የአካባቢ ተጽእኖዎች በስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ በተለያየ መንገድ አዎንታዊና አሉታዊ አሻራ ሊያሳርፉ እንደሚችሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል። በተለይም ከአተነፋፈስ ስርአት ጋር በእጅጉ ቁርኝት ያላቸው እንደ አትሌቲክስ ያሉ ስፖርቶች በተበከለ አየርና ከፍተኛ ሙቀት የመታወክ እድላቸው ሰፊ በመሆኑ ልምምዶችና ውድድሮችን በተስማሚ የአየር ንብረት ማድረግ ግዴታ እየሆነ መጥቷል። ያደጉት አገራት ይህን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የሚመጣን ፈተና ለመወጣት ቴክኖሎጂዎችን እንደ አንድ አማራጭ መጠቀም ከጀመሩ ሰነባብተዋል። በኢትዮጵያም በተለይም አትሌቶችና አሰልጣኞች ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀሙ እድል ባይኖራቸውም ምቹ የሆነ የአየር ጸባይ ያለበትን አካባቢ እየፈለጉ ከከተማ ውጪ ልምምዶችን ሲሰሩ ማየት የተለመደ ነው።
የዓለም አትሌቲክስም በዚህ ረገድ 214 አባል ፌዴሬሽኖችን በአንድ አድርጎ ከ2020-2030 የሚተገበርና ቀጣይነት ያለዉ ስትራቴጂ በመቅረጽ የአየር ንብረት ለውጥ ስፖርቱ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመዋጋት እየሰራ ይገኛል። ዋና ዓላማውም በ2030 ከካርቦን ልቀት ነጻ የሆነ ተቋምን ለመገንባት ነው። የአስር ዓመቱ እቅድ የተዘጋጀው በአካባቢ፣ ማህበረሰብና ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ጥቅሞችን ለማድረስ ሲሆን በዚህም የስፖርትንና የአትሌቲክስን ጉልበት በመጠቀም ለማህበረሰብ የተሻለ ዓለምን ለመፍጠር ያለመ ነው። ስትራቴጂው ከፍተኛ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያላቸው መርሆችና ተግባራዊነትን ያቀፈም ነው።
የአየር ንብረትና የአየር ብክለት ጉዳይ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የቤት ውስጥና የቤት ውጪ የስፖርት ውድድሮችን የማዘጋጀት ፍቃድ ለማግኘት እንደ ቁልፍ ጉዳይ እየታየ ይገኛል። ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ስጋት ውስጥ እየወደቀች በምትገኝበት በዚህ ወቅት በተለያየ መንገድ ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቀው በካይ ጋዝ በስፖርት ውድድሮች ላይ ተጽዕኖ በመፍጠር ውጤታማነት ላይ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል። እነዚህን በአየር ብክለት ምክንያት የሚመጡትን ተጽዕኖዎች በመቆጣጠር ለስፖርት ዝግጅቶች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋልም ይህን ተጽእኖ ለማስቀረት እየተወሰደ የሚገኝ አንዱ ርምጃ ነው። ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችም የተበከለ አየርን በማጥራት፣ ከፍተኛ ሙቀትን በመቀነስና ቀዝቃዛውን ወደ ተስተካከለ አየር በመቀየር ለስፖርተኞች ምቹ ነገርን በመፍጠር ለውድድሮች መሳካት የጎላሚናን በመወጣት ላይ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ ለስፖርተኞች በተለይም ለአትሌቶች ምቹ የአየር ሁኔታን የመፍጠርና ከብክለት የጸዳ አካባቢን እውን የማድረግ ስራ ከአምስት ዓመት በፊት ተሞክሮ እንደነበር ይታወሳል። ጀግናው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ተገጥሞ የነበረ ቢሆንም ቴክኖሎጂው የፈጠረው ተፅእኖ፣ ያመጣው ለውጥና ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይህ ነው ሳይባል ቆይቷል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ሪጅን አትሌቲክስ ምክር ቤት ጉባኤ የአየር ብክለት መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ስራ የማስጀመር መርሃግብር ተከናውኖ ነበር። ቴክኖሎጂው በይፋ ስራ መጀመሩ በወቅቱ በነበረው መርሃግብር የተገለፀ ሲሆን፣ የስፖርቱን ማህበረሰብ በተለይም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ለአካባቢ ቀጣይነት እየተጫወቱ ያሉትን ሚና የሚያሳይ እንደሚሆን ተጠቁሟል። የአየር ጥራት መቆጣጠሪያ መሳርያው በአካባቢ አየር ውስጥ የሚገኘዉን የተበከለ አየር (ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ) በመሰብሰብ ስፖርተኞች ንጹ አየር በመተንፈስ ውጤታማ እንዲሆኑ አሰተዋጾው ከፍተኛ እንደሚሆን ተገልጿል።
በወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተገጠመው የአየር ጥራት መቆጣጠርያ (air quality sensor) ቴክኖሎጂ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የጋራ ትብብር ሲሆን፣ የተከላው ስራ የተከናወነው በተባበሩት የአካባቢ ፕሮግራም አፍሪካ እና በስቶክሆልም ኢንስቲትዩት አፍሪካ ሽርክና መሆኑ ተገልጿል። ይህም በኢትዮጵያና በምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክሱን የማገዝና የተሻለ የማድረግ አንድ እርምጃ እንደሆነ ታምኖበታል።
ቴክኖሎጂው ስፖርቱን ታሳቢ አድርጎ ይስራ እንጂ ለከተማውም ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ተጠቁሟል። ከቴክኖሎጂው ባሻገር ከሰው ሰራሽ የተፈጥሮ ጸጋዎችን መንከባከብም የአየር ብክለትን ለመቀነስ አንዱ መፍትሄ በመሆኑ የአትሌቲክሱና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል። ለዚህም ምሳሌ እንዲሆን የዓለም ቻምፒዮኗ አትሌት ለተሰንበት ግደይና አትሌት ታደሰ ወርቁ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሲገጠም ከተገኙት እንግዶች ጋር በጋራ በመሆን ችግኝ ተክለው የድርሻቸውን በመወጣት ፋና ወጊ ሆነዋል።
የአየር ጥራት መቆጣጠርያ (air quality sensor) መሳሪያ ስራውን በይፋ ያስጀመሩት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽንና የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፕሬዚዳንትና የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ሲሆን፣ የኢፌዴሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር፣ የጤና ሚኒስትር፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተወካዮች ተገኝተው ቴክኖሎጂው በይፋ ስራ መጀመሩን አብስረዋል።
ዓለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 17/2015 ዓ.ም