በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ረጅም አመታትን ካስቆጠሩ አንጋፋ የስፖርት መድረኮች አንዱ በሠራተኞች መካከል የሚካሄደው ውድድር ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) አማካኝነት በየአመቱ በሦስት የተለያዩ መድረኮች የሚካሄዱ ስፖርታዊ ውድድሮች በርካታ ቁጥር ያለው ተሳታፊ የሚያስተናግዱ ናቸው። የበጋ ወራት ውድድሮች፣አገር አቀፍ የሠራተኞች ውድድርና ዓለም አቀፉን የሠራተኞች ቀን መታሰቢያ (ሜይዴይን) አስመልክቶ የሚካሄዱት ሦስት የውድድር መድረኮች በተለይም ለሠራተኛው ብዙ ትርጉም ያላቸው፣ እንደ አገርም ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያስገኙ ናቸው። እነዚህ የውድድር መድረኮች የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞቻቸውን የሚያሳትፉባቸው ቢሆኑም የኮቪድ-19 ወረርሽን 2012 መጋቢት ላይ ከተከሰተ በኋላ ባለፉት ሦስት አመታት ተቋርጠው ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ይህ ተወዳጅ የስፖርት መድረክ ካለፈው እሁድ ጀምሮ ለስድስት ወራት በሚቆየው በበጋ ወራት ውድድር ተመልሷል፡፡ ይህም በሠራተኛው ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡
የሠራተኛው የበጋ ወራት ውድድር በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ወደ ውድድር ሲመለስ በመክፈቻ ሥነሥርዓቱ በእግር ኳስና አትሌቲክስ እንዲሁም አዝናኝ በሆነው የገመድ ጉተታ ውድድር የተለያዩ ፉክክሮች ተደርገዋል፡፡
በውድድሩ መክፈቻ ሥነሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ፣ ‹‹ያለፉት ሦስት አመታት ስፖርት በተለይም ለእኛ ለሠራተኞች ምን ያህል አቀራራቢ እንደነበረና በኮቪድ-19 ወረርሽን ምክንያት ተራርቀን በቆየንባቸው ጊዜያት አለመገናኘትና መራራቅ ምን ያህል እንደሚያረሳሳን በተግባር ያየንበት ጊዜ ነው። የሠራተኛው ስፖርታዊ መድረክ ጤናማ፣ ንቁና አምራች ዜጎችን ከመፍጠርና ሠራተኛውን እርስበርስ ከማቀራረብ ባለፈ ምርጥ የአገር ስፖርተኞች የሚገኙበት መድረክ ነው። የሠራተኛው ስፖርት መድረክ በወረርሽኙ ምክንያት ተቋርጦ በቆየበት ጊዜ በርካታ ቅን አሰሪዎች የስፖርትን ተቋማዊና አገራዊ ፋይዳ ተረድተው ሠራተኞቻቸውን በተለያዩ አማራጭ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሳተፉ አድርገዋል›› በማለት ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ስፖርት ተቋማዊና አገራዊ ገጽታን የማስተዋወቅና የመገንባት አቅም ያለው መድረክ መሆኑን ሌሎችም ተረድተው አርአያቸውን እንደሚከተሉም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
የኢሠማኮ ማህበራዊ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊና የስፖርት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ፍሰሃፂዮን ቢያድግልኝ በበኩላቸው፣ ‹‹በዚህ ዘመን ሠራተኛው በስፖርት የሚያደርገው ተሳትፎ ለሚሠራበት ድርጅት ውጤታማነት የሚኖረውን አስተዋጽኦ አሰሪዎች በቀላሉ የሚረዱት ነው። በመሆኑም ስፖርቱ የሠራተኛውን አንድነትና ለጋራ ጉዳይ አብሮ የመቆም ባህሉን ያጠናክራል። በአሰሪና ሠራተኛው መካከልም ጥሩ ግንኙነት እንዲዳብር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል›› ያሉ ሲሆን ኢሰማኮም ይህን በመገንዘብ በእቅድ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ለሠራተኛው የራሴ የሚለው ስፖርታዊ ውድድሮችን ማዘጋጀት መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም የበጋ ወራት ውድድር፣ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን መታሰቢያ የሜይ ዴይ ውድድር እንዲሁም የአገር አቀፍ የሠራተኞች ውድድሮችን በስፖርት ኮሚቴው አማካኝነት እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡
በሠራተኛው ስፖርት መድረኮች ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ተቋማት አንዱ የሆነው የአንበሳ የከተማ አውቶቡስ አገልግሎት ድርጅት የሠራተኛ ስፖርት ቡድን መሪ አብዱላዚዝ መሐመድ፣ ‹‹የሠራተኛው ስፖርት ተቋርጦ በነበረባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታት ብዙም እንቅስቃሴ አላደረግንም፣ ከ2013 አጋማሽ ጀምሮ ግን ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው ስፖርት ለሁሉም እንቅስቃሴ ላይ እየተሳተፍን ነው፣ በሥራ ቦታዎችም ሠራተኛው ከስፖርቱ እንዳይርቅ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ስናደርግ ቆይተናል፣ የሠራተኛው የስፖርት መድረክ ወደ ውድድር ሲመለስም በአስር የስፖርት ዓይነቶች ለመሳተፍ መጥተናል፣ የሠራተኛው ስፖርት ሲቋረጥ ሠራተኛው ላይ ብዙ ተጽእኖ ነበረው፣ ይህ መድረክ ብዙ ሰዎችን የምናገኝበት ነው፣ ይህም የመተዋወቅና ልምድ የመለዋወጥ ባህላችንን ያጎለብታል፣ የሠራተኛው ስፖርት ተቋርጦ በመቆየቱ ይህን አሳጥቶናል፣ ዛሬ ተመልሶ በመጀመሩ ግን አጥተን የነበረው ነገር ዳግም በማግኘታችን ተደስተናል፣ ጥሩ መነቃቃትም ፈጥሮብናል፣ ይሄ የውድድር መድረክ ሠራተኛው ብዙ ነገር የሚያገኝበት ነው›› በማለት ለአዲስ ዘመን አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ስፖርት በመሳተፍ በብሔራዊ በሠራተኛው ስፖርት የሚሳተፈው ሌላኛው ተቋም የቃሊቲ ብረታብረት ፋብሪካ የሠራተኞች ስፖርት ማህበር ሰብሳቢ ቶምቴሳ አወል በበኩላቸው፣ ‹‹የሠራተኞች ስፖርት ተቋርጦ መቆየቱ ትንሽ ጎድቶናል፣ ቡድናችን እንዲሳሳ አድርጓል፣ ያምሆኖ በወቅቱ ሥራ አካባቢ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ስንጥር ነበር፣ የሠራተኛው ስፖርት አሁን ወደ ውድድር መመለሱ በጣም አስደስቶናል፣ የስፖርት ፍቅር ያላቸው ጥሩ አመራሮች ስላሉንም ዘንድሮ የበለጠ ተነቃቅተን ጥሩ ተሳትፎ ይኖረናል፣ ድርጅታችን ሠራተኛው በስፖርቱ እንዲሳተፍ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ወጪ ያደርጋል፣ሠራተኛውም በራሱ መዋጮ ይደጉማል›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015