሰብ አልፎ ጎረቤትና ወዳጅ የሚታደምበት የሠርግ ሥነሥርዓትም ቢሆን አብሮነት የሚጠናከርበት ነው፡፡ በዚህ አብሮነት ጎልቶ በሚታይበት ወር ሰዎች በየአደባባዩ ያሳዩትን ትሕትና አይተንበታል፡፡ በዚህ መልኩ የሚደምቀውን የጥምቀት በዓል ለመታደም ከባሕር ማዶ ሳይቀር የሚመጡ እንግዶች ሲማረኩም እናያለን፡፡ በአንደበታቸውም ሲመሰክሩ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንሰማለን፡፡
ባሳለፍነው የጥምቀት በዓል በተለይም የወጣቶች በጎ ሥራና ትሕትና የጎላ ነበር፡፡ ቀናነታቸው ለእምነታቸው ብቻ አልነበረም፡፡ ከእምነቱ የሚጠበቀውን በጎነት በተግባር ለማዋል በበዓሉ ድካም የተሰማቸው ከድካማቸው እንዲበረቱ እግር አጥበውና አሽተው ትሕትናቸውን ያሳዩ ወጣቶችን ለማየት ችለናል፡ ፡ካየሁትና ከታዘብኩት ጎልቶ የወጣውን እንዲህ ለአብነት ጠቀስኩ እንጂ ወጣቶቹ ከማስተናበር ጀምሮ ያጋጥማሉ ተብለው ቀድሞ በስጋት ጥንቃቄ ሲደረግ የነበረውን ሁሉ ለመከላከል ዝግጁ ከመሆን ጀምሮ በትሕትና የተለያዩ በጎ የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡
ውድ አንባቢያን ታዲያ ምን አዲስ ነገር አለ በዚህ ወቅት በጎ ተግባሩ ሁሌም የተለመደ ነው ትሉ ይሆናል፡፡ የተለመደውን ልነግራችሁ ሳይሆን የተለመደውን በበዓል ጊዜ የምናየውንና የምናሳየውን ትሕትና እና አብሮነት በሌላ ጊዜ ወይንም በአዘቦቱ ለምን አናየውም? በሚለው ላይ ነው ትኩረቴ፡፡
በግሌ በበዓላት ወይንም አንድ ክስተት ሲኖር ያ ኩነት እስኪያልፍ ብቻ በተወሰኑ አካላት ብቻ የሚከናወኑ በበጎነት የሚገለጹ ነገሮች በቂ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ በሀገር ደረጃ የሚገለጽ በሁሉም ዜጎች መልካምነት መኖር አለበት ባይ ነኝ፡፡ የበጎነቱ ተግባርም ከወጣቶች ብቻ ሳይሆን ታዳጊዎችን ጨምሮ ከጎልማሶችና ከአረጋውያን በአጠቃላይ የዜጎችም ኃላፊነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ችግሮችን ወይንም ነገሮችን የአንድ አካል ብቻ አድርጎ መውሰድ፣ግለኝነት፣ምን አገባኝ፣ምንቸገረኝ የኢትዮጵያውያን መገለጫ አይደለም፡፡ እንደውም ከራሱ የሌላውን ጉዳይ እንደራሱ አድርጎ ችግሩን ሲጋራ፣ደስታና ኃዘንን በጋራ ሲወጣ ነው የሚታወቀው፡፡ግለኝነትን ስላልኖርንበት ቃሉንም የምናውቀው በንባብ ወይንም በምዕራቡ ሀገር ከኖሩ ተሞክሮ ካላቸው ሲነገር ነው፡፡
በምዕራቡ በአብዛኛው ግለኝነቱ የበዛ በመሆኑ እርስበርስ ላለው ግንኙነት ግዴለሽነቱ የበዛ እንደሆነና የሚፈፀመው ወንጀልም ከዚሁ የመነጨ እንደሆነም ሲነገር እንሰማለን፡፡ አንድ ታዳጊ አብረውት በሚማሩ ተማሪዎች ላይ የጥይት ኡሩምታ አዘነበ የሚለው ወሬ አዲስ አይደለም፡፡
ማኅበራዊ ቀውስ ያስከተለው የግለኝነት ችግር እንደሆነም በጥርጣሬ ከሚነሱ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያም አንዳንድ ወጣ ያሉ ድርጊቶችን ሳይ ከዚህ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡ ምናልባት ይሄ ግሎባላይዜሽን ወይንም ዓለም አንድ መንደር እየሆነች ነው የሚለው እያሳሳተን ይሆን?ብዬ አስባለሁ፡፡
የበጎነት መገለጫ የሆኑ ተግባሮችን ለአንድ ወቅት ክስተት ካየን በኋላ በሌላ ጊዜ ሲደገም አለማስተዋሌ ጥያቄ ይፈጥርብኛል፡፡ በወጣቶቹ ትሕትና እና መልካም ተግባር ተደስቶ ምርቃቱንና ምስጋናውን ሲያሽጎደጉድ የነበረው ማኅበረሰብም መልካም ነገር በተናገረው አንደበቱ መልሶ እርግማንና ነቀፌታውን ሲያዥጎደጉድ ይሰማል፡፡
ይሄ ለምን ሆነ?አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ ለመቀማት በወገን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ሲፈጸም ያ ትሕትና የተሞላበት በጎነት የት ገባ? ያስብላል፡፡ በየትራንስፖርቱና በተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች ያለው መከባበርና መተሳሰብ ኢትዮጵያውያንን በሚገልጽ መልኩ ሆኖ የማላገኝባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ፡፡
እንዲህ ያሉ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ገንዘብ አይጠይቁም፡፡ ቅን ልቦና፣ሰፋ ያለ አዕምሮና ሰብዓዊነት ብቻ ነው የሚያስፈልገው፡፡ በገንዘብ አቅም ያጣውንም ቢሆን ዛሬ የኑሮ ውድነቱ አላፈናፍን ቢልም ‹‹ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ደግሞ ጌጡ›› በሚባለው ብሂል መወጣት የሚቻልበት ዕድል አለ፡፡ ዋናው ‹‹ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም›› እንደሚባለው ፍላጎት ነው የሚያስፈልገው፡፡
እንዲህ ያለው ነገርም እየደበዘዘ ነው ባይ ነኝ እኔ፡፡ የዳር ተመልካች መሆንም ሌላው የታዘብኩት ጉዳይ ነው፡፡ እንከኖች ቢኖሩም በዚህ ውስጥ ተሆኖ በሀገር ውስጥ የሚሠራው የልማትም ሆነ ሌላ ሥራን ገንቢ በሆነ መልኩ ሳይሆን የሚያጣጥል ትችት ጎልቶ ይታያል፡፡እንደዜጋ ያገባኛል ከሚለው ምን አገባኝ የሚለው ጎልቶ ይስተዋላል፡፡
በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማኅበራዊ ግንኙነታችን እና በኢኮኖሚ ላይ በእያንዳንዳችን ላይ ተጽዕኖውን ያሳረፈብን ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጭም ገጥሟት የነበረው ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናንም ጉዳያችን ያደርግነው ስንቶቻችን ነን? የሚለውንም ጉዳይ ብናይ እንዲሁ ለጉዳዩ ሩቅ የመሆን ነገር ነው የታዘብኩት፡፡
ለዚህም በየማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉት መረጃዎች ማሳያ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ዜግነት በያዙ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣በሀገር ውስጥም ሆነው ጉዳዩን የሌላ ሀገር አስመስለው ሲያቀርቡ ይሄ ያገባኛል የኔ ጉዳይ ነው የሚለው ኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ እየራቀ እንዲሄድ፣የፖለቲካ ጽንሰ ሀሳቡ በሚፈቅደው ሀገራዊ ይዘትን ሳይለቅ ከሚሰጠው ትችት ፈር የለቀቀ ሆኖ እንዲሰማኝ ነው ያደረገኝ፡፡
እንደውም የወሬ አጀንዳ በማድረግ የገቢ ምንጭ ነው የሆነላቸው፡፡ ማኅበራዊ ድረገጾች ዛሬ ለጋዜጠኝነት በአቋራጭ መክበሪያ ሆኗልም እየተባለ ነው፡፡ ለሙያቸውና ሙያቸው ብቻ ጊዜ ሰጥተው ጥሪት ሳይኖራቸው፣በኑሯቸውም እልፍ ያለ ነገር ሳያገኙ የጋዜጠኝነትን ሥነምግባር ባልተከተለ፣ለሀገርና ለዜጋ ቦታ ሳይሰጥ ገንዘብ ተኮር መረጃ በማስተላለፍ ለዛሬ ብቻ ባደሩት ሲቆጩና ሲበሳጩ ይስተዋላል፡፡
የትችት ናዳ እየወረደባቸው እራሳቸውን ለማስተካከል ፍቃደኝነቱ የሌላቸው ለመሳሳት ዝግጁ የሆነ በማግኘታቸው ነው የሚሉም አልጠፉም፡፡ ይኸው ማኅበራዊ ድረገጽ ላይ ተብሏል ብለው የሚከራከሩ ያጋጥማሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚታወቁት ‹‹ነገርን ከሥሩ፣ውሃን ከጥሩ›› በሚል አባባላቸው ነው፡፡
ለውሳኔ ሳይቸኩሉ፣ነገሮችን ለማመዛዘን፣ክፉና ደጉን ለመለየት ጊዜ የመስጠት የቆየ እሴት አላቸው፡፡ እንዲህ ያሉ መልካም ነገሮች ለአንዳንድ ዓላማዎች የሚውሉባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም ዘላቂ ባለመሆናቸው ወጥነታቸውን እናጣለን፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም