ሀገሪቱ የሰሚንቶ ዋጋ እየናረ መጥቶ ለግንባታው ዘርፍ ትልቅ ፈተና እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል።መንግሥትም ይህን የሲሚንቶ ዋጋ ለማረጋጋት በተደጋጋሚ የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል፤ ይሁንና ዋጋውም አልቀመስ ብሎ መቆየቱም ይታወሳል።
የሲሚንቶ ዋጋ በከፍተኛ መጠን ማሻቀብ ብቻም አልነበረም ችግሩ።ምርቱ በገበያው ሊገኝ አለመቻሉም ሌላው ፈተና ነበር።መንግስት በሲሚንቶ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የወሰደው እርምጃም ሌላ ችግር አስከትሏል፤ የኬላ መብዛትና ሲሚንቶ ይዞ መንቀሳቀስ ፈታኝ ሆነው ነበርና።መንግስት ለግዙፍ ፕሮጀክቶች ምቹ ሁኔታ ቢፈጥርም፣ ሌሎች ፕሮጀክቶችና ትናንሽና ቀላል ግንባታዎች ምርቱን በገበያው ላይ እንደልብ ማግኘት አለመቻላቸውን ተከትሎም ግንባታ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ታይቷል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ መንግሥት ሲወስዳቸው የነበሩ የመፍትሔ አማራጮች የዘርፉን ችግር በዘላቂነት መፍታት አልቻሉም።መፍታት አለመቻል ብቻም ችግሩ ይበልጥ እየተወሳሰበ ነው የመጣው።ሲሚንቶ የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ መሆኑ እየተጠቀሰም ቅሬታዎች ይነሱበትም እንደነበር ይታወቃል።
ይህን ሁሉ ተከትሎም መንግስት ከአንድ ወር በፊት ወደ ሌላ እርምጃ ገብቷል።ቀደም ሲል በሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት ላይ ያወጣውን መመሪያ በማሻሻል የገበያ ስርዓቱን ቀድሞ ወደነበረበት በመመለስ ሲሚንቶ በነጻ ገበያ እንዲመራ የሚያስችል ውሳኔ አሳልፏል።በዚህም መሰረት የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭትን ለመቆጣጠር የወጣው መመሪያ ቁጥር 908/2014 ተሽሮ መመሪያ ቁጥር 940/2015 እንዲጸድቅ ተደርጎ አዲስ ውሳኔ ከተላለፈ በኋላ ወደ ስራ ተገብቷል።በአሁኑ ወቅትም ሲሚንቶ ለገበያ እየቀረበ ያለው በዚህ መመሪያ መሰረት ነው።
በውሳኔው መሰረትም የሲሚንቶ ገበያ፤ “በነጻ ገበያ” እንዲመራ ሆኖ በየአካባቢው የሚኖረውን የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋ የመወሰን ኃላፊነትም ለፋብሪካዎች ተሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም፤ በፋብሪካዎች እና ተጠቃሚዎች መካከል ያሉት አከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ከሲሚንቶ ግብይት እና ስርጭት እንዲወጡ ያደረገውን አሰራር የቀለበሰ ሆኗል።
ውሳኔው መተግበር በጀመረባቸው ሰሞናት በዚህ ገጽ በሰራነው ዘገባ ያነጋገርናቸው የግንባታ ተቋራጮች ሲሚንቶ ገበያ ላይ መታየት መጀመሩን፣ ዋጋውም ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸውልን ነበር።ሲሚንቶ በነጸ ገበያ መሸጥ መጀመሩ ቀደም ሲል ጭር ብለው የሰነባበቱ የሲሚንቶ መሸጫ አካባቢዎች ሞቅ ደመቅ እንዲሉ እያደረጋቸው መሆኑንም ደግሞ ሰሞኑን ገበያዎቹን ተዘዋውረን በተመለከትንበት ወቅት ማረጋገጥ ችለናል፡፡
በእያንዳንዱ የሲሚንቶ መሸጫ አካባቢ ምርቱ ሲወጣና ሲወርድ እየታየ ነው።ነጋዴዎቹም አቅርቦት መኖሩን ተከትሎ ሱቆቻቸውን ከፍተው እየሰሩ መሆናቸውን አረጋግጠውልናል።በአካባቢዎቹ በሲሚንቶ ጫኝና አውራጅነት የሚሰሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ስራቸው እንደተመለሰላቸው ነው የገለጹት።
አቶ አስቻለው ተካ አዲስ አበባ ውስጥ ጀሞ ቁጥር ሶስት ፉሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሚንቶ በችርቻሮ በመሸጥ ይተዳደራሉ። መንግሥት ከዚህ ቀደም በሲሚንቶ ገበያው ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ያስችላል በሚል አውጥቶት የነበረው መመሪያ ሲሚንቶ ቸርቻሪዎች ሲሚንቶ እንዳይገዙ እና እንዳይሸጡ የሚያደርግ እንደነበር ያስታውሳሉ፤ በወቅቱ እርሳቸው እና መሰል ቸርቻሪዎችን ብቻ ሳይሆን ገዢዎችም ጭምር እጅግ ተጎድተው እንደነበር ነው የሚገልጹት። መመሪያው በወጣበት ወቅት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከሁለት ሺ ብር በላይ ሲሸጥ እንደነበረ ተናግረዋል።
በቅርቡ መንግሥት ሲሚንቶ በነፃ ገበያ እንዲመራ በሚል ያስተላለፈውን መመሪያ ተከትሎ በሦስት እና በአራት ቀናት ውስጥ ዋጋው መሻሻል ማሳየቱን በመጥቀስ፤ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከአንድ ሺ እስከ አንድ ሺ 500 እንዲሁም አንድ ሺ 700 ድረስ ወርዶ መሸጥ ጀምሯል ሲሉ ያመለክታሉ። በጅምላ ለሚገዙ ደግሞ ዋጋው ከዚህም በላይ እንደሚቀንስ ነው የጠቆሙት።
እርሳቸው እንዳሉት፤ እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች የሲሚንቶ አከፋፋዮች ኢትዮጵያ ውስጥ በቂ የሲሚንቶ ምርት እንዳለ ያምናሉ፤ በመሆኑም ዋጋው ከዚህ በታች ይወርዳል የሚል ተስፋ አላቸው። ለዚህም ሲሚንቶ ፈላጊ ደንበኞች ተረጋግተው እንዲጠባበቁና እጅግ አስቸኳይ ለሆነ ግንባታ ካልሆነ በስተቀር ተስገብግቦ መግዛት ተገቢ እንዳልሆነና መረጋጋት እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።
በመገናኛ አካባቢ ከሚገኙና ሲሚንቶን በችርቻሮ ከሚሸጡ ነጋዴዎች መካከል አቶ ትንሳኤ ክብሩ አንዱ ናቸው። እሳቸውም በጀሞ ቁጥር ሶስት ፉሪ አካባቢ ሲሚንቶ በችርቻሮ በመሸጥ እንደተሰማሩት አቶ አስቻለው ሁሉ፤ በአሁኑ ወቅት ያለውን የገበያ ሁኔታ የተሻለ ሲሉ ይገልጹታል፡፡
መንግሥት የዛሬ አንድ ወር አካባቢ በሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት ላይ ያሳለፈው መመሪያ ማለትም የሲሚንቶ ገበያ በነጻ ገበያ እንዲመራ መፍቀዱ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ይገልጻሉ።እንደ አቶ ትንሳኤ ገለጻ፤ ከዚህ ቀደም አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ1800 እስከ 2000 ብር ይሸጥ ነበር።ምርቱም እንደልብ አይገኝም ነበር፤ አሁን ያለው የገበያ እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ገበያውን ከዚህ በበለጠ ማረጋጋት እንደሚቻል አቶ ትንሳኤ የጠቆሙት።ለዚህም ከዚህ ቀደም የችርቻሮ ነጋዴዎች በቀጥታ ምርቱን ከፋብሪካ ማውጣት የሚችሉበት መንገድ እንዲመቻች ነጋዴዎቹ ተሰባስበው መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያልቻሉ ቢሆንም፣ የሲሚንቶ ግብይት በመንግሥት ቁጥጥር ውስጥ ከነበረበት ጊዜ ይልቅ አሁን የተሻለ ነው ሲሉ ያብራራሉ።በአሁኑ ወቅትም ሲሚንቶ በመንግሥት ቁጥጥር ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞ በነበረው የገበያ ሥርዓት ማለትም በነጻ ገበያ እየተመራ መሆኑን አብራርተው፣ ይህ በመሆኑም ገበያው እየተረጋጋ ይገኛል ብለዋል።
የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት ዙሪያ ያለው ችግር ዘርፈ ብዙ እንደነበር አቶ ትንሳኤ ያመለክታሉ።በሲሚንቶ ግብይት ስርዓት ውስጥ የተፈጠረው ችግር በርካታ በዘርፉ ተሰማርተው ሕይወታቸውን ይመሩና ቤተሰብ ያስተዳድሩ የነበሩ ነጋዴዎች ከመስመር እንዲወጡ ያደረገ እንደነበር በማስታወስም፣ አሁንም ድረስ ወደ ቀድሞው መስመር ለመግባት የተቸገሩ ነጋዴዎች ስለመኖራቸው አቶ ትንሳኤ ያመለክታሉ።የተወሰኑ የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆች ዛሬም ድረስ መዘጋታቸውን ጠቅሰው፣ ምክንያቱ የሲሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያው ያስከተለው ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚያቀርቡት የሲሚንቶ ምርት ዋጋ የሚለያይ መሆኑን ያነሱት አቶ ትንሳኤ፤ አሁንም ቢሆን የተጋነነ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን የሚረብሹ አንዳንድ ፋብሪካዎች ስለመኖራቸው ጠቁመዋል።ለአብነትም ሀበሻ ሲሚንቶ ነጋዴውን አስገዳጅ ወደሆነ መንገድ ውስጥ በመግፋት ተጨማሪ ክፍያ እየጠየቁ እንደሆነ ነው የተናጉት።በአሁን ወቅትም ቀድሞ የተከፈለ ክፍያ ላይ ጭምር ተጨማሪ ዋጋ ካልተከፈለ ሲሚንቶውን እንደማይሰጡና አቅራቢውን አስገዳጅ በሆነ ውል እያሰሩት እንደሆነ ነው የገለጹት።በዚህም መሰረት አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከፋብሪካው ሲወጣ ከ1000 እሰከ 1100 ብር ድረስ እየጠየቁ እንደሆነም አንስተዋል።
ከፋብሪካው በ1000 እና 1100 ብር የወጣ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ደግሞ አቅራቢው ወይም ኤጀንቱ የራሱን ድርሻ ጨምሮ እንዲሁም የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ ቸርቻሪው ጋር ሲደርስ ዋጋው የተጋነነ ይሆናል።ለዚህም ፋብሪካዎች በተመጣጣኝና ተመሳሳይ በሆነ ዋጋ ቢያቀርቡ መልካም ነው በማለት ሀሳባቸውን የገለጹት አቶ ትንሳኤ፤ ቀድሞ በተከፈለ ክፍያ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን እንደ ችግር ጠቅሰዋል፡፡
በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ የቆየውን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ አማራጮችን ሲያቀርብ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ትንሳኤ፤ ነጋዴዎችም በበኩላቸው መፍትሔ ያሉትን ሃሳብ ሲጠቀሙ እንደነበር ጠቅሰዋል። በዚህም መሰረት ነጋዴዎች በማህበር ተደራጅተው አክሲዮን ማህበር በማቋቋም ነጋዴው ከፋብሪካው ጋር ትስስር በመፍጠር በቀጥታ መግዛት የሚችልበት ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቀው እንደነበር ይገልጻሉ።ይህ አይነቱ አሰራር ቢፈቀድ በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት እንደሚችል ነው ያመላከቱት፡፡
ሲሚንቶ በችርቻሮ የምትሸጠው ሌላኛዋ ነጋዴ ትዕግስት ታደሰም በተመሳሳይ አሁን ያለው የገበያ እንቅስቃሴ የተሻለ እንደሆነ ነው የገለጸችው።ባለፉት ጥቂት ወራት ምንም አይነት የሲሚንቶ ምርት ማግኘት ባለመቻሏ መሥራት እንዳልቻለች በማስታወስ፤ አሁን ላይ በመጠኑም ቢሆን ምርቱን እያገኘች መሸጥ መቻሏ ትልቅ ለውጥ እንደሆነ ነው ያነሳችው።
ባለፉት ወራት የአካባቢው የሥራ እንቅስቃሴ እጅግ ተቀዛቅዞ የነበረው ከምርት አቅርቦት እጥረት በተጨማሪ ሲሚንቶውን በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ነበር የሚል እምነት እንዳላት የገለጸችው ትዕግስት፤ አሁን ያለው የገበያ ሁኔታ ጥሩ እንደሆነና ምንም ካለመሥራት አሁን የተሻለ ነው ትላለች።
ለወራት ምንም የሲሚንቶ ምርት ማግኘት ባለመቻሉ ከሥራ ውጭ እንደነበረች ጠቅሳ፣ አሁን በመጠኑም ቢሆን እያገኘች መሆኑን ተናግራለች።አጠቃላይ የሲሚንቶ ዋጋ እንደየደረጃው የሚለያይ መሆኑን በመጥቀስም አንድ ኩንታል ሲሚንቶ ከ1500 እስከ 1600 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሳለች።ይህ ለውጥ የመጣው መንግሥት ከገበያው ውስጥ እጁን በማውጣቱና የሲሚንቶ ገበያ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በነጻ ገበያ እንዲመራ በመፈቀዱ ምክንያት ነው ብላለች፡፡
ባለፉት ወራት ነጋዴውን ጨምሮ ጫኝ አውራጆች ሁሉ ሥራ ፈት ሆነው ሲማረሩ እንደነበር በማስታወስ አሁን ሁሉም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብላለች።ደንበኞችም በጣም ተቸግረው ነበር ያለችው ትእግስት፣ በውድ ዋጋም ለመግዛትም ችግር እንደነበር አስታውሳለች።በአሁኑ ወቅት ሲሚንቶ ካለፈው ጊዜ በተሻለ ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝ፣ ምርቱ ግን አሁንም በሚፈለገው መጠን እየቀረበ አለመሆኑን ጠቁማለች።የሲሚንቶ ምርት በሁሉም ሱቆች እንደሌለ ጠቅሳ፣ ሁሉም ነጋዴ እያገኘ እንዳልሆነ ነው ያመለከተችው።
ሲሚንቶ በማውረድና በመጫን ሥራ የተሰማራው ወጣት ቸርነት ታከለ፤ በመገናኛ አካባቢ ለረዥም ጊዜ እንደቆየ በመግለጽ፤ አንድ ኩንታል ሲሚንቶ በሰባት ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሂሳብ የሚያወርድና የሚጭን መሆኑን ተናግሯል።በዚህ ሥራ በቆየበት ጊዜም አንድ ኩንታል ሲሚንቶ እስከ ሶስት ሺ ብር ሲሸጥ መመልከቱን ይናገራል።ነጋዴዎች የምርት አቅርቦት ሲገጥማቸውና መሸጫ ሱቆቻቸው ሲዘጉ እሱን ጨምሮ መሰሎቹ የዕለት ጉርስ ተቸግረው እንደነበርም አስታውሷል።
በጀሞ ቁጥር ሶስት ፉሪ አካባቢ ሲሚንቶ በመጫንና በማውረድ የሚተዳደረው ወጣት ታሬ ገመቺስ በበኩሉ በቅርቡ የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆች እየተከፈቱ ሲሚንቶም እየመጣ ነው ይላል።በዚህም ደስተኛ መሆኑን ጠቅሶ፤ የሲሚንቶ ችግር ሲሚንቶ መሸጫ ሱቆቹን እስከመዘጋት አድርሷቸው እንደነበር ያስታውሳል።ሱቆቹ በመዘጋታቸው ምክንያት እሱን ጨምሮ ሌሎች አብረውት የሚሰሩ ወጣቶች ሥራ ፈተው መቆየታቸውን አስታውሶ፣ በዚህ የተነሳም በልቶ ለማደር ሲቸገሩ እንደነበር ያመለክታል፡፡
እንደ ወጣት ታሬ ሁሉ በአካባቢው የጉልበት ሥራ እየሠራ የሚተዳደረው ወጣት ዳኘው ጥላሁን የሲሚንቶ ገበያ ሲቀዛቀዝ የዕለት ጉርስ የሚሆን ገቢ አጥቶ እንደነበር ነው የገለጸው።በዚህም ሲሚንቶ ከመጫንና ከማውረድ ውጭ የሆኑ ማንኛውንም የጉልበት ሥራ በአካባቢው ሲሰራ መቆየቱን አመልክቶ፣ አሁን ግን የሲሚንቶ መሸጫ ሱቆቹ እየተከፈቱ መሆናቸውን ተናግሯል፤ ይህም የመጫንና የማውረድ ሥራውን እንዲቀጥል እንዳስቻለው ተናግሯል፡፡
ከሲሚንቶ አቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴርን ሀሳብ ለማካተት ብንሞክረም አልተሳካልንም፤ ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ላይ በቅርቡ በአምራቾቹ በኩል መግለጫ እንደሚሰጥበት በመግለጽ ምላሹን በዚያው ማግኘት እንደሚቻል አስታውቆናል።
አዲሱ መመሪያ ከወጣበት እስከ አለፈው ታኅሣሥ አጋማሽ ድረስ ለአምስት ወራት በሥራ ላይ በቆየው አሰራር መሰረት፤ የሲሚንቶ አከፋፋዮች የሚመረጡት በክልል እና በከተማ አስተዳደሮች አማካኝነት ነበር። ባለፈው ታኅሣሥ አጋማሽ ይፋ የተደረገው አዲስ መመሪያ በአንጻሩ፤ ፋብሪካዎች “የሲሚንቶ ምርቱን ተደራሽ ያደርጉልኛል” የሚሏቸውን አከፋፋዮች ራሳቸው እንዲመርጡ ነጻነት የሰጠ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በወቅቱ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደገለጸው፤ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በመመሪያ የተተገበረው አሰራር ውጤቶችን ቢያስገኝም እንደ ምርት እጥረት ያሉ ተግዳሮቶች ግን ተፈጥረዋል። በአገሪቱ ከሚገኙና ከአስር የሚልቁ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ውስጥ በአግባቡ አምርተው ለገበያ ማቅረብ የቻሉት ከሶስት የሚበልጡ አልነበሩም።ሚኒስቴሩ ባለፈው ወር የሲሚንቶ ገበያ በነጻ ገበያ እንዲመራ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ በገበያው ላይ የተወሰኑ ለውጦች እየታየ ስለመሆኑ የዝግጅት ክፍላችን በሰራው ዘገባ አመልክቶም ነበር።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም