ለስፖርት መሰረታዊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ለልምምድ እንዲሁም ለውድድር የሚሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች በብዛትና በጥራት ያለመኖር በስፖርት ውጤታማነት ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ አለው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በተለይም ትልልቅ ስታዲየሞችን ለመገንባት ጥረት ማድረግ ከጀመረች ብትሰነብትም ውጥኖቿን ለማጠናቀቅ አልታደለችም። ይህም በስፖርት ቤተሰቡ በተደጋሚ ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ሲገነቡ ቆይተዋል፤ ሆኖም መጠናቀቅና በመስፈርቱ መሰረት መገንባት ስላልቻሉ የስፖርቱ ትልቅ ችግር ሆኖ ቀጥሏል፡፡
በተለይ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ባለመኖሩ ምክንያት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎችን በስደት ለማካሄድ ተገዷል፡፡ በዚህ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጪ ምንዛሬ እንዲወጣ አድርጓል። ከአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በተጓዳኝም የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ ሌሎች ጨዋታዎችን ለማከናወንም አመቺ ሁኔታ ባለመኖሩ ውድድሩ በተለያዩ ክልሎች እየተዘዋወረ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ውድድሩ ከአዲስ አበባ ከራቀ ሁለት የውድድር ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን፤ የከተማዋ የስፖርት ቤተሰብም በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ምክንያት የሚወደውን ስፖርት በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ለመከታተል ተገዷል፡፡
ይህንን ተከትሎም ሊጉን የሚመራው አክሲዮን ማህበር በቅርቡ የተለያዩ ጥናቶችን ባቀረበበት ሲምፖዚየም ላይ የስታዲየሞችን ጥያቄ አቅርቧል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤ ኢትዮጵያ በስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ኋላ ቀር ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ ጥቂት ስታዲየሞች ቢገነቡም ዓለም አቀፍ አወዳዳሪ አካላት በሚፈቅዱት መስፈርት መሰረት የተገነቡ እንዳልሆኑ አብራርተዋል። ይህና ሌሎች ምክንያቶች ተዳምረውም የኢትዮጵያን እግር ኳስ እንዳዳከሙት ገልጸዋል።
መቶ አለቃ ፍቃደ በንግግራቸው ‹‹በደርግ ዘመነ መንግስት የቻይና መንግስት 60 ሺ ሰው የመያዝ አቅም ያለው ስታዲየም በነጻ ለመገንባት ጥያቄ አቅርቦ ሳለ የመንግስት ለውጥ ተደረገ፡፡ በቀጣይ የመጣው መንግስትም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት የተገኘው እድል ቀረ፡፡ አሁን ደግሞ ከቻይና ተቋራጭ ጋር የግንባታ ውል በመግባት እሱም ሊሳካ አልቻለም፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳትም በተመሳሳይ ሁኔታ በመዘግየቱ ብሄራዊ ቡድኑ በስደት በሰው ሀገር ላይ ይጫወታል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግም ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ መካሄድ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህና ሌሎች ችግሮች ተዳምረውም የሀገሪቷን እግር ኳስ አዳክመዋል። በመሆኑም መቼ ወደ አዲስ አበባ ይመለሳል?›› ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስትር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ በግንባታ እና በእድሳት ላይ የሚገኙትን ስታዲየሞች ያሉበትን ሁኔታ አብራርተዋል። ወቅታዊው ሀገራዊ ጉዳይ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ቢሆንም መንግስት በፌዴራልና በክልል ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው እንዲጠናቀቁ የሚቻለውን ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የግንባታዎቹ መዘግየት ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን መንግስት ቢገነዘብም በየወቅቱ የሚያጋጥሙና ከእቅድ ውጪ የሆኑ ጉዳዮች ተጨማሪ ጊዜና ወጪ እንዲያስፈልግ ማድረጋቸውን አስረድተዋል። ከቴክኒካዊ ጉዳዮች በተጨማሪ ከቢሮ ጀምሮ እስከ ኮንትራክተሮች ያለው ሰው ወለድ ችግርም ሌላው እንቅፋት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ መንግስት በመፍትሄነት ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ በክልል የሚገነቡ ስታዲየሞችን የሚመለከት ነው፡፡ ይኸውም በገንዘብ ችግር ምክንያት በመሆኑ ሚኒስትሩ ስፖንሰሮችን በማፈላለግ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በማስተሳሰርና ብድር እንዲያገኙ በማድረግ ስራዎቹ እንዲቀጥሉ እየተደረገ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። በፌዴራል ደረጃ የሚገነቡትን በሚመለከትም በተለይ የአዲስ አበባ ስታዲየም ለቀጣይ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የብሄራዊ ስታዲየም ግንባታ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ እንዲሁም በሀገሪቷ በነበረው ሁኔታና ባጋጠመው የፋይናንስ ችግር፣ ይህን ተከትሎም በተፈጠረው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረትን ማስተናገድ የግድ ሆኗል፡፡ ቀድሞ ለመስራት ከስምምነት የተደረሰው ከ5ቢሊየን ወደ 20ቢሊየን ብር ተጠይቋል፡፡ ይህም ለአንድ ዘርፍ ሀገሪቷ ካላት ውስን ሀብት ለዚህ ለማዋል ስለማይቻል ድርድር አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ከቻይና መንግስት ጋር ባለው መልካም ግንኙነት የዋጋ ንረቱ እንዲቀንስ የተለያዩ ጥረቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ.ም