የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) በአልጄሪያ እየተካሄደ በሚገኘው የቻን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ መሳተፍ ቢችሉም የምድብ ጨዋታዎችን መሻገር ሳይችሉ በጊዜ ተሰናብተዋል። ይህ ቡድን ወደ አልጄሪያ ከመጓዙ በፊት ቢያንስ ከምድብ የማለፍ ተስፋ የተጣለበት ነበር። አሰልጣኝ ውበቱ አባተም ከወራት በፊት ተጨማሪ የሁለት ዓመት ኮንትራት ሲሰጣቸው በዚህ ውድድር ከቀደሙት ሁለት ተሳትፎዎች የተሻለ ስኬት የማስመዝገብ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አይዘነጋም። ያምሆኖ በውድድሩ እጅግ ደካማው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው የታየው።
ዋልያዎቹ የምድብ ጨዋታቸውን ደካማ ተደርጋ ከተቆጠረችው ሞዛምቢክ 0ለ0 ከመለያየት ውጪ በአልጄሪያ 1ለ0፣ በሊቢያ ደግሞ 3ለ1 ተሸንፈው ውድድሩን ቋጭተዋል። ይህም የኢትዮጵያን ሶስተኛ የቻን ተሳትፎ ካለፉት ሁለት ተሳትፎዎች የባሰ እንጂ የተሻለ ስኬት እንዳያስመዘግብ አድርጎታል። አሰልጣኝ ውበቱም የተሻለ ስኬት ያስመዘግባሉ ተብሎ ተስፋ ቢጣልባቸውም በመጀመሪያው ተሳትፎ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እንዲሁም በሁለተኛው ተሳትፎ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ካስመዘገቡት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ሳይችሉ ቀርተዋል። ከውጤቱም በላይ ዋልያዎቹ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴና በአጠቃላይ የነበሩባቸው በርካታ ክፍተቶች የኢትዮጵያን እግር ኳስ ደረጃ ቁልጭ አድርጎ ከማሳየት በዘለለ ከወቀሳ አላዳናቸውም። ለዋልያዎቹ ጥሩ የማይባል የቻን ውድድር ቆይታ ከእግር ኳሱ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ባሻገር መታየት የሚገባቸው ክፍተቶችም አገርን ዋጋ ማስከፈላቸው አልቀረም።
ዋልያዎቹ በተለይም በመጀመሪያው የሞዛምቢክ ጨዋታ አሸንፈው የበለጠ መነቃቃት መፍጠር የሚችሉበት እድል መምከኑ ብዙዎችን አስቆጭቷል። በአጠቃላይ ቡድኑ በቀጣይ ጨዋታዎች ላይ ለመፍረክረኩም የመጀመሪያው ጨዋታ የራሱ ተጽእኖ ነበረው። በዚህ ጨዋታ ዋልያዎቹ በርካታ የግብ እድል ቢፈጥሩም ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ለዚህም ቡድኑ ልምድና ብቃቱ ያለው ጨራሽ አጥቂ ማጣቱ ዋጋ አስከፍሎ ታል። ባለፉት በርካታ ዓመታት የዋልያዎቹ ግብ አዳኝ የሆነው ጌታነህ ከበደ ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር የገቡበት እሰጥ አገባ ለተከፈለው ዋጋ ዋነኞቹ ተጠያቂዎች ናቸው። ጌታነህና አሰልጣኝ ውበቱ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው የተፈጠረው አለመግባባት በቻን ቡድኑ ምርጫ ላይ መፈጠር አልነበረበትም። ወሳኙ አጥቂ ጥሪ ከተደረገለት ቀን ዘግይቶ በመምጣቱ አሰልጣኙ በዲስፕሊን ምክንያት እንደቀነሱት መናገራቸው ይታወቃል። በመጀመሪያ ተጫዋቹ የአሰልጣኙን መመሪያ ማክበር ነበረበት። ቀጥሎም አሰልጣኙ ተጫዋቹን ከቡድኑ ከመቀነስ በፊት ለአገር ውጤት ሲባል ነገሮችን ግራና ቀኝ መመልከት ነበረባቸው። አንዳንዴ ነገሮች ደረቅ በሆኑ መርሆዎች ብቻ ሲመሩ እንዲህ አይነት ጣጣ እንደሚያመጡ ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ፌዴሬሽኑም ለእንዲህ አይነት ችግሮች በአሰልጣኙ ስራ ጣልቃ መግባት ተገቢ ባይሆንም ሁለቱንም አካላት ለማግባባት ያደረገውን ጥረት በይፋ አላየንም። ዞሮ ዞሮ በሁለቱ አካላት እሰጥ አገባ የተጎዱት ግለሰቦች ሳይሆኑ አገር ናት።
ቴክኒካዊ የሆኑ ጉዳዮችን በዝርዝር ለመመልከት አስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንድ ወሳኝ ነጥቦችን ማንሳት የግድ ነው። በቡድኑ ውስጥ ለእያንዳንዱ ቦታ ምርጡን ተጫዋች የመምረጥ እና ጠንካራ አንድ ቡድን የማቀናጀት ጽንሰ ሃሳብ የእግርኳስ ዓለምን የለወጠ እና የገዛ የዘመኑ ምርጥ ዕቅድ ነው። አንድ ቡድን እቅድ ከሌለው ሁሌም መፍረክረኩ አይቀርም። መሸነፍ ተፈጥሯዊ ቢሆንም ትልቁ ችግር የሽንፈቱን ምክንያት አለማወቅ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሁልጊዜም ችግር ደግሞ ሲያሸንፍም ያሸነፈበትን ምክንያት ሲሸነፍም የተሸነፈበትን ምክንያት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አለማወቁ ነው። የሽንፈትን ምክንያት ማወቅ ወደ ዋናው እቅድ ይወስድሀል። ማስተካከል የሚገባን ነገር ለማስተካከልና የነገን የቤት ስራ ለመስራት ትልቅ ግብአት ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትልቁ ችግር ለሚፈለገው የጨዋታ እቅድ ተጫዋቾችን አለማዘጋጀት እና ተጫዋቾችን ወደ ሚፈለገው ዓላማ አለማምጣት ነው። በእግርኳስ ጨዋታ ውስጥ ትልቁ ነገር የቡድን የመጫወቻ ቅርፅ መፍጠር እና ይህንን ቅርፅ ጠብቆ መጓዝ መቻል ነው። የሜዳ ውስጥ የጨዋታ ቅርፅን ጠብቆ መጓዝ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትልቁ ችግር ነው።
አንድ ቡድን የሚጫወትበትን የጨዋታ ቅርፅ ጠብቆ መጓዝ እና በሌሎች የግል (ተናጠል)፥ እንቅስቃሴዎች አለመዋጥ ዋነኛ ዓላማው መሆን አለበት። ቡድን ማለት ያለውን ነገር የሚጠብቅ ማለት ነው። ይህ እሳቤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ የጎደለ አንድ ትልቅ ክፍተት ነው።
አንድ ተጫዋች በቦታው የሚጫወትበት ዓላማ ሲኖረው ነገሮች ቀላል ናቸው። የኳሱን ሂደት ወደ ፊት እንዲያራምዱ ለማስቻል ሶስት መአዘኖች ወይም ኳስ የመቀበያ አማራጭ በመፍጠር ለኳስ ተቀባዩ እና አቀባዩ ቦታ እና ጊዜ በመግዛት በማንኛውም ጊዜ በርካታ የቅብብል አማራጮችን በመፍጠር መቀጠል ማለት ነው። ከዚያም ተጋጣሚውን ወደ ኳሱ በመሳብ ተጫዋቹ የሚቀጥለውን ቅብብል ለመቀጠል የቡድን ጓደኛውን በሌላ ቦታ ነፃ ያወጣዋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተጫዋች ብቃት ችግር ሳይሆን ተጫዋቹን የማብቃት መሰረታዊ የእሳቤ ክፍተት አለ። ይህንን ማሳደግ፣ መስራት እና መሸከም የሚችል ሃሳብ ግን አሰልጣኞች ቢቀያየሩም መቀየር እንዳልቻለ ከዋልያዎቹ የቻን ቆይታ የበለጠ በግልጽ የሚያሳይ ምሳሌ ሊኖር አይችልም።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015