የፈረንጆቹን የክረምት ወቅት ተከትሎ በብዛት ይካሄዱ የነበሩ የማራቶንና የጎዳና ላይ ውድድሮች በሀገር አቋራጭ ሩጫዎች ተተክተዋል። በዚህ ሳምንት መጨረሻም ከጎዳና ላይ ውድድሮች ይልቅ መሰናክሎች የሚበዛበት አገር አቋራጭ ውድድር በስፋት ይካሄዳል። ይሁን እንጂ ክረምቱ በማይጠነክርባቸው አንዳንድ የዓለማችን ከተሞች አልፎ አልፎ የጎዳና ላይ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ከነዚህም መካከል በመጪው እሁድ በጃፓኗ ኦሳካ ከተማ የሚካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር ተጠባቂ ነው።
በሌላው ዓለም እምብዛም የማይታወቀውን የሴቶች ብቻ የጎዳና ላይ ውድድሮችን በማዘጋጀት ከሚታወቁት ሀገራት መካከል አንዷ ጃፓን ስትሆን፤ ኦሳካ ይህን ሴቶች ብቻ የሚሳተፉበትን ማራቶን ታሰናዳለች። ይህ የማራቶን ውድድር እአአ ከ1982 አንስቶ ሴት የማራቶን ሯጮችን ብቻ በማወዳደር 42ኛ ዓመቱን ዘንድሮ ያስቆጥራል። በጃፓን ሶስተኛዋ ትልቅ ከተማ በሆነችው ኦሳካ የሚደረገው ይህ ውድድር በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶችን ያሳትፋል። በዓለም አትሌቲክስ ዕውቅና ያለው ይህ ውድድር ከጃፓናዊያን አትሌቶች ባሻገር የሌሎች ሀገራትን ታዋቂ አትሌቶችን የሚያሳትፍም ነው። ውድድሩ እአአ ከ2011 አንስቶ ተወዳዳሪዎች ያልፉባቸው የነበሩ አቀበትና ኮረብታማ ስፍራዎችን በማስወገዱ ፈጣን ሰዓት የሚመዘገብበት ሆኗል። በዚህም የአትሌቶች የተሳትፎ ፍላጎት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።
ከቀናት በኋላ የሚካሄደው ይህ ውድድር ኢትዮጵያዊያን እና ኬንያዊያን የማራቶን አትሌቶች የሚካፈሉበት እንደመሆኑም ከፍተኛ ፉክክር ሊካሄድበትና የቦታው ፈጣን ሰዓት ሊመዘገብበት እንደሚችል ተገምቷል። የቦታው ክብረወሰን ባለፈው ዓመት በጃፓናዊቷ አትሌት ሚዙኪ ማሱዳ ሲያዝ፤ አትሌቷ የገባችበት ሰዓትም 2:20:52 ነው። ይሁንና የምስራቅ አፍሪካዊያኑ ሀገራት አትሌቶች ፈጣን ሰዓት በሰከንዶች የተሻለ በመሆኑ በዚህ ዓመትም አዲስ ሰዓት ይመዘገባል በሚል ይጠበቃል። በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑና ለአሸናፊነት ከፍተኛ ቅድመ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከልም ኢትዮጵያዊያኑ ሄቨን ኃይሉ እንዲሁም ሲሳይ መሰረት ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በዚህ ውድድር የተካፈሉ ሲሆን፤ እአአ በ2010 አማኔ ጎበና እንዲሁም እአአ በ2019 ፋጡማ ሳዶ አሸናፊዎች ነበሩ። ጃፓን እአአ በ2007 የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናን ባስተናገደችበት ናጋይ ስታዲየም ፍጻሜውን የሚያደርገው ውድድር ዘንድሮም በቀዳሚነት ይገባሉ በሚል ይጠበቃል። ከተወዳዳሪ አትሌቶች መካከል ባላቸው ፈጣን ሰዓት ሁለተኛ ደረጃ በመያዝ የተቀመጠችው አትሌት ሄቨን ኃይሉ 2:20:19 የሆነ ሰዓት አላት። አትሌቷ ይህንን ሰዓት ያስመዘገበችው እአአ 2021 በአምስተርዳም ማራቶን ሲሆን፤ በወቅቱ በአንድ ሰከንድ ብቻ ቀድማት ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ኬንያዊት አትሌት በዚህ ውድድርም ተፎካካሪዋ ትሆናለች በሚል ይጠበቃል።
ኬንያዊቷ አትሌት ማውሬን ቼፕኬሞይ በወቅቱ ከሄቨን ጋር እልህ አስጨረሽ ውድድር በማድረግ ነበር ቀድማት የገባቸው። ያስመዘገበችው 2:20:18 የሆነ ሰዓትም የግሏ ምርጥ በመባል ተመዝግቦላታል፤ ይኸውም የዚህ ውድድር አሸናፊ ያደርጋታል በሚል በውድድሩ አዘጋጆች እንድትጠበቅ አድርጓታል። ነገር ግን በአንድ ሰከንድ ልዩነት በተከታይነት ስሟ ከሰፈረው ኢትዮጵያዊቷ ሄቨን ጋር እጅግ ፈታኝ የአሸናፊነት ፍልሚያ እንደሚገጥማትም ተገምቷል። ማራቶንን እንዲሁም ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች ላይ በመሮጥ የዓመታት ልምድን ያካበተችው አትሌቷ በጃፓኗ ኦሳካ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በተፎካካሪዋ ላይ ድልን በመቀዳጀት በውድድሩ ሌላኛዋ አሸናፊ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለመሆንም ትሮጣለች።
አምና በዙሪክ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ሲሳይ መሰረትም ለአሸናፊነት ከሚጠበቁት አትሌቶች መካከል አካቷታል። በውድድሩ ሶስተኛዋ ባለ ፈጣን ሰዓት አትሌት ስትሆን፤ በዙሪክ ያስመዘገበችው 2:20:50 የሆነ ሰዓትም የግሏ ምርጥ ነው። አትሌቷ በዓመቱ በበርሊን ማራቶንም ተሳትፎ ያደረገች ቢሆንም ርቀቱን የሸፈነችበት ሰዓት በስምንት ደቂቃዎች የዘገየ ነበር። በጎዳና ላይ ሩጫዎች ልምድ ያላት ሲሳይ በዚህ ውድድር ላይም ለሀገሯ ልጅ እንዲሁም ለኬንያዊቷ አትሌት ፈተና ልትሆንባቸው እንደምትችልም ተገምቷል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም