መንግስት የማዕድን ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ ከፍ ያለ አበርክቶ እንዲኖረው እየሰራ ይገኛል። ለውጤታማነቱ ደግሞ በተደራጀና በተቀናጀ የሚመራበትን ሥርአት በመዘርጋት፣ ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በፖሊሲ በማሻሻል፣ ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግና ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት በመንግሥት በኩል ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
የማዕድን ሀብት በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደመገኘቱ የክልል መንግስታት ሀብቱን ከመጠበቅ ጀምሮ በልማቱ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሀገራዊ ልማት ለማምጣት አቅም እንደሚፈጥርም ይታመናል። ሀብቱ ለምቶ ለተገቢው ዓላማ እንዲውል የአሰራር ሥርአት በመዘርጋት የድርሻቸውን በመወጣት ላይ ከሚገኙ ክልሎች መካከል ደግሞ የኦሮሚያ ክልል አንዱ ሲሆን፣ እምቅ የሆነ የማዕድን ሀብት በተለይም የወርቅ ማዕድን ከሚገኝባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ የሚመደብ ነው። በወርቅ ማዕድን ጉጂ ሻኪሶ አካባቢን ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
የኦሮሚያ ክልል የኢንቨስትመንት ግሩፕ (ቡድን) የያዘ በማዕድን ዘርፍ ላይ የሚሰራ “ኦ ማይኒንግ” የሚል ስያሜ ያለው መንግሥታዊ የልማት ድርጅት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። “ኦ ማይኒንግ” የተሰኘውን የኢንቨስትመንት ግሩፕ ለምን ማቋቋም እንዳስፈለገ፣ እያከናወናቸው ስላሉ ተግባራት እንዲሁም አጠቃላይ በክልሉ የማዕድን ልማት ጋር በተያያዘ ከዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር መስፍን አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ቆይታ!
አዲስ ዘመን፦ በቅድሚያ ኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለማቋቋም መነሻ የሆነውን ምክንያት ቢገልጹልን?
ዶክተር መስፍን፦ ኦ ማይኒንግ የኢንቨስትመት ግሩፕ ሲሆን መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ነው። በዚህ ዓመት ነው የተቋቋመው። በስሩም የተለያዩ የማዕድን ዘርፎች ያሉትና በማዕድን ዘርፍ ላይ የሚሰሩ መንግሥታዊ ተቋማትን ያስተዳድራል። ድርጅቱንም ማቋቋም ያስፈለገው በአራት ዋና ተግባራት ነው። በማዕድን ዘርፉ ላይ የግሉን ባለሀብት በማጠናከርና በማበረታት እንደሀገር የተያዘውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሳካ ማድረግ ትልቁን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ በሽርክና እና በተለያየ መንገድ የሚሰሩ ከሀገር ውስጥና ከውጭም ኢንቨስተሮችን በመሳብ እንዲሁም ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ ለኢንቨስተሮቹ ምቹ ሁኔታን መፍጠርን ታሳቢ ያደረገ ነው። የማዕድን ዘርፍን የገበያ ክፍተት መሙላት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማሳደግ፣ የአካባቢ ብክለትን የማያስከትል የማዕድን ልማት ማከናወንና ማዕድኑ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚኖረው ማህበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ማረጋገጥ ተግባራቶቹ ናቸው።
ኢትዮጵያ በጥናት የተረጋገጠ ከፍተኛ የማዕድን ክምችት ያላት ሲሆን፣ ከነዚህ መካከልም በዓለም ተፈላጊና ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ይገኛሉ። በዚህ ልክ ከዘርፉ በገቢ ተጠቃሚ መሆን ባለመቻሏ የተለያዩ ጥቅሞችን አጥታለች። ዘርፉ በሀገር ምጣኔ ሀብት ውስጥ ያለበትን ሚና አልተወጣም። ለዚህም እንደምክንያት የሚነሳው የትኩረት ማነስ ነው። ከ1967 እስከ 1983 ባሉት አመታት ዘርፉ በመንግሥት ብቻ ነበር የተያዘው። በማዕድን ልማት የግል ባለሀብቶች አይሳተፉም ነበር። ይህም ዘርፉን ውጤታማ እንዳይሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል። ዘርፉ ልምቶ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያስመዘግብ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እድገት ውስጥ አንዱ ተደርጎ የተወሰደው ከቅርብ አመታት ወዲህ ነው። በዚህ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እድገት 10 በመቶ ድርሻ የተጣለው በማዕድን ዘርፉ ነው።
እስካሁን ባለው የማዕድን ልማት ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የተሰጠ አልነበረም። ልማቱ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን በጠበቀ እንዲከናወን በትኩረት መሥራት ይጠበቃል። ማዕድኑ በሚገኝበት ስፍራ የሚኖረው ማህበረሰብ ከልማቱ ተጠቃሚ አለመሆኑም ሌላው ክፍተት በመሆኑ ይህንንም በማሻሻል ፍትሐዊነትን ማስፈን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፦ በኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ውስጥ የተሰባሰቡት እነማናቸው?
ዶክተር መስፍን፦ ኦ ማይኒንግ እናት ግሩፕ ሆኖ ነው የሚያገለግለው። በመሆኑም በሥሩ የተለያዩ ኩባንያዎች ይገኛሉ። ወርቅን ጨምሮ በተለያዩ የማዕድን አይነቶች ላይ ልማቱ ሲከናወን መንግሥት ድርሻ ወይንም ሼር ይኖረዋል። ኩባንያዎችም ሆኑ የአካባቢ ማህበረሰብ በልማቱ ሲሳተፉ በተመሳሳይ ድርሻ ወይንም ሼር ይኖራቸዋል። የመንግስት ድርሻ ከ50 በመቶ በላይ ከሆነ በመምራት፣ በመደገፍና በማስተባበር ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል።በልማቱ ላይ የሚሳተፉት ኩባንያዎችም ተጠሪነታቸው ለኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ይሆናል ማለት ነው። ድርጅቱ በአሁኑ ጊዜም የተለያዩ ኩባንያዎችን በሥሩ አቋቁሟል።
አዲስ ዘመን፦ ኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የበላይ ሆኖ ሲሰራ ምን አይነት ድጋፎችን በማድረግ ነው ኩባንያዎችን ውጤታማ የሚያደርጋቸው?
ዶክተር መስፍን፦ ድርጅቱ ኩባንያዎቹ ለሥራ ከሚያወጡት ከእቅድ ጀምሮ ክትትል ያደርጋል። በእቅዳቸው መሰረት መፈፀማቸውንም ይገመግማል። በግምገማው መሠረትም ውጤታማ ሆኖ ያልተገኘ ኩባንያ ቀጥታ ለቦርድ ያስተላልፋል። ኩባንያዎቹ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሰሩ ይደግፋቸዋል። የለማው ማዕድንም በህጋዊ መንገድ ገበያ ላይ እንዲውል በተለይም በየአካባቢው የለማውን የወርቅ ማዕድን ገዝቶ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርብ እንዲሁም ለማዕድን ልማቱ የሚውሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ ገዝቶ የማሰራጨት ህጋዊ መብት ተሰጥቶታል። ድርጅቱ ኩባንያ መሥርቶ ወደ ልማት የመግባት ህጋዊ መብትም አለው።
አዲስ ዘመን፦ የማዕድን ልማቱን የሚመራ እራሱን የቻለ ተቋም እንዳለ ይታወቃል። ኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ምን የተለየ ድርሻ እንዲኖረው ነው የተቋቋመው?
ዶክተር መስፍን፦ ኦሮሚያ ማዕድን ኤጀንሲ የመምራት ሚና ነው ያለው። ኦ ማይኒንግ የሚሰራውንም ሥራ ይከታተላል፣ ይገመግማል እንዲሁም አቅጣጫ ያስቀምጣል። የኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ተግባር ደግሞ ማዕድን የመፈለግ፣ የማግኘትና የማምረት በአጠቃላይ የማልማት ሥራ ነው የሚሰራው። የሁለቱ ተቋማት የሥራ ድርሻ በዚህ መልኩ የሚገለጽ ቢሆንም ለአንድ ዓላማ ስለሚሰሩ ተደጋግፈው ነው የሚሰሩት።
አዲስ ዘመን፦ የኦ ማይኒንግ ኢንቨስትመንት ግሩፕን በዚህ መልኩ ከነገሩኝ ከተቋቋመ ጀምሮ ያከናወናቸውን ሥራዎች ደግሞ ይገለጹልኝ?
ዶክተር መስፍን፦ በወርቅ ልማት ላይ አቅም ካላቸው ድርጅቶች ጋር በጋራ ሥራ ተጀምሯል። የደለል ወርቅ ማጠቢያ ማሽን ተከላ ተከናውኗል። ከልማቱ ከሚገኘው ገቢ ሶስት በመቶ ለአካባቢ ልማት የሚውልበት መንገድም ተመቻችቷል። የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችንም ለአካባቢው ማህበረሰብ በመስጠት ተጠቃሚነት ላይም ትኩረት ተሰጥቷል። ከአካባቢ ማህበረሰብ ጋር የሚሰራ ሥራ ልማቱን የተሳካ ስለሚያደርገው ነው በዚህ መልኩ እንቅስቃሴ የተጀመረው።
አዲስ ዘመን፦ ኦ ማይኒንግ ከተቋቋመ አጭር ጊዜው እንደሆነ ገልጸውልናል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ የወርቅ ማጠቢያ ማሽን ተከላ በማከናወን ወደ ሥራ ገብቷል። የጥናት ሥራ መቅደም አልነበረበትም?
ዶክተር መስፍን፦ እዚህ ላይ መታየት ያለበት ኦ ማይኒንግ ከመቋቋሙ በፊትም የማዕድንና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ተብሎ የማዕድን ልማቱ ይከናወን ነበር። አልሚ ኩባንያዎችም ነበሩ።ነገር ግን በሚፈለገው ደረጃ በማዕድን ዘርፍ ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ ማዕድን እራሱን ችሎ እንዲሰራ ተደረገ። በዚሁ መሠረትም ተቋቋመ። ቀደም ሲል በተከናወኑ የአዋጭነት የጥናት ሥራዎች መሠረት ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል።
አዲስ ዘመን፦ በማዕድን ልማቱ በዚህ ወቅት በስፋት እየተነሳ ያለው እየለማ ያለው የወርቅ መጠንና ለብሔራዊ ባንክ መግባት ያለበት እየተጣጣመ እንዳልሆነ ነው። ኦ ማይኒንግ በዚህ ላይ ምን ሚና አለው?
ዶክተር መስፍን፦ ህገወጥ ግብይቱ በአንድ አካባቢ ላይ ብቻ አይደለም እየተፈጸመ ያለው።ዘርፉን የሚያስተዳድረው አካል ነው የሚቆጣጠረው። ኦ ማይኒግ በተቻለ መጠን በሥሩ ያሉ ኩባንያዎችና በአካባቢ ማህበረሰብ የሚለማውን ወርቅ ሰብስቦ ቀጥታ ለብሔራዊ ባንክ እንዲገባ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል። በማዕድን ልማቱ በተለይም በወርቅ ዙሪያ የሀገርን ኢኮኖሚ ያሳድጋል ተብሎ በሚታሰበው የደለል ወይንም ጽንሰ ወርቅ ላይ ነው ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው። በመሆኑም ትላልቅ የውጭ ኩባንያዎችን በማሳተፍ ልማቱን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው። ፍላጎት መኖሩንም አረጋግጠናል። ሌላው በቅርብ ጊዜ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የማርብል ፕሮጀክት ነው። ልማቱንም በምዕራብ ሐረርጌ መኢሶ ወረዳ ውስጥ ለማከናወን ነው የታቀደው።
ለዚሁ ልማት የሚውል ማሽንም በግዥ ከውጭ ገብቷል። ግንባታውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይከናወናል። በአካባቢው የተደራጁ ወጣቶችም የማርብል ልማት ሼር ሆልደር ወይንም ባለድርሻ እንዲሆኑ ተደርጓል። በልማቱ ቡርቃ የሚባል ኩባንያ ነው በልማቱ የሚሳተፈው።ምዕራብ ወለጋ መንዲ በሚባል አካባቢም በተመሳሳይ የማርብል ልማት ለማከናወን ማሽን የማስገባት ቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል። በአካባቢው የሚገኘው የማርብል ማዕድን የተለያየ ቀለም ያለው ለውጭ ገበያ የሚሆን ተመራጭ ነው። የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ተስፋ የተጣለበት ነው። ሆኖም ግን በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ለጊዜው እንቅስቃሴው ተቋርጧል።
ለሲሚንቶ ፋብሪካ ግብአት የሚውል የከሰል ድንጋይ ክምችትም ኢሊባቦር ያዩ አካባቢ ይገኛል። በተለያየ ምክንያት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ ሳይኮን ቆይቷል። አሁን ግን በአዲስ መልክ ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ነው። በዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ጋር በጋራ ለመሥራት ቅድመ ሁኔታ ተመቻችቷል። 337 የሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችም የሼር ወይንም የሽርክና ተጠቃሚዎች ይሆናሉ። በአሁኑ ጊዜም ለልማቱ ሥራ የሚያስፈልግ ማሽን ከውጭ ለማስገባት በሂደት ላይ ይገኛል። ከወርቅ ማዕድን ውጭ በዓለም ገበያ ከአንድ ሺ በመቶ በላይ ዋጋቸው የጨመረ የማዕድን አይነቶች አሉ። በተለይም ለተለያየ ኤሌክትሮኒክስ ግብአት የሚውል ሊትየም የሚባል የማዕድን አይነት በጣም ተፈላጊ ነው። በሀገራችን ክምችት በመኖሩ ተጠቃሚ መሆን ይቻላል። የማዕድን ልማት ሥራ እውቀትና የገንዘብ አቅም ይጠይቃል። የማዕድን ልማት አካባቢን የሚጎዳ በመሆኑም ይህን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ በአግባቡ መምራት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፦ ለህገ ወጥነት መስፋፋት የጥቁር ገበያ ሚና በመጉላቱ እንደሆነም ይነሳል። ምን ሀሳብ አለዎት?
ዶክተር መስፍን፦ ገንዘብ ላይ ብቻ ትኩረት ከተደረገ ሀገር እና ትውልድ ችግር ውስጥ ሊገባ ይችላል። ጊዜያዊ ጥቅም ላይ ማተኮር አግባብ ነው ብዬ አላምንም። እያንዳንዱ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል። የወርቅ ማዕድን ሽያጭ ላይ መንግሥት የ35 በመቶ ጭማሪ አድርጓል። ማንኛውም አልሚ ለብሔራዊ ባንክ ወርቅ ሲያስገባ በዚህ ጭማሪ ተጠቃሚ ይሆናል። ይሄ በመንግሥት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል። ሌሎች የማዕድን አይነቶች ላይ በተመሳሳይ ህገወጥ ግብይት ይስተዋላል። ጠንካራ የሆነ የቁጥጥር ሥርአት በመዘርጋት በመከላከሉ ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ግንዛቤው አለ። በአሁኑ ጊዜ በኩባንያም ሆነ በባህላዊ የወርቅ አምራቾች የሚመረተው የወርቅ መጠን አማካዩ ይታወቃል። በዚህ መንገድም መከታተል ይቻላል።
አዲስ ዘመን፦ ለማዕድን ልማት ሥራ የተረጋጋ ሰላም፣ የተሟላ መሠረተ ልማት፣ ህገ ወጥነትን መከላከል፣ የአካባቢ ማህበረሰብንን በማሳተፍ ተጠቃሚ ማድረግ፣ የአካባቢ ሥነ ምህዳርን መጠበቅ የሚሉት አስፈላጊ ነገሮች ምን ያህል ትኩረት ተሰጥቷቸዋል?
ዶክተር መስፍን፦ እነዚህ አግባብነት ያላቸው ጥያቄዎች በተገቢው ካልተመለሱ በልማቱ ላይ የሚሳተፉት ኩባንያዎች ዘላቂነታቸው ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። በመሆኑም በእያንዳንዱ ላይ መሥራት ይጠበቃል። ለአብነትም የአካባቢ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አንድ አልሚ ኩባንያ ወደ ልማቱ ከመገባቱ በፊት ከማህበረሰቡና ከአካባቢው አስተዳደር ጋር መተማመን ላይ መደረስ አለበት። አንድ ኩባንያ በሚፈጥረው ግድፈት ሌሎችንም በተመሳሳይ የማየት ሁኔታ ስለሚፈጠር ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በዚህ አግባብ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው። ከፀጥታ ጋር በተያያዘም ልማቱ በሚከናወንበት አካባቢ ካለው የፀጥታ ኃይል ጋር እየተሰራ ሲሆን፣ እስካሁንም ያለው ትብብርና ግንኙነት ጥሩ በመሆኑ የፀጥታ ኃይሉ ደጋፊ ሆኖ ነው ያገኘነው። ማህበረሰቡ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ከተደረገ በማዕድን ልማት አካባቢ የሚነሳውን የፀጥታ ስጋትና ተግዳሮቶችን መቀነስ ይቻላል። ፀጥታን በማስከበር ረገድ የአካባቢው ማህበረሰብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ኦ ማይኒንግ ይህን መንገድ በመከተሉም ለወርቅ ማጠቢያ የተከላቸው ማሽኖች በማህበረሰቡ ጥበቃ ሥር እንደሆኑ እንዲተማመን አድርጎታል። ተጠቃሚነታቸው የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ግን ያምናል።
አዲስ ዘመን፦ የማዕድን ልማቱ በስፋት እየተከናወነ ያለው በኩባንያ ደረጃ ነው ወይንስ በአነስተኛ አልሚዎች ነው?
ዶክተር መስፍን፦ በወርቅ ማዕድን ልማት ሚድሮክ ግሩፕ ነው የሚጠቀሰው። አሁን ላይ ወደ ኩባንያ የሚመጡ መሻሻል እየታየ ነው። የወርቅ ማጠቢያ ማሽኖችን በመጠቀም ጭምር ያለው ነገር በልማቱ የሚያበረታታ ነው። እስካሁን ባለው ግን በአነስተኛ አልሚዎች ነው የሚከናወነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ጊዜ እጅግ አመሰግናለሁ።
ዶክተር መስፍን፦ እኔም አመሰግናለሁ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥር 19 ቀን 2015 ዓ.ም