የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን በ1960ዎቹ የታተሙ ጋዜጦችን ዘገባ ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ በአንጋፋው ጋዜጣ አዲስ ዘመን ከታተሙ ዘገባዎች መካከል ማጭበርበር፣ የትራፊክ እና የንግድ ሥርዓት መጣስ እንዲሁም ልማት ተኮር ዜናዎች ይገኙበታል፡፡ አንዳንዶቹ ዘገባዎች ዝርዝር መረጃ በደንብ የሌላቸው ናቸው፡፡ መግቢያው ዜና ላይ የሚናገረው የገንዘብ መጠንና ማጠቃለያው ዜና ላይ የሚጠቀሰው የገንዘብ መጠን የሚለያይበት አለ፡፡ ከዚህ ባሻገር የናይጄሪያው ቢያፍራን አስመልክቶ የወጣው ዘገባ ቀደም ሲል በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ከተማ ይፍሩ የእርስ በርስ ጦርነቱን ለማስወገድ ያደረጉትን የእርቅ አውርድ ጥረት አስመልከቶ የሚያስታውሰን ነገር አለ፡፡
ለማኙ ታሰረ
ድሬዳዋ (ኢ-ዜ-አ-)፤ ጌታቸው ኃይሉ የሚባለው ሰው ሙሉ ጤንነት እያለው በሽተኛ ነኝ እያለ በመሬት እየተንፏቀቀ ሲለምን ተገኝቶ ድሬዳዋ ፫ኛ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የፈጸመው ወንጀል በማስረጃ ስለተረጋገጠበት በስድስት ወራት እስራት እንዲቀጣ ተፈረደበት ፡፡
ጌታቸው ኃይሉ ስሙን በመለዋወጥ ጀማል ኢሳ በመባል እየተጠራ ጤናማ ሆኖ ሠርቶ መኖሩን ጠልቶ የሆቴል ቤት እየተዘዋወረ በመለመኑ ሰውን ያስቸገረ እንደነበረ ሕግ አስከባሪው የሃምሳ አለቃ ከበደ ካብትህ ይመር ገለጡ፡፡
(ጥቅምት ፬ ቀን ፲፱፻፷ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
በሞተር የሚሠራ የኤሌክትሪክ መብራት ለማሠራት ብር አዋጡ
የአሩሲ ጠቅላይ ግዛት የጢቾ አውራጃ ሕዝብ ፲፭ ሺ ብር በማዋጣት በሞተር ኃይል የሚሠራ የኤሌክትሪክ መብራት ለማቋቋም ተስማማ፡፡
ኅዳር ፮ ቀን በወረዳው ገዥ ይኩኖ አምላክ ኃይለ ማርያም አማካይነት በሕዝቡ ፴፩ሺህ ብር የተዋጣ መሆኑን አቶ ፈቃደ ወንድሙ ገለፁ፡፡
(ጥቅምት ታኅሣሥ ፪ ቀን ፲፱፻፷ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ዋጋ ያስበለጡ ተቀጡ
ጅማ፣ዲላ (ኢ-ዜ-አ-) ፤ በከፋ ክፍለ ሀገር በሶኮሩና በመሐል ማጂ ወረዳዎች ኗሪ የሆኑ አራት ነዋሪዎች ከተወሰነው ዋጋ በላይ ጨው ሲሸጡ በመገኘታቸው ተከሰው በጠቅላላው ፮፻፭ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል፡፡
ከተከሳሾቹ መካከል በ፲፫ ብር ከ፶ ሳንቲም መሸጥ የሚገባቸውን አንድ ቁምጣ ጨው ከ፳፰ እስከ ፵ ብር ሲሸጡ የተገኙት አቶ ናጂ አሊ ፫፻ ብር ሲቀጡ ፤ አቶ መሐመድ ጀማልም ተመሳሳይ ጥፋት በመፈጸማቸው ፪፻፶ ብር መቀመጫ እንዲከፍሉ ፤ ባይከፍሉ ግን ፴፷ ቀናት እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን የየወረዳው ፍርድ ቤት ዳኞች ገልጠዋል፡፡
እንዲሁም አቶ አደም መሸሻና አቶ የሱፍ ትኩዬ የተባሉት ነጋዴዎች ፤ በመሐል ማጂ ወረዳ አንድ አሞሌ ጨው ከዋጋው አስበልጠው ፫ ብር ሲሸጡ በመገኘታቸው ተከሰው አድራጎታቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠ ፤እያንዳንዳቸው ፶፭ ብር መቀጫ እንዲከፍሉ የዲላ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰሞኑን በዋለው ችሎት በይኖበታል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ አቶ ሰሎሞን በርሔ የሕዝብ ማመላለሻ ሹፌር ከማዘጋጃ ቤት የሚጠየቀውን ግብር ላለመክፈል ሲል ለሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች መነሻና መድረሻ ከተከለከለው ሥፍራ ውጭ ሕዝብ ሲያሳፍርና ሲያወርድ በመገኘቱ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍል የዲላ ወረዳ ፍርድ ቤት ሰሞኑን ባዋለው ችሎት በይኖበታል፡፡
ተከሳሹ ቅጣቱ የተበየነበት መንገደኞችን ከአዋሳ ከተማ ዲላ ካደረሰ በኋላ ለመነሻና መድረሻ በተከለለው ሥፍራ በማውረድ ፋንታ ፤ መንገደኞቹን ባልተለመደበት ቦታ ደብቆ ሲያወርድ፤ ሌሎችንም ሲያሳፍር መገኘቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት ነው፡፡
ሰሎሞን ከአሁን በፊትም ለመኪናዎች መነሻና መድረሻ ከተከለለው ቦታ አላቆምም በማለቱ ተከሶ ፲፭ የተቀጣና ማስጠንቀቂያም ተሰጥቶት እንደነበር ተገልጧል፡፡
ከዚህም ሌላ ዋለልኝ ደሚ የተባለው የከባድ የጭነት መኪና ሹፌር አለደረጃው የ፫ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ይዞ በመገኘቱ ይኸው ፍርድ ቤት የ፶ ብር ቅጣት የበየነበት መሆኑን የደራሳ አውራጃ ፖሊስ ትራፊክ ሹም የአስር አለቃ ነጋሽ አብዲ ገልጠዋል፡፡
(ጥቅምት ግንቦት ፲ ቀን ፲፱፻፷፰ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ቢያፍራ መነጠል የለባትም የኮንጎ ፕሬዚዳንት
ብራዛቪል ፤(ኤ-ኤፍ-ፒ-) የኮንጎ ብራዛቪል ፕሬዚዳንት ማጆር ማሪየን ኑጉዋቢ ፤ቢያፍራ የሚለው ቃል ከክፍለ ዓለማችን ውስጥ ጨርሶ መጥፋት አለበት በማለት፤ ፌዴራል ናጄሪያን የሚደግፉ መሆናቸውን ትናንት በይፋ ማስታወቃቸው ተገለጠ፡፡
ማጆር ንጉዋቢ ይህን መግለጫ የሰጡት ፤አዲስ አበባ ተደርጎ ከነበረው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባዔ ሲመለሱ መሆኑ ታውቋል፡፡
መስከረም ፫ ቀን ፲፱፻፷፪ ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን )
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015