የሙዚቃ ታሪክ ሲወሳ ከፍተኛውን ድርሻ ይዘው ታሪካቸው የሚነገርላቸው፤ ህዝብም የሚያውቃቸው ድምፃውያኑ ብቻ ናቸው። ከድምፃውያኑ ጀርባ ሆነው ሙዚቃውን ሙዚቃ ያደረጉ ባለሙያዎች ባስ ሲልም ከነጭራሽ ስማቸውን የሚያነሳ የለም። አልያም በሥራቸው ልክ ታሪካቸው አልተነገረላቸውም። በተመሳሳይ ሙዚቃው ተከሽኖ አድማጭ ዘንድ እንዲደርስ ድልድይ የሚሆኑት አቀናባሪዎች (ፕሮዲውሰሮች) ታሪክ ከነጭራሹ አስታዋሽ ሳያገኝ ነው የቆየው። ይህንን ድልድይ ከገነቡና የኢትዮጵያን የዘመናዊ ሙዚቃ ቅጂ ኢንዱስትሪ ሕይወት ከዘሩበት ሰዎች አንዱና የዘርፉ ፈር ቀዳጅ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቅጂ (ሪከርዲንግ) ባለቤት አምሃ እሸቴ ናቸው።
በ1950ዎቹ አዲስ አበባ ከምዕራባውያኑ የዘመናዊ ሙዚቃ ስልት ብሉስ፣ ሶልና ሮክ ኤንድ ሮል ጋር የተዋወቀችበት ዘመን ነበር። በተለይም የዚህ ዘመን ወጣቶች ለእነዚህ የውጭ ሙዚቃዎች የተለየ ፍቅር እያሳደሩ ቢሄኑም እንደልባቸው ሙዚቃውን አግኝተው የሚያዳምጡበት እድል ግን አልነበራቸውም። ታዲያ የዚያን ዘመን ወጣቶች ለእነዚህ የሙዚቃ ስልቶች ያላቸውን ጥማት የሚያስታግሱበት የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮን በማድመጥ ብቻ ነበር።
አምሃ እሸቴም በወጣትነት እድሜያቸው የእነዚህ የዘመኑ ተወዳጅ የሙዚቃ ስልቶች አፍቃሪ ነበሩ። ይሁንና በነበረው የአቅርቦት ችግር ምክንያት እሳቸውም ሆኑ ጓደኞቻቸው እንደልባቸው ሙዚቃዎቹን አግኝተው መዝናናት አልቻሉም። አምሃ ይህንን ችግር ለመፍታት የራሳቸውን ሙዚቃ መደብር ለመክፈት ይወስናሉ። በዚህ ጊዜ አምሃ ለስራ ጉዳይ አስመራ የሚሄዱበት አጋጣሚ ይፈጠራል። በጊዜው አሜሪካ ቃኘው የተሰኘ የጦር ሰፈር በአስመራ ነበራት። ይህ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ወታደሮቹ የሚዝናኑበት የራሱ ሬዲዮ ጣቢያ ነበረው። አምሃ አስመራ በቆዩባቸው ጊዜያት አዲስ አበባ እያሉ ይጓጓላቸው የነበሩ ሙዚቃዎች በቃኘው ሬዲዮ እንደልባቸው የመኮምከም እድል አገኙ። ስለዚህ አጋጣሚ አምሃ ሲናገሩ ‹‹በጊዜው በሙዚቃው ተመስጬ ለሰዓታት ከተቀመጥኩበት አልነሳም ነበር›› ይላሉ።
በአስመራ አሜሪካኖቹ ከፍተውት የነበረው የቃኘው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ የሙዚቃ ፍቅራቸውን በእጥፍ እንደጨመረላቸው ይናገራሉ። በአዲስ አበባም ቢሆን የክቡር ዘበኛ ንብረት የነበረው የጠቅል ሬዲዮ ጣቢያ አልፎ አልፎ የሚለቃቸውን ሙዚቃዎች መስማት የመንፈስ ሀሴትን ያጎናፅፋቸው ነበር።
ጅማሮ “ሃራምቤ” የሙዚቃ መደብር
አምሃ በጊዜው የውጭ የሙዚቃ ሪኮርዶችን ከአሜሪካ ለማስመጣት ብዙ ፈተናዎች ነበሩባቸው። በመጀመሪያ ደረጃ በቂ ገንዘብ እጃቸው ላይ አልነበረም፤ ሁለተኛ ሪከርዶቹ ቢመጡም ሱቅ የሚከፍቱበት ቦታ ገና አላዘጋጁም። ሆኖም ገንዘቡ በብድር ሲገኝ የቦታው ጉዳይ አራዳ ከአንድ ልብስ ሰፊ ዘንድ ጥገኝነት በማግኘት ተፈታ። አምሃ ከውጭ ያዘዟቸውን ሙዚቃዎች አዲስ አበባ ሲደርሱ የመጀመሪያዋ ‹‹ሃራምቤ›› ሙዚቃ ቤት ተከፈተች። የነጀምስ ብራውን፣ ጂም ሬቭስ፣ ኦቲስ ሬዲንግ እና ዊልሰን ፒኬትን ሙዚቃዎች የያዘችው ሃራምቤ ገና በተከፈተች እለት ነበር ገበያዋ የደራው። ገና በመጀመሪያው ቀን ከመጡት ሪከርዶች ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተሸጠው አለቁ። በገበያው ሁኔታ ሞራላቸው የተነሳሳው አምሃ ሌሎች ተጨማሪ ሪኮርዶችን አዘው ንግዱን ማጧጧፍ ተያያዙት። የአዲስ አበባ ወጣትም የልቡ ደረሰ። ሃራምቤ ቁጥር ሁለት በፒያሳ ስትከፈት ከአዲስ አበባ ውጪም በናዝሬት፣ በአስመራና በድሬዳዋ አምሃ ሙዚቃ ቤቶችን መክፈት ቻሉ።
ከሙዚቃ መደብር ወደ ሙዚቃ ሪኮርድ
ካሰቡት በላይ ገበያው የቀናቸው አምሃ ከአሜሪካ በተጨማሪ ከኬኒያ፣ ከሱዳን፣ ከህንድ እና ከምዕራብ አፍሪካ ሃገራት ሙዚቃዎችን ማስመጣት ቀጠሉ። በተለይም ከሱዳን የመሃመድ ወርዲ ሙዚቃዎች እጅግ ተወዳጅ ነበሩ። አንድ ጥያቄ ግን አምሃ ጭንቅላት ውስጥ ይመላለስ ነበር። ይኸውም ‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃስ? የሚል ነበር።
አምሃ የውጭ ሃገር ሙዚቃዎችን እያስመጡ ከመሸጥ በተጨማሪ በሃገር ውስጥ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችን ስራ ፕሮዲውስ ማድረግ አለብኝ ብለው ማሰብ ጀመሩ። ይህ ግን ቀላል አልነበረም። ከባድ ያደረገው ደግሞ የገንዘብ ችግር ሳይሆን የህግ ጉዳይ ነው። በወቅቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙዚቃ የማሳተምና የማከፋፈል ስራ የባለቤትነት መብት በህግ የተሰጠው የሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ብቻ ነበር። ይህ የሞኖፖል መብት በህግ ለቲያትር ቤቱ ቢሰጠውም ቲያትር ቤቱ ግን ለ20 ዓመታት ያህል ምንምአይነት ሙዚቃ አላሳተመም ነበር።
ይህን የተመለከቱት ወጣቱ አምሃ ‹‹ለምን እኔ አላሳትምም?›› ሲሉ በድፍረት ተነሱ። በወቅቱ ከትያትር ቤቶቹ የተሰጠው ምላሽ ‹‹መብቱ የኛ ነውና እንዳትሞክረው›› የሚል ዝግ መልስ ነበር። አምሃ ጉዳዩ አስጨነቃቸው። የንጉሰ ነገስቱን ህግ መጣስ ደሞ የሚያመጣውን መዘዝ ያውቃሉ። በሌላ ጎኑ እሳቸው የተለያዩ የውጭ ሀገራትን ሙዚቃ እያመጡ እየሸጡ የሀገራቸው ሙዚቀኞች በሸክላ አለመቀረፅ፣ ለሌላውም ዓለም አለመተዋወቅ ከንክኗቸዋል።
ያለው አማራጭ በድፍረት አሳትሞ የሚመጣውን በፀጋ መቀበል ብቻ ሆነ። ለዚህ ደግሞ የሚተባበር ድምፃዊ ያስፈልጋል። አምሃ የሚያውቃቸውን ዘፋኞች አማከሩ። ሁሉም ፈሩ። ‹‹አዬ ጦስ ታመጣብናለህ›› እያሉ ወደኋላ አፈገፈጉ። በዚህ መሀል አንድ ወጣት ድምፃዊ ብቅ አለ። ድምፃዊው ከአምሃ ጋር የማይደፈረውን ለመድፈር ተስማማ። ‹‹ከታሰርንም እየዘፈንን አብረን እንገባለን›› ሲል የአምሃን ልብ በወኔ ሞላው። እናም ሆነ። እንደተፈራው እዚህ ግባ የሚባል ቅጣት ግን አልነበረም።
ይህ ድምፃዊ ተወዳጁ አለማየሁ እሸቴ ሲሆን በአጋጣሚውም በአምሀ እሸቴ ሪከርድስ አማካኝነት የመጀመርያ የሸክላ ሙዚቃ አሳታሚ ለመሆን በቃ። ይህም ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ በጀርመን ሀገር ካሳተሙት መዲናና ዘለሰኛ፣ ከነፈረደ ጎላ የሸክላ ስራ፣ እንዲሁም በጣሊያን ወረራ ወቅት ከታተሙ ጥቂት ሸክላዎች በኋላ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ህትመት ለመሆን በቃ።
በዚህ መሰረት በአምሃ ሪከርድስ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃው የታተመለት አለማየሁ እሸቴ ነበር። ስራዎቹ ደግሞ ‹‹ትማርኪኛለሽ›› የተሰኘ የአማርኛ ዘፈንና አንድ የሱዳንኛ ዘፈን ነበር። እነኚህ ዘፈኖች በ1961 ዓ.ም ህንድ ሃገር ተሰርተው በሃራምቤ ሙዚቃ ቤት ለገበያ ሲቀርቡ ተቀባይነታቸው ከፍተኛ ሆነ። ቀጠለናም ሌላ የአለማየሁ እሸቴ ነጠላ ዜማ ታተመ። ከዚያ በኋላማ አምሃ ሪከርድስ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ፕሮዳክሽን ነገሰበት።
ሙላቱ አስታጥቄ፣ ግርማ በየነ፣ ጌታቸው ካሳ፣ ተስፋማርያም ኪዳኔ፣ ተሾመ ምትኩ፣ ሰይፉ ዮሐንስ የመሳሰሉት እውቅ የሙዚቃ ስራዎች በአምሃ ሪከርድስ ታትመው ለገበያ ቀረቡ። ከእነዚህ መካከል የካሳ ተሰማ ‹‹ትዝታ›› የተሰኘው ሙዚቃ አምስት ሺ ኮፒ በመሸጥ ክብረወሰኑን ሰበረ። የአምሃ ሪከርድስ ስኬት ሌሎች ሰዎችን ወደእዚህ ኢንዱስትሪ እንዲቀላቀሉ መንገድ የጠረገ ሆነ። ካሳሁን እሸቴ (ፊሊፕስ) እና አሊታጎ (ካፊያ ሪኮርድስ) አምሃ በቀደደው መንገድ የመጡ ናቸው።
አምሃ ለሙዚቀኞች ይከፈል የነበረውንም አነስተኛ ክፍያ እንዲለወጥ የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ ሰው ነበሩ። በ1966 ዓ.ም ገደማ ለመሃሙድ አህመድ ለአንድ ነጠላ ዜማ ሁለት ሺ ብር በመክፈልም መሃሙድን የጊዜው ከፍተኛ ተከፋይ አድርገውት ነበር። በዚህ ጊዜ የአብዛኞቹ ስመ-ጥር ዘፋኞች ወርሃዊ ደመወዝ በአማካይ ከ200 ብር እንደማይበልጥ ሲታወስ ለነጠላ ዜማው የተከፈለው ገንዘብ ምን ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም።
ሶል ኤኮስ ባንድ
አምሃ ከፕሮዳክሽን ስራው ባሻገር ስኬታማ የሆነ የሙዚቃ ባንድ ማቋቋም ችለው ነበር። ሶል ኤኮስ የተባለው ይኸው ባንድ በድምፃዊነት አለማየሁ እሸቴንና ተሾመ ምትኩን ያቀፈ ሲሆን አሉላ ዮሐንስ ሊድ ጊታር፤ ታምራት ፈረንጅ ትራምፔት፤ መሰለ ገሰሰ ድራም፤ ተኪ አድሃኖም ጊታር፤ እንዲሁም ቴዎድሮስ ምትኩ ሳክስፎን ይጫወቱ ነበር። በሶል ኤኮስ ባንድ ተሰርተው ተወዳጅነት ካተረፉ ሙዚቃዎች መካከል የተሾመ ምትኩ ‹‹ጋራ ስር ነው ቤትሽ›› እንዲሁም የሰይፉ ዮሐንስ ‹‹ኤቦ ላላ›› ተጠቃሽ ናቸው።
ሶል ኤኮስ ባንድ በዘመኑ በሂልተን ሆቴል ምርቃት እንዲጫወት የተመረጠ ባንድ ከመሆኑም ባሻገር በአዲስ አበባ ትልልቅ የሰርግ ፕሮግራሞች ላይ የሚፈለግ ባንድ ነበር። ከአዲስ አበባ ውጭም በክፍለሃገር ከተሞች እየተጋበዘ የተጫወተ ስመጥር ባንድ ነበር።
የአምሃ የስደት ህይወት
‹‹ደርግ ወደ ስልጣን ሲመጣ ነጻነታችንን ይዞ የመጣ መስሎን እጃችንን ዘርግተን ነው የተቀበልነው›› ይላሉ አምሃ። ዳሩ ግን ነገሮች ሁሉ እንደታሰበው አለመሄዳቸውን ይገልፃሉ። ደርግ ወደ ስልጣን በመጣበት ዓመት የጥላሁን ገሠሠን፤ የአለማየሁ እሸቴን፤ የተክሌ ተስፋእግዚን፤ እና የሙሉቀን መለሰን ስራ ለመስራት ወደ ግሪክ ተጉዘው ነበር። ስራዎቹ ካለቁ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩ የተክሌ ተስፋእዝጊ ትግርኛ ሙዚቃ ጉምሩክ ላይ እንዳይገባ ታገደ። ምክንያቱ ደግሞ ስርዓቱን የሚቃወም ነው በሚል ነበር። ዘፈኑ ከመከልከሉም በተጨማሪ በዘፈኑ ስራ የተሳተፉ ባለሙያዎችና የአምሃ ወላጅ አባት ታሰሩ። ይህንን የሰሙት አምሃ ለራሳቸው ደህንነት ስለሰጉ በወጡበት ቀሩ።
በስደት በኖሩበት አሜሪካም አምሃ ከሙዚቃው ዘርፍ አልተለዩም ነበር። በዋሽንግተን ዲሲ ቡሉናይል የተሰኘ ክለብ በመክፈት በከተማው አንዱ ተወዳጅ ክለብ እስከመሆን ደርሶም ነበር። ከአገር ቤት እነ ግርማ በየነን፤ መሃሙድ አህመድን፤ ጌታቸው ካሳን የመሳሰሉ ድምፃውያንን ያቀፈ ቡድን በማስመጣትም በአሜሪካ በትልልቅ መድረኮች ላይ ስራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ረድተዋቸዋል። ምስጋና ለፍራንሲስ ፋልሴቶ አምሃ እጅ የነበሩ ኦርጅናል ሪኮርዶች በኢትዮጲክስ ስብስብ ውስጥ መካተት ችለዋል። አምሃም ይህንን የፋልሴቶን ጥረትና ስራ እጅግ አድርገው ያመሰግኑም ነበር።
የአምሃ ሌጋሲ
አምስት አስርት ዓመታትን ባስቆጠረ ጉዞ አምሃ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ አይተኬ ሚናን ተጫውቷል። የሙዚቃ መደብር በመክፈት፤ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችን ስራ ፕሮዲውስ በማድረግ፤ በማሳተም፤ በማከፋፈል እንዲሁም በማማከር ረገድ የዋሉት ውለታ ታሪክ ሊዘነጋው የሚችል አይደለም። ብዙ ስራዎችን የሰራው ግርማ በየነ በአንድ ወቅት ሲናገር አምሃ በስራው ልክ እውቅና አልተሰጠውም ብሏል። እውነት ነው፤ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላበረከተው አስተዋፅኦ በቅጡ አልዘከርናቸውም።
በሀገራችን በግለሰብ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የሸክላ ሕትመትን የጀመሩትንና ለሙዚቃችን ታላቅ አስተዋፅዖ ያደረጉትን አቶ አምሀ እሸቴ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ሚያዚያ 22 ቀን 2013 ዓ.ም በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተውናል። በአገራችን የመንግስት የሙዚቃ ባንዶች ብቻ በነበሩበት እና ከአገር ፍቅር ማህበር ውጪ ሙዚቃን ማሳተም በማይፈቀድበት በግለሰብ ተነሳሽነት ሙዚቃን ለማሳተም የደፈሩ አቶ አምሀ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃን ካዘመኑት አሳታሚና አከፋፋዮች ግንባር ቀደሙን ሰው በዛሬው በባለውለታዎቻችን አምድ እንዲህ ልንዘክራቸው ወደናል! ቸር እንሰንብት!።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥር 17/2015 ዓ.ም