ኢትዮጵያ ስኬታማ ከሆነችባቸው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ መድረኮች አንዱ የዓለም አገር አቋራጭ ቻምፒዮና ነው። የአትሌቶች አቅምና ጉልበት በተለያዩ መሰናክሎች የሚፈተንበት የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ከሳምንታት በኋላ ዘንድሮ ለ44ኛ ጊዜ በአውስትራሊያ ባትረስ ይካሄዳል። ኢትዮጵያም በዚህ ቻምፒዮና ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጅቷን ከጀመረች ሰንብታለች። ለዚህም ከወር በፊት ሱሉልታ ላይ በተካሄደው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ተመርጠው ሲዘጋጁ ቆይተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 8 አሰልጣኞችንና 34 አትሌቶችን (ከነተጠባባቂዎቻቸው) ከጥር 3/2015 ዓ.ም አንስቶ ሆቴል እንዲገቡ በማድረግ ነበር ዝግጅቱ የጀመረው።
28 አትሌቶችም በሴትና ወንድ አዋቂዎች 10 ኪሎ ሜትር፣ በወጣት ወንድ 8 ኪሎ ሜትር፣ ወጣት ሴት 6 ኪሎ ሜትር እንዲሁም በድብልቅ ሪሌ አገራቸውን የሚወክሉ ይሆናል። ዝግጅቱ ያለበትን ሁኔታም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነትን ጨምሮ፤ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ እንዲሁም የስፖርቱ ባለሙያዎች በአካል በመገኘት ክትትል እያደረጉ ይገኛሉ።
በ 3 ሺ ሜትር መሰናክል ሩጫዎች የሚታወቀው አትሌት ጌትነት ዋለ በአገር አቋራጭ ውድድር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፍ ሲሆን፤ ዝግጅቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እንደ ቡድን ተናበው ልምምድ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ለአዲስ ዘመን ተናግሯል። ዝግጅቱ በተለያዩ ስፍራዎች በመገኘት እንዲሁም ውድድሩን ያማከለ እንደመሆኑ ቡድኑን ውጤታማ እንደሚያደርገውም አትሌት ጌትነት ዋለ ያለውን እምነት ገልጿል።
አትሌት መቅደስ አበበ በበኩሏ፣ ብሄራዊ ቡድኑ እንደሚወዳደርበት ርቀት አይነት ጥሩ የሚባል ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ትጠቁማለች። በ10 ኪሎ ሜትር አዋቂ ተሳታፊ የምትሆነው መቅደስ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር አቋራጭ ውድድር ላይ የምትሮጥ ቢሆንም በግሏም ሆነ እንደ ቡድን ለአገሯ ሜዳሊያ ለማስመዝገብ ጠንካራ ዝግጅት እያደረገች እንደምትገኝ አስተያየት ሰጥታለች።
የድብልቅ ሪሌ አትሌቶች አሰልጣኝ ብርሃኑ መኮንን፤ ቡድኑ ጥሪ ከተደረገለት ጊዜ አንስቶ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው መንጠባጠብ ሳይኖር ተሰባስቦ ወደ ሥልጠና መግባቱን ይገልጻሉ። በአገር ውስጥ በተካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር ላይ ተካፋይ የነበሩት ታዋቂና ልምድ ያላቸው አትሌቶች በመሆናቸው የብሄራዊ ቡድኑ ስብስብም አሉ የተባሉ አትሌቶችን እንዲሁም አዳዲስ አትሌቶችን ያካተተ መሆኑን አሰልጣኙ ገልጸዋል። እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፣ ውድድሩ በርካታ መሰናክሎች የሚኖሩት እንደመሆኑ የስልጠና እቅድ በማውጣትና ውጣ ውረድ የሚበዛባቸውን ቦታዎች በመለየትም ጭምር ዝግጅቱ በመከናወን ላይ ይገኛል። ከአትሌቶች አመጋገብ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘም የፌዴሬሽኑ ባለሙያዎች ያረፉበትን ሆቴል ጨምሮ ሰፊ ዝግጅት በመደረጉ አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያገኙ መሆኑንም አሰልጣኙ ተናግረዋል።
የአገር አቋራጭ ውድድሮች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የበላይነት ጎልቶ የሚታይበት መድረክ ነው። ኢትዮጵያም በዚህ ውድድር ውጤታማ ብትሆንም ባለፉት ሁለት ውድድሮች የኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች በውጤት ረገድ ብልጫውን ይዘው ታይተዋል። በዚህ ዓመት ግን ኢትዮጵያ የተሻለ ውጤት ለማግኘት ቡድኑ ብቃት ያላቸው አትሌቶችን ከማካተቱም ባለፈ አትሌቶችም ሆኑ አሰልጣኞች ስኬታማ ለመሆን በቁርጠኝነት በመስራት ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የወጣት አትሌቶች አሰልጣኙ ኃብተማርያም አየሁም በተመሳሳይ ቡድኑ ምርጥ ብቃት ላይ በሚገኙና በሥነምግባር በታነጹ አትሌቶች የተገነባ መሆኑን ይገልጻሉ። ቡድኑ በየዕለቱ የሁለት ጊዜ ልምምዶችን እየሰራ ሲሆን፤ በፌዴሬሽኑ በኩል በሚደረገው ክትትልም ለዝጅግቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። ሁሉም አትሌቶች በመልካም ጤና ላይ የሚገኙ በመሆኑ እንዲሁም ከዚህ ቀደምም በሌሎች ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ልምድ ያላቸው በመሆኑ እንዲሁም ውድድሩ የሚካሄድበት ባትረስ የአየር ሁኔታ በኢትዮጵያ ጋር ካለው ተቀራራቢ በመሆኑ ለውጤት ይጠበቃሉ።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር የስራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ፤ ዝግጅቱ በጃንሜዳ፣ እንጦጦ፣ ሱሉልታ፣ ቃሊቲ፣ ወንጂና የተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።፡ የሥልጠና መርሃ ግብሩም እነዚህን ቦታዎች ማዕከል ያደረገው ውድድሩ ከሚካሄድበት ጋር ተቀራራቢ የሆነ የአየር ንብረት ያላቸው በመሆኑ ነው። ውድድሩ የሚካሄድበት የባትረስት ወቅታዊ የአየር ሁኔታ ከ 26-31 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚገመት በመሆኑ በኢትዮጵያ ካለው ጋር ተቀረራቢ ሊባል የሚችል ነው።
ዝግጅቱ ላይ እየተካፈሉ ያሉ አትሌቶችም በመልካም ሥነምግባር እንዲሁም በቡድን ስሜት ልምምዳቸውን አጠናክረው እያከናወኑ ይገኛሉ። በመካከላቸውም ጠንካራ የቡድን ስሜት ከወዲሁ እየታየ ሲሆን፤ ካለፉት ውድድሮችም የተሻለ ውጤት በግልና በቡድን ሊገኝ እንደሚችልም ይጠቁማሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም