ፍቅር መልክ ቢኖረው እላለው..እምነት አካል ነፍስ ቢኖረው እላለሁ..
ሁሉም በከዱኝ ሰዓት አብሮኝ የቆመ አንድ ወዳጅ አለኝ..ኪም የተባለ። ኪም ሰው አይደለም..ውሻ ነው። ከእምነት፣ ከጽናት፣ ከፍቅር ጋር የተበጀ ውሻ። ነፍሴ ከነፍሱ ያፈነገጠችበት እለታት የላትም። በጭራዎቹ ውዝዋዜ መውደዱን ይነግረኛል።
ከኪም ጋር ነው የምኖረው። አንድም ቀን ውሻ መስሎኝ አያውቅም። እንደታናሽ ወንድም ቆጥሬ ከጎኔ እሸጉጠዋለሁ። ዓለምን ለሁለት ዞረናታል። ከኋላዬ ኩስ ኩስ እያለ ያልረገጥነው የምድር ዳርቻ የለም። የሆዴን እነግረዋለሁ..አይኖቹን ተክሎ ያደምጠኛል። ዓለም ባዶነትን በሰጠችኝ ማግስት ጎኔ የነበረው እሱ ነው። ሰዎች በራቁኝ ጊዜ፣ ማንም ባልፈለገኝ ጊዜ አብሮኝ እሱ ነበር። በጎዳና ተዳዳሪነት ትቦ ውስጥ እና አስፓልት ዳር ሳድር ኪም አብሮኝ ነበር። መጽናኛዬ ነው..ከሰው ልጅ ያጣሁትን ፍቅርና እምነት ያጎናጸፈኝ።
ከማድርበት የጎዳናው ጥግ ላይ አንድም ቀን ፊታቸውን አይቼው የማላውቀው ሲቆጡና ሲነጫነጩ ብቻ የምሰማቸው ትልቅ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ አንድ አሮጊት አሉ። እና እኚህ አሮጊት ኪምን አይወዱትም። የዘወትር መነጫነጫቸው ኪም ነው። ‹በሽታዬ የሚነሳው ይሄን ውሻ ሳይ ነው ግቢዬ እንዳይገባ› ሲሉ ዘወትር እሰማለሁ። ለምን እንደሚጠሉት ግን አላውቅም። ሳት ብሎት ግቢያቸው ከገባ ‹‹ይሄን ሰላቢ ጥቁር ውሻ ከግቢዬ አባሩልኝ› ሲሉ እንደ እሳቸው ከቤት ወጥተው ለማያውቁ የልጅ ልጆቻቸው ትዕዛዝ ይሰጣሉ። ያኔ ኪምን ለመምታት የማይወረወር ድንጋይ፣ የማይቅመዘመዝ ቅምዝምዝ የለም። እድል በቀናው ተመቶ እድል ባልቀናው ተስቶ ከዛ ሁሉ ዱላና ኢላማ አምልጦ እያለከለከ ወደእኔ ይመጣል። እጄን ከመላ ጥቁር መልኩ ተለይታ የልብ ቅርጽ የተሰራች ግንባሩን እያሻሸሁ አጽናናዋለሁ። ቡቺ ከዛ ቤት ከተባረረ በኋላም ግቢው ሰላም አያገኝም። መልኳን የማላውቀው አሮጊት ግሩምሩምታና ዛቻ ይሰማኛል።
‹ይሄ ገፊ ውሻ..ሁለተኛ ዝር እንዳይል እግሩን ሰብራችሁ ጣሉልኝ› ሲሉ በምሬት ይናገራሉ። በዛ ቀን የማልሰማው የእርግማንና የዛቻ አይነት አልነበረም። በነጋታው ያው ነው..ግቢያቸው ውስጥ ኪም ገብቶ የአሮጊቷ ምሬት፣ የልጅ ልጆቻቸው ቅምዝምዝ ቆርቆሮ አጥራቸው ላይ እያረፈ ይሰማኛል። ብዙ ዱላዎች፣ ብዙ ድንጋዮች፣ ብዙ ቅምዝምዞች ወደ ኪም ተነጣጥረው ሲመቱትና ሲስቱት አደምጣለሁ። እዛ ግቢ ውስጥ የኪም ስቃይ ይሰማኛል። ድንጋይ ሲያርፍበት የሚያወጣው የስቃይ ድምጽ ነፍሴን ለሁለት ይተረክካታል።
በዛ ግቢ ውስጥ የቡቺ ስቃይ የኔ ስቃይ ነበር። በር ተዘግቶበት በነዛ ሁሉ ክፉ እጆች ሲቀጠቀጥ የኔ ነፍስ ነበር የምትሰቃየው። አስፓልቱ ዳር ሆኜ ኪም ላይ የተወረወሩትን፣ የተምዘገዘጉትን፣ የተወነጨፉትን ጉልጥምቶች እቆጥራለሁ። አስፓልቱ ዳር ሆኜ ኪም ላይ የተነጣጠሩትን፣ የታለሙትን ድንጋዮች አሰላለሁ። ቡቺ ላይ ያለሙ እነዛን እጆች፣ ቡቺን የመቱ እነዛን ጎለንጓዮች እረግማቸዋለው። ቆርቆሮ አጥራቸው ቡቺን በሳቱ ብዙ ድንጋዮች፣ ብዙ ጉልጥምቶች ሲደበደብና ሲያቃስት እሰማለሁ። በቆርቆሮው ስቃይ እፎይ እላለሁ..ቡቺን ስተው ቆርቆሮው ላይ ባረፉ ድንጋዮች የተመስጌን ጸሎት አደርሳለሁ። ያ ሁሉ ድንጋይና ቅምዝምዝ አርፎበት ቢሆን ስል ይሰቀጥጠኛል። አጠገቤ ደርሶ የሆነውን እስካይ ድረስ ነፍሴ በመከራ ውስጥ ናት። አንዳንድ ቀን በለስ አይቀናውም ተመትቶ እያነከሰ አሊያም ደግሞ በደም ተጨማልቆ ወደ እኔ ይመጣል። ዛሬም የሆነው ይሄን ነበር። ቡቺ ግንባሩ ላይ ተፈንክቶ..እግሩ ተሰብሮ እያነከሰ መጣ። ሁሌ እንዲህ ሲሆን በለቅሶ ነው የምቀበለው። እዚህ ዓለም ላይ እንደ ኪም ጉዳት የሚጎዳኝና የሚሰብረኝ የለም። ኀዘኑ ይጎዳኛል..ህመሙ ያመኛል። ለፍቅር ብቻ የተፈጠረች ነፍሱ ፍቅርን በማያውቁ የሰው ልጆች እንዲህ መሰቃየቷ ሰው መሆኔን እንድጠላ ያደርገኛል።
ቡቺን ከነደሙ አቅፈዋለሁ። ጉያዬ ውስጥ አስገብቼው እንሰቀሰቃለሁ። ምላሱን ጎልጉሎ ይሄ ነው በማይባል ስቃይ እያለከለከና እየተንዘፈዘፈ ፊቴ ሳገኘው እሰበራለሁ። እየደባበስኩ ላጽናናው እሞክራለሁ። በዛ ሁሉ መከራው ውስጥ ጭራውን ይቆላልኛል።
ይሄ ብቻ አይደለም..
ሙሉ ጸጉራቸው ሽበት የወረሰው በምርኩዝ የሚሄዱ አንድ አዛውንት እዛ ግቢ አውቃለሁ..መልኳን የማላውቀው ሴትዮ ባለቤት ስለመሆናቸው ነጋሪ አላሻኝም። እናም እኚህ ሰውዬ ቤታቸው አጠገብ ካለው አስፓልት ዳር ስለምንተኛ ግዛታቸውን የቀማናቸው ያክል ነው የሚሰማቸው። ሲወጡና ሲገቡ በአይናቸው እንደገረመሙን ነው..እኔና ኪምን።
የኪምን ሰባራ እግር አሽቼና አስሬ አዳንኩት። የግንባሩ ቁስልም ሻረለት። በዛ ሁሉ ህመሙ ውስጥ ለዛች ሴት የሚሆን ጥላቻ አጥቶ ወደ ቤቷ በመሄድ ጉልጥምት ሲጥመዘመዝበት ነበር። እግዚአብሄር ውሻን ሲፈጥር ከፍቅሩ እኩል፣ ከታማኝነቱ እኩል አንድ ጸጋን ሰጥቶታል ብዬ አስባለሁ። እርሱም ‹ቶሎ የሚሽር ቁስልን ነው›። ሰውስ ወደ ታማሚ ቤት ለጥየቃ ሄዶ ‹የውሻ ቁስል ያርግልህ! አይደል የሚለው? አይ ሰው! ራሱ ጎድቶ..ራሱ አቁስሎ የውሻ ቁስል ያርግልህ ሲል መልካም ምኞቱን ይገልጻል። እግዚአብሄር በሰው ልጅ ለተናቀው ውሻ እንኳንም ይሄን አደረገ እያልኩ ምድር ላይ እስካለሁ ድረስ አከብረዋለሁ።
አንድ ቀን ሌላ ሆነ..
ባልተፈጠረ የምለው አንድ ቀን በእኔና በኪም መካከል ተፈጠረ።
አንድ ቀን ረፋድ ላይ ኪምን የማትወደውን ሴትዮ ቤት ብዙ ውሻዎች ከበውት አየሁ። ምንድነው ስል ልደቷ እንደሆነ ሰማሁ። ወዲያው ሰማንያ ስምንት ቁጥር ያለበት ቶርታ ኬክ በብዙ ወንድና ሴት ቆነጃጅት ተይዞ ወደ ቤቷ ሲገባ አየሁ። ጎዳና እያደርኩ አብልታኝ አታውቅም። የእሷ ሰርግ፣ የእሷ ትንሳኤ ለእኔና ለቡቺ ምንም እንደሆነ እናውቀዋለን። ረፋድ ላይ ኪምን ከአጠገቤ አጣሁት። ቅልውጥና ሄዶ ይሆናል ስል እርግጠኛ ሆንኩ። ብዙ ወዳጆቹን አግኝቶ፣ ስጋ እየሸተተው አርፎ ይቀመጣል ማለት ዘበት ነው። ወዳቆሰለችው ሴትዮ ቤት ለቅልውጥና እንደሄደ አምኜ ተቀበልኩ።
ውሾች የተጠሩ ይመስል ልደቷ ላይ ብዙ ውሾች ተገኝተው ነበር..ኪምን ጨምሮ። በውሻ ተከባ ልደቷን እያከበረች ውሻ መጥላቷ አልገባህ አለኝ። ጎዳና ላይ ሆኜ ብዙ እንግዶች ስጦታ እየያዙ ከውጭ ወደ ቤት ሲገቡ እመለከታለሁ። ሙዚቃ፣ እልልታ፣ መልካም ምኞት ግቢውን ሞልቶታል።
ያን ቀን ከኪም ጋር ሳንገናኝ ቀን ሙሉ ሆነ። ወደ ግቢው ጠጋ ብዬ በስጋ ከሚጣሉ ውሾች መካከል ፈለኩት የለም። ማታ ሆነ ኪም አልመጣም። የሚያድረው አድሮ የሚወጣው ወጥቶ የሴትዮዋ ቤት ተዘጋ። ኪም ግን አሁንም አልነበረም። ይሄድበታል ብዬ ወደማስብበት ቦታ ሁሉ ፈለኩት አላገኘሁትም። የምናድርበት ትቦ ውስጥ ለመግባት እንዲመቸው የካርቶን መዝጊያውን ገርበብ አድርጌ ጠበኩት። እኩለ ለሊት ላይ ገርበብ ባደረኩት የካርቶን በር አልፎ እያዘገመ ወዳለሁበት መጣ። ያለወትሮው ሌላ ሆኖ ነበር። ጸጉሩ ቆሟል..በአፉ አረፋ ይወጣል። እየተንቀጠቀጠ አጠገቤ መጥቶ ቆመ።
የሆነውን ሳላውቅ እንደለመድኩትና እንዳስለመድኩት ግንባሩን ዳበስኩት። ጭራውን በቀስታ አንቀሳቀሰልኝ..። መቆም ስላልቻለ እያየሁት አጠገቤ ላይ ተኛ። በተኛበት ሰውነቱ ተንቀጠቀጠ..አረፋ ደፈቀ። በቃ ኪም ሞተ።
ዓለም በረሳችኝ ጊዜ፣ የሰው ልጅ በናቀኝ ጊዜ ወዳጅ የሆነኝ ወንድሜ ጓደኛዬ ተለየኝ..በቃ ልል የምችለው ይሄን ብቻ ነው። ኪም ሁሉ ነገሬ ነበር።
ከሳምንት በኋላ ፊቷን አይቼው ከማላውቀው ከቡቺ ገዳይ አሮጊት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኘሁ። ተስፋ የቆረጥኩ ሰው አይደለሁ? ሁሉንም ላደርጋት እችል ነበር። ግን ኪም ያስተማረኝ ፍቅር ነበርና ተውኳት። ቀይ ናት..እንደ ባሏ በምርኩዝ የምትሄድ። ውጪውን ቃኝታ ወደ ቤቷ ገባች።
የዓለም ማዲያት..ከፍቅር የጎደሉ አንዳንድ ነፍሶች ናቸው። ጸዳሏ ደግሞ በፍቅር የሞሉ አንዳንድ ነፍሶች።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015