የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በከተማ አስተዳደሩ የተጣለበትን የገቢ መሠብሰብ ኃላፊነት በሚገባ ለመወጣት እና ከተማዋ ከምታመነጨው ኢኮኖሚ በበጀት ዓመቱ የ70 ቢሊየን ብር ዕቅድን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይገልጻል። በስድስት ወራት ውስጥም ዘርፈ ብዙ ስራዎችንና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማከናወን እያደገ የመጣውን የግብር ከፋይ ቁጥር ተደራሽ ባደረገ መልኩ ቀልጣፋና ውጤታማ ስራ ማከናወኑን አስታውቋል፡፡ ለመሆኑ ተቋሙ ከተጣለበት መንግስታዊ ኃላፊነት አንጻር ህገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ መስመር አምጥቷል፣ ህገወጥ አሰራሮችን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን በማረምና በማስተካከል ረገድ ምን ያህል ተጉዟል። ከግብር ስወራና ከመሳሰሉት ጋር የተያያዙ ስራዎች በሚፈለገው ልክ የክትትልና የቁጥጥር ስራው ተሰርቷል። በእነዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሉጌታ ተፈራ ምላሽ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን፡- በበጀት ዓመቱ ግብር ለመሰብሰብ ስትነሱ በቀዳሚነት የተቀመጡ መርሆች ምንድን ናቸው?
አቶ ሙሉጌታ፡- የከተማችንን መሰረታዊ ፍላጎቶችና ጥያቄዎችን ለመመለስ በመጀመሪያ ትኩረት የሚሰጠው ገቢ ማግኘት ላይ ነው።ይህ ቢሮ ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የሚፈልገውን ገቢ በመሰብሰብ ረገድ ቀዳሚው ሚና እና ተግባሩን እንዲወጣ ኃላፊነት የተጣለበት ተቋም ነው። በመሆኑም ይህን ገቢ ለመሰብሰብና የከተማዋ ዕድገት ለማምጣት በግልጽ የተቀመጠ ነው።በመርህ ደረጃም መግባባት የተደረሰበት ከመሆኑም በላይ ኃላፊነቶችም በግልጽ የተቀመጡ ናቸው።
የገቢው አሰባሰቡ ዘመናዊነት የተከተለ እንዲሆን፣ ቀልጣፋ አሰራር እንዲተገበር፣ ግብር አሰባሰቡ ፍትሃዊ እንዲሆን፣ በተጨማሪም ተደራሽ በሆነ መንገድ መስራት የሚለውም ቀዳሚው ሥራችን ነው።
እንደ ከተማ አስተዳደሩ ይህ ቢሮ ከፍተኛው ገቢ መሰብሰብ እንዳለበት ይታመናል።ከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ የ100 ቢሊዮን ብር በጀት አውጇል።ይህ በጣም ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ነው።ይሁንና ከዚህ ውስጥ የከተማዋ ከፍተኛ ገቢ የሚሸፈነው ወይንም 70 ቢሊዮን ብር በገቢዎች ቢሮ በሚሰበስበው ነው፡፡
ቢሯችን ከሚሰበስበው 70 ቢሊዮን ብር በተጨማሪ ቀሪው ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት በሚሰጡት አገልግሎት እና የተለያዩ አግባቦች የሚሰብሰብ መሆኑ ይታወቃል።ስለዚህ ትልቅ ሥራ እንደሚጠበቅብን አውቀንና ተማምነን ነው ወደ ሥራ የገባነው።ከአመራር እስከ ባለሙያው ምን መሠራት አለበት የሚለው የሥራ ድርሻም በሚገባ ኃላፊነት ወስደን ነው ወደ ተግባር እንቅስቃሴ የገባነው።
በመሆኑም እንደተቋም በ2015 በጀት ዓመት 70 ቢሊዮን ለመሰብሰብ በተጀመረው ሥራ በርካታ ተግባራትን አከናውነናል።ሥራችንን ስንጀምር ሰፊ የንቅናቄ መድረኮችን በተለያየ ቦታዎች አካሂደናል።በዚህም በጀመርነው ንቅናቄ በየቅርንጫፎቻችን ምን መሠራት አለበት በሚለው ታቅዶ አስፈላጊ ተግባራት ተከናውነዋል።በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ከሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎችና አመራሮች ጋር የተግባቦት ሥራዎችን በሰፊው በማከናወን ለእቅዳችን እና ግባችን መሳካት መሰረት ተጥሏል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ከማን ጋር ምን መሥራት አለበት
በሚለውም ላይ ነው ትኩረት የሰጠው።በዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ በጣም ትልቅ ሥራዎች የተከናወኑበት ነው።ይህን በማድረጋችን ባለድርሻ አካላትን እንደየአስፈላጊነቱ ለማሳተፍ እና እቅዳችንን ለማሳካት ተገቢውን እርምጃ ሄደናል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት ከተማዋ አለኝ የምትለው ሁነኛ የግብር ከፋይ ስንት ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- በከተማችን የግብር ከፋዮች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው።በተለይም በምንፈጥራቸው መድረኮችና የተግባቦት ሥራ በርካቶችን ወደ ህጋዊ መስመር በማስገባት ገቢ መክፈል እንዳለባቸው አምነው እየከፈሉ ነው።ከ449 ሺህ ግብር ከፋዮች ውስጥ 93 ከመቶ የሚሆኑት በግብር ማሳወቅያ ወቅት ወደ ቢሯችን መጥተው ኃላፊነታቸው ተወጥተዋል።ይህ ሊሆን የቻለው በየጊዜው በምናከናውናቸው ተግባራት ነው።ከዚህ ውጭ ያሉትን ቀሪዎቹ ደግሞ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተገቢው የማሳወቅ ስራ በመስራት ገቢ እንዲሰበሰብ ተደርጓል።
አዲስ ዘመን፡- ተቋሙ በስድስት ወራት ምን ያክል ገቢ ሰብስቧል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ከላይ እንደተገለጸው በበጀት ዓመቱ በሰፊው መስራት አለብን ብለን ነው የተነሳነው።በእቅዳችን ከተያዘው 60 ከመቶ መሰብሰብ ችለናል።ቀሪው 40 ከመቶ ደግሞ በቀሪው ጊዜ ይሰበሰባል።ይህን ለማድረግም ከመጀመሪያው ጀምሮ በከተማ ከንቲባ ጭምር ትልቅ የንቅናቄ ሥራዎች ሰርተናል።ይህን ለማሳካትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋርም በተቀናጀ አሰራር ዘርግተናል።ብልሹ አሰራርንም ለማቃለል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ነው እየሰራን ያለነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቢሮው የ2015 የበጀት ዓመት ዕቅድ ከ2013 እና ከ2014 ዓ.ም ንፅፅር ምን ይመስል?
አቶ ሙሉጌታ፡- በአጠቃላይ ቢሮው ከዓመት ወደ ዓመት አሰራሩን በማዘመን፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ በአመራሩና በፈፃሚው መካከል ከፍተኛ መናበብና ተነሳሽነት በመፍጠር የገቢ አሰባሰብ አቅሙን እያሳደገ ሲሆን ይህም በ2013 በጀት ዓመት 42.40 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን በ2014 በጀት ዓመት ደግሞ 55.77 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ችሏል። በ2015 በጀት ዓመት ቢሮው 70 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራት ቢሮው ለመሰብሰብ በዕቅድ ከተያዘው 39.55 ቢሊዮን ብር፣ 42.29 ቢሊዮን ብር በመሰብስበ የዕቅዱን 106.95 በመቶ ማሳካት ተችሏል።ይህ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 10.85 ቢሊዮን ብር ወይም 34.48 በመቶ ብልጫ አለው።
አዲስ ዘመን፡- የስድስት ወራት የገቢ ዕቅድና አፈጻጸም ስኬታማነት አስተዋፅኦ ያደረገው ምንድ ነው? ለውጤቱ ያበቃችሁ ምን እንደሆን ገምግማችኋል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ቢሮው በስድስት ወር ለመሰብሰብ በዕቅድ ከተያዘው 39 ነጥብ 55 ቢሊዮን ብር፣ 42 ነጥብ 29 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 106 ነጥብ 95 በመቶ ማሳካት ችሏል።ይህ አፈጻጸም ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 10 ነጥብ 85 ቢሊዮን ብር ወይም 34 ነጥብ 48 በመቶ ብልጫ አለው፡፡
ቢሮው የህግ ዘርፍ የበጀት ዓመቱን የገቢ ዕቅድ ለማሳካት ከአጋር እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በጋራ በመንቀሳቀስ፣ ግብርን በፍቃደኝነት የመክፈል ባህልን እንዲያድግ በማድረግ፣ ታክስ ከፋዩን ማህበረሰብ በልዩ ልዩ የግንኙነት አግባቦች በማስተማር፣ በመደገፍ እና እውቅና በመስጠት እንዲሁም የህግ ተገዥነትን በማሳደግ ለስድስት ወራቱ ዕቅድ ስኬት የበኩሉን ሚና ተወጥቷል፡፡
ከሞደርናይዤሽን ሥራዎች አኳያም ቢሮው የተገልጋዩን እርካታ በላቀ ደረጃ ለማረጋገጥ የግብር ክፍያን የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮችን እየተጠቀመ ነው።እስካሁን ተቋሙ የሲ.ቢ ኢ፣ የቴሌ ብር እና የ7075 የውስጥ የስልክ መስመሮችን በመጠቀም ፈጣን መስተንግዶ መስጠት ከማስቻሉ ባለፈ የብልሹ አሰራር መንስኤዎችን ለመቀነስ ዓይነተኛ ሚና ተወጥቷል።ይህም ለስድስት ወሩ የዕቅድ ስኬት አስተዋፅኦ ነበረው።የታክስ ስራዎች በተመለከተም ቢሮው በታክስ ዙሪያ ግብር ከፋዩ የነቃ ግንዛቤ ይዞ ግብሩን በወቅቱ እንዲከፍል በኦዲት፣ በገቢ ሂሳብ እና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ስራዎች
በቅድመ ሁኔታ መሰራታቸው ለገቢ መጨመርና ለዕቅዱ መሳካት ጉልህ ድርሻ አብርክቷል።
አዲስ ዘመን፡- ቢሮው የባለጉዳዮችን ቅሬታ ለመፍታት ብሎም በፍጥነት ለማስተናገድ ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አኳያ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሙሉጌታ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የገቢውን አቅም ለማሳደግ አንዱና ትኩረት የሰጠው ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም ነው።በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎች የድምር ውጤታቸው የተሻለ እንደሚሆን እናምናለን።በተለያዩ አግባቦችም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ነው የምንሠራው።ቴክኖሎጂ ሁኔታዎችን ጊዜ እና ገንዘብን ከመቆጠቡም በተጨማሪ አሰልቺ አሰራሮችን ለመቅረፍ ይጠቅማል። ቴክኖሎጂ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ያዘለ ነው።በተለይም ብልሹ አሰራሮችን በመቅረፍ ረገድ ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ የለውም።ይህም በመሆኑ በቴክኖሎጂ ላይ ትልቅ ትኩረት አድርገናል።
ለምሳሌ ግብር ከፋዮች ከአንድ በላይ አካውንት ሊኖራቸው ስለሚችል ብዙ አማራጮችን ተጠቅመናል።ይህም የግብር ከፋዮችን ምቾትና ፍላጎት ለመጠበቅ ስንል ከሀገራችን ካሉ አስራ ስድስት ባንኮች ጋር እንደ አስፈላጊነቱ እየሠራን ነው።ይህም በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እያገኘን ነው።
ከኢትዮ- ቴሌኮም ጋርም በመነጋገር አስፈላጊ የሚባሉ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በመጠቀም ደንበኞቻችን ላይ የምንሰበስበውን ግብር ለማሳካት ጥረት እያደረግን ነው።ከዚህም በተጨማሪ 7075 ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ መረጃ የሚያገኙበት አጭር መስመር ጥቅም ላይ አውለናል።በዚህ መስመር የሚፈልጉትን ጥያቄ ማንሳት ይችላሉ።በቂ ማብራሪያ የሚሰጣቸው ይሆናል።ይህ ለደንበኞቻችን ብቻ ሳይሆን ስለተቋሙ የተለያዩ አሰራሮችን እና ተግባራትን ለማወቅ ለሚሹ አካላትም ትልቅ ፋይዳ እየሰጠ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ተቋም በባህሪው ከፍተኛ ገንዘብ የሚሰበስብ ነው።ለሙስና ቀዳዳ የሚከፍቱ አሰራሮችም አሉ። በዚህ በኩል አመራሮችና ባለሙያዎች ለሙስና እንዳይጋለጡ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- ቢሯችን ሙስናን በመዋጋት ረገድ ከአመራር እስከ ሰራተኛ በተናበበ መንገድ ይሰራል።ሙስና ማለት የአንድ ሀገር የዕድገት ፀር ነው።ይህም በመሆኑ በዚህ ላይ ትልቅ ትኩረት ነው የምንሰጠው።ይሁንና ግን አሁንም ሙሉ ለሙሉ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን አስቀርተናል ማለት አይቻልም። ሆኖም ተቋማችን ይህን ለማስቀረት ትኩረት ሰጥቷል፡፡
ለአብነትም በጎ ግብር ከፋይ እና በጎ ባለሙያ ማፍራት አለብን በሚል በስፋት እየሰራን ነው።ይሁንና በተለያዩ ወቅቶች አግባብነት የጎደለው ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትን እያገኘን ነው።በዚህ ላይ የተገኙት ላይ ደግሞ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ ቀጥለናል፡፡
በዚህ ዓመት እና ባለፈው ዓመት ከዚህ ጋር በተያያዘ 260 ባለሙያዎች ላይ እርምጃ ወስደናል።እርምጃው የየራሱ ሂደት እና ህጋዊ አግባብ ያለው ነው።ይህም እስከ ሥራ ማባረር የደረሰ እርምጃ ነው የተወሰደው ።ይህ ግን ሙሉ ለሙሉ ችግሩን ለመቅረፍ አስችሎናል ብለን አንቀመጥም።ብዙ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አሉ።ግብር በባህሪው ብዙ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት እና ባለጉዳዮችም በርካቶች ስለሆኑ መሰል ድርጊቶች እንደሚኖሩ ታሳቢ አድርገን በጥንቃቄ እንሰራለን።ባለሙያዎችም ሆኑ አመራሮች ከመሰል ድርጊቶች እንዲታቀቡ በየጊዜው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንሰራለን። በተጨማሪም የድጋፍ እና ክትትል ስራችንም በተጠናከረ ሁኔታ የሚካሄድ ነው የሚሆነው።በውስጣዊ አሰራሮችም ጠንካራ ዲስፕሊን እንከተላለን፡፡
ሙስና እና ብልሹ አሰራር በባለሙዎች ብቻ የሚገለፅ በዚያው የተወሰነ አይደለም።ስለዚህ ከግብር ከፋዮች አኳያም 1000 ግብር ከፋዮች ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃዎች ተወስዶባቸዋል። ከዚህ አለፍ ብሎ ወንጀል ፈጽመው የተገኙትን ደግሞ ከከተማው የፍትህ አካላት ጋር በመሆን ክስ የመመስረት እና በህግ አግባብ ብይን የሚሰጥበት ሂደት አለ።በአሰራር ሥርዓቱ መሰረትም ህግና ፍትህ የሚተገበር ይሆናል ፡፡
በአጠቃላይ ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሙስና እና ብልሹ አሰራሮች የከተማዋም ሆነ የሀገሪቱ ፈተና በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራው ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ከፍተኛ ግብይት ከሚፈፀምባቸውና ግብር ስወራ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች አንዱ መርካቶ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል።ይህ ችግር አሁን ተቀርፏል?
አቶ ሙሉጌታ፡- በመርካቶ አካባቢ የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች አሉ። በዚህ ገበያ ሰፋ ያለ ነገር አለ።በህገ ወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩትን ወደ ህጋዊ መንገድ እንዲመጡና ህጋዊ የሆኑ አካላት ደግሞ እንዲበረታቱ በስፋት ሰርተናል።በዚህም 35 ሺህ የሚደርሱ ግብር ከፋዮች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው እንዲሰሩ አድርገናል።እነዚህን ተግባራት ስናከናውን ከሚመለከታቸው የፌደራል እና የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የመጣ ነው።በከተማ ካሉን ሁሉም ቅርንጫፎች እና ንዑስ ቅርንጫፎች ጋር በመነጋገር እና በመናበብ የመደጋገፍና ክትትል ሥራ እያከናወንን ነው፡፡
በመርካቶ አካባቢ ግን ብዙ በችግር የሚነሱ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው በጣም ሊበረታቱ እና ሊደነቁ የሚገቡ ጉዳዮችም መኖራቸውን ማስተዋል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ሊበረታቱ እና ሊደነቁ የሚገቡ ያሏቸውን በማሳያነት ይንገሩን ?
አቶ ሙሉጌታ፡- በዚህ አካባቢ በጣም ከፍተኛ የሆነ የቢዝነስ እንቅስቃሴ አለ።ነገር ግን በመርካቶ የምናገኘው ቢዝነስ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የህዝብ መስተጋብር ያለበት ስፍራ ነው።የኢትዮጵያን ስብጥር ቀለም የምንመለከትበት የግብይትና የመኖሪያ ሰፈር ጭምር ነው። ይህን እሴት መንከባከብና ወደ ተሻለ መስመር ማስገባት ይጠበቅብናል።መርካቶ ላይ ያለውን መልካም መስተጋብር በማጠናከርና ዘመናዊ በሆነ መንገድ በመከተል ማስቀጠል ተገቢ ነው።
መርካቶ አካባቢ መሠራት ያለበት የቀድሞው ሙሉ ለሙሉ በአዲስ አሰራርና መንገድ መተካት ወይንም ደግሞ ሌላ ገፅ ለመስጠት ሳይሆን በቴኖክሎጂ እና ህጋዊነት መስመርን በተከተለ መንገድ ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባት ነው። ይህን ሥራ በአሁኑ ወቅት ጀምረናል።ከዚህ አኳያ ከዚህ ቀደም ግብር ከፋይ የነበሩት 20ሺ የሚበልጡ አልነበሩም።ይሁንና ባለፈው ዓመትና በዚህ ዓመት ሰፊ የንቅናቄ ሥራ በመስራታችንና ግንዛቤ በመፈጠሩ በአሁኑ ወቅት 35ሺ ግብር ከፋዮች ተገኝተዋል።ሆኖም መርካቶ ውስጥ ካለው የቢዝነስ እንቅስቃሴ አኳያ ይህም በቂ አይደለም።በመሆኑም በሚቀጥለው ይህን አሰራር የማዘመንና የሚሰበሰበውን ግብር በማሳደግ ውጤታማ ማድረግ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እስካሁን ያልተሻገራቸው ፈተናዎች ምንድን ናቸው?
አቶ ሙሉጌታ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በየጊዜው የተሻሻሉ አሰራሮችን በመተግበር ላይ ይገኛል።በዚህም ደንበኞቹን ፍላጎት ለመጠበቅ እየሠራ ሲሆን በርካታ ለውጦችም እያየን ነው።ይሁንና አሁንም ድረስ መስተካከል ያለባቸውና ያልተሻገርናቸው ችግሮች አሉ።
ሀሰተኛ ደረሰኝን በሚመለከት በተደጋጋሚ ሥራ ለመስራት ሞክረናል።ይሁንና አሁንም በመሰረታዊነት ተፈቷል ማለት አይቻልም።ይህ ትኩረት የሚሻና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ጥረት የሚጠይቅ ነው።ሌላው ከተሸጠው ዕቃ በማሳነስ ዋጋ መፃፍና መንግስት ማግኘት ያለበትን ጥቅም የመሰወርም ችግር አለ።ይህን ችግር ለማቃለል ከሚመለከታው አካላት ጋር መስራትና ርብርብር በማድረግ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡
ከሸማቾች አኳያም አሁንም ችግሮች ይስተዋላል። የሸማቾችም ደረሰኝ የመጠየቅ ባህል አልዳበረም።ይህን እሳቤ ለማጠናከር እና ደረሰኝ የሚጠይቁትንም የማበረታት ሥራ መጀመር ይገባል።
በኢ-መደበኛ ሁኔታ የተደራጁና ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ፈተና ነው።ያለ ንግድ ፈቃድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችም የቢሮውና የከተማዋ ፈተና መሆኑ መታወቅ አለበት። እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ከንግድ ቢሮ ጋር በመነጋገር ወደ ታክስ መርህ እንዲመጡ እያደረግን ነው፡፡
ኢ-መደበኛ ነጋዴዎችን ህጋዊ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ነው።ከንግድ ማህበረሰብ አኳያም እስካሁን ያልተፈቱ ችግሮች አሉ።በሚወጣው መርሐ ግብር መሰረት በወቅቱ መጥተው ግብር ማሳወቅና መክፈል ላይ ከፍተኛ መጓተት አለ።በርካቶቹ ግብር ከፋዮች የሚመጡት በመጨረሻው ሠዓት ነው።ይህ ሲሆን ሥራው ላይ ጫና ይፈጥራል።ከዚህ በተጨማሪም ለብልሹ አሰራርም በር የሚከፍት ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ቀጣይ ትኩረት ምንድን ነው?
አቶ ሙሉጌታ፡- በመጀመሪያ አሁንም የሥነ ምግባር ግንባታ ሥራ ላይ በስፋት የሚሰራ ይሆናል።ሥራዎች ጥናትን መሰረት ያደረጉ መሆን እንዳለበት መግባባት ላይ ተደርሷል።ለግብር ከፋዮችም ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት አድርገናል።አገልግሎት አሰጣጣችን በተጠናከረ መንገድ ማስኬድና ሌላኛው የትኩረት ነጥብ ነው።ከዚህም በተጨማሪ የተገልጋዮችን ምቾት ለመጠበቅና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት የምንተገብርና የምንጠቀም ይሆናል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር በማስገባታችን በግብር ከፋዩና በፈፃሚው መካከል የነበረውን ግንኙነት መቀነስ መቻሉ የሥነ ምግባር ጉድለቶችን ማሻሻል ተችሏል። በቀጣይም በመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ወይንም ስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀማችን ግምገማ በመነሳት የተገኙ መልካም ውጤቶችን በማስቀጠል የነበሩ ተግዳሮቶችን በአሠራር በመፍታት የቀጣይ የገቢ አሰባሰባችንን በላቀ ደረጃ በማሳለጥ ዕቅዳችንን ለማሳካት በቀሪው ጊዜ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ለነበርዎት ቆይታ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥር 17 ቀን 2015 ዓ.ም