የኢትዮጵያ የቻን ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) በአልጄሪያ ለሰባተኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የቻን ውድድር ላይ ተሳትፈው ከምድባቸው አለማለፋቸውን ተከትሎ ከውድድሩ በጊዜ መሰናበታቸው ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ የዋልያዎቹን አባላት ከአልጄሪያ ወደ ኢትዮጵያ በጊዜ ለመመለስ የተደረገው ጥረት አልተሳካም ነበር። የብሔራዊ ቡድኑ ልዑክ ከቀናት በፊት ከአናባ ወደ አልጀርስ የተጓዘ ሲሆን ከአልጀርስ ግብፅ ደርሶ ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስ ነበር የታሰበው። ነገር ግን ወደ አልጄርያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ስለሌለው አማራጭ የሆነው የግብፅ አየር መንገድ የእለቱን መስተንግዶዬን ጨርሻለሁ በማለት ልዑኩን ሳያስተናግድ ቀርቷል። በዚህም ቢያንስ 22ቱን ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የተደረገው ጥረት አልተሳካም።
ከመነሻው ብሔራዊ ቡድኑ የደርሶ መልስ ትኬት የተቆረጠለት ቢሆንም ቡድኑ በውድድሩ የታሰበውን ያህል ርቀት ባለመጓዙ የመመለሻ ቀኑ በግማሽ አጥሯል። ስለዚህም የመመለሻ ቀን የትኬት ማስተካከል ስራ አስፈልጓል። ይህም የግብፅ አየር መንገድ በረራዎች ሁሉ ቀድመው ቦታ የተያዘባቸው መሆኑ ለማስተካከሉ ስራ እክል ፈጥሮ ቆይቷል። ፌዴሬሽኑም ልዑኩን ለመመለስ የተለያዩ አማራጮችን በመፈለግ ቡድኑ ዘግይቶም ቢሆን ተከፋፍሎ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለስ ችሏል።
የብሔራዊ ቡድኑ የመልስ ጉዞ መዘግየቱን ተከትሎ ከ14ተኛ ሳምንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ የሚካሄደው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የፊታችን ቅዳሜ ጥር 20 በሸገር ደርቢ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጉት ጨዋታ እንደሚጀመር ቀደም ብሎ የተገለጸ ቢሆንም ለአንድ ሳምንት ለመራዘም ተገዷል።
የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በድሬዳዋ የነበረውን ቆይታ ካጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒዮንሺፕ(ቻን) ውድድር ላይ መሳተፉን ተከትሎ ፕሪሚየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት ላይ መቋረጡ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድኑ ከውድድሩ ውጭ ከሆነ በኋላ ትኩረቶች ሁሉ ወደ ሊጉ የዞሩ ሲሆን አክሲዮን ማኅበሩም የተስተካካይ ሳምንት ጨዋታዎችን ጨምሮ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም ከ14ኛ እስከ 19ኛ ሳምንት ድረስ የሚደረጉትን ጨዋታዎች መርሐ-ግብር ይፋ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ቀጣይ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብሮች የሚከናወኑባቸው ቀናት ላይ ማስተካከያ አድርጓል። ይፋ በሆነው አዲስ መርሐ-ግብርም የአንድ ሳምንት አራት የጨዋታ ቀናት ሐሙስ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜ እና እሁድ እንደሚደረጉ ታውቋል። ከዚህ በፊት በጨዋታ ሳምንታት መካከል ሁለት የእረፍት ቀናት የነበሩ ሲሆን አሁን ግን የእረፍት ቀናቱ ወደ ሦስት እንዲያድጉ ተደርጓል።
ይህ ለውጥ የተደረገበትን ምክንያት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ለሶከር ኢትዮጵያ ሲያስረዱ፣ “መርሐ-ግብሩን ስናወጣ የመጫወቻ ቀኖቹ በዚህ መንገድ የተመረጡት ለተመልካቾች ምቹ እንዲሆኑ ታስቦ ነው። ከዚህ በፊት በአዘቦት ቀናትም በአብዛኛው ጨዋታዎች ይደረጉ ነበር። ይህ ደግሞ ተመልካቾች ወደ ስታዲየም መጥተው ጨዋታዎችን የሚመለከቱበትን ዕድል ያጠባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከዚህ በፊት እንደገለፅነው የውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ባለመብት ስታዲየሞች በተመልካቾች እንዲሞሉ የቀደመ ጥያቄም ስለነበረው መርሐ-ግብራችን ላይ የቀናት ለውጦችን ለማድረግ ችለናል። ስለዚህ አሁን በወጣው መርሐ-ግብር ሁሉም የጨዋታ ቀናት ከሐሙስ እስከ እሁድ የሚደረጉ ይሆናል።” ብለዋል።
ፕሪሚየር ሊጉ እስከ ድሬዳዋ በነበረው ቆይታ ከስምንት አመት በኋላ ወደ ሊጉ ተመልሶ እየተፎካከረ በሚገኘው ኢትዮጵያ መድን መሪነት የተጠናቀቀ ሲሆን መድን የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ መቀመጥ የቻለው በስምንት ጨዋታ አስራ ስምንት ነጥብና አምስት ግቦችን ሰብስቦ ነው። በተመሳሳይ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በስምንት ጨዋታ አስራ አምስት ነጥብና አስራ አንድ ግብ በመሰብሰብ ይከተላል። በሰባት ጨዋታ እኩል አስራ አራት ነጥብ መሰብሰብ የቻሉት ባህርዳር ከነማና ሃዲያ ሆሳእናም በግብ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ በቅርብ ርቀት ተፎካካሪ ናቸው። የሊጉ ውድድሮች በቀጣይ ሳምንት ሲጀምሩ በጉጉት በሚጠበቀው የሸገር ደርቢ ጨዋታ ቻምፒዮኖቹን የሚገጥመው ኢትዮጵያ ቡናም በሰባት ጨዋታ አስር ነጥብ ይዞ ስምንተኛ ደረጃ ላይ በሚገኝበት ወቅት ነው ትልቁን የከተማ ተቀናቃኝ የሚገጥመው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም