ኢትዮጵያ በማእድን ሀብት የበለጸገች ስለመሆኗ መረጃዎች ያመለክታሉ። በአገሪቱ የሚመረተው ወርቅ፣ የከበሩ የጌጣጌጥ ማእድናት፣ የግንባታ ግብአቶች ለእዚህ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። ለኢንዱስትሪ ኃይል ማመንጫነት የሚያገለግለው የድንጋይ ከሰልም እየተመረቱ ካሉ የማእድን ሀብቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የብረት፣ የተፈጥሮ ጋዝ፣ ወዘተ፣ ማእድናት ባለቤት ስለመሆኗና ማእድናቱ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በስፋት ስለመገኘታቸውም መረጃዎች ያመለክታሉ።
አገሪቱ ይህን የማእድን ዘርፉን እምቅ አቅምና ፋይዳ በሚገባ በመገንዘብ በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የአስር አመት መሪ እቅድ ትኩረት ከሰጠቻቸው አምስቱ ዘርፎች አንዱ የማእድን ዘርፍ እንዲሆን አድርጋለች። ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከማዕድን ሀብቷ ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገች ትገኛለች።
አገሪቱ ከእነዚህ የማእድን ሀብቶች ይበልጥ ተጠቃሚ ስትሆን የሚታየው ግን ከወርቅ ማእድን ነው። ልማቱ በባህላዊ መንገድና በኩባንያዎች እየተካሄደ ሲሆን፣ ምርቱ ለብሔራዊ ባንክ እየቀረበ ለአገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው።
በቀጣይም ከዚህ ማእድን ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ነው። ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት 510 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለማምረት እየሰራች መሆኑን የማእድን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በቅርቡ በተለይ ለኢፕድ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት ከ510 ሺህ ኪሎ ግራም የማያንስ ወርቅ በኩባንያዎች ደረጃ እንደሚመረት ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል። ይህንን ሥራ የሚያከናውኑት ኩባንያዎች በቅርቡ ሥራ ይጀምራሉ ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ ለአብነትም በጋምቤላ ያለው ኢትዮማይንስ በሦስት ወራት ወደ ሥራ እንደሚገባና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያለው ኩርሙክ የወርቅ ኩባንያ በአምስት ዓመታት ውስጥም ወደ ምርት ይገባል ሲሉ አብራርተዋል።
በአገሪቱ የወርቅ ልማት በስፋት እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ናቸው። አምራቾቹ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅ በማምረት ይታወቃሉ። ለአብነትም ባለፈው በጀት አመት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 22 ኩንታል ወርቅ ተገኝቷል። ዘንድሮም ክልሉ 34 ኩንታል ወርቅ ለማስገባት አቅዶ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ባህላዊ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታት በሚል ባሳለፈው ውሳኔ ካለፈው ሰኔ 16 ቀን 2014 አንስቶ ከዓለም ገበያ 35 በመቶ ጭማሪ ያለው ዋጋ በመስጠት ወርቅ ሲረከብ ቆይቷል። ባንኩ ባህላዊ የወርቅ አምራቾችን ለማበረታታትና ህገወጥ የወርቅ ንግድን ለመቆጣጠር ቀደም ሲል የተለያዩ ተግባሮችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሶ፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን እያየ ከወርቅ አምራቾቹ በሚያበረታታ መልኩ ወርቅ ሲገዛ መቆየቱን በወቅቱ አስታውሰዋል። ያንን ተከትሎም አበረታች ሊባል የሚችል የወርቅ አቅርቦት ወደ ብሔራዊ ባንክ ሲገባ እንደነበርም አስታውሰዋል። የወርቅ ምርቱም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘቱን በወቅቱ መግለጹን ባንኩ በወቅቱ የሰጠው መረጃ ያመለክታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከአነስተኛ ወርቅ አምራቾች ወደ ባንኩ መግባት ያለበት ወርቅ መጠን እያሽቆለቆለ መሆኑን በተያዘው 2015 በጀት አመት መግለጹ ይታወሳል። ለእዚህ ምክንያቱ የወርቅ ህገወጥ ግብይት መሆኑ እየተጠቆመ ነው። የፌዴራል መንግይት የተለያዩ አካላትና የክልል አካላትም በወርቅ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ግብይት ለማስቆም እየሰሩ ያለበት ሁኔታም ይህንኑ ያመለክታል። ከጋምቤላ ክልልና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ያገኘናቸው መረጃዎችም በወርቅ ግብይት ላይ ህገወጥ ተግባር እየተፈጸመ መሆኑን ያመለክታሉ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማእድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ ባለፈው ሳምንት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ ክልሉ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት በኩል በኮንትሮባንድ ንግድ የተነሳ ችግር ገጥሞት ቆይቷል። በክልሉ የሚመረተው ወርቅና ለብሔራዊ ባንክ ገቢ የሚደረገው ወርቅ መጠን ሰፊ ልዩነት እየታየበት ነው። በክልሉ ወርቅ በብዛት የሚመረት ቢሆንም፣ እዚህ የሚታየው ቅናሽ ነው ብሔራዊ ባንክ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ቅናሽ እንዲታይ እያደረገ ያለው ሲሉም ኃላፊው አስታውቀዋል።
አቶ ካሚል እንዳሉት፤ በኮንትሮባንድ ንግድ ሳቢያ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው የወርቅ መጠን በጣም ቀንሷል። ይህ ብቻም ሳይሆን ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚሰበሰበው የወርቅ መጠንም በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።
ቀደም ሲል በክልሉ በሳምንት አልገባም ከተባለ ሰኞ ሰኞ ብቻ 10 ኪሎ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረግ እንደነበር ኃላፊው አመልክተው፣ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ ከ20 እስከ ሰላሳ ኪሎ ግራም ይገባ ነበር ሲሉ ያስታውሳሉ። ይህ መጠን አንዳንዴ 40 ኪሎ ግራምም ይደርስ እንደነበርም ጠቅሰው፣ አሁን ግን ሰኞ ብቻ አስር ኪሎ ይገባ የነበረው ወርቅ ወደ ሁለት ኪሎና ሦስት ኪሎ ወርዷል። በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ኪሎ የገባበት ጊዜም አለ ሲሉ ነው ያብራሩት።
ኃላፊው ክልሉ በተያዘው 2015 በጀት አመትም 34 ኩንታል ወርቅ ለማምረት ማቅዱን ጠቁመው፣ በዚህ ስድስት ወር ወደ 18 ኩንታል ወርቅ ለማምረት ታቅዶ አንደነበርም አስታውሰዋል። በዚህ ስድስት ወር ወደ ሦስት መቶ ኪሎ ግራም ነው ያገኘነው ይላሉ፤ ይህም በጣም ትንሽ መሆኑን ነው ያመለከቱት።
በጋምቤላ ክልል በግብረ ኃይል እየተከናወነ ያለውን የህገወጥ ወርቅ ግብይት ተግባር የመከላከልና መቆጣጠር ሥራን ተከትሎ መሻሻሎች እንዳሉ ቢጠቆምም፣ ችግሩ አሁንም እንዳለ ነው እየተጠቆመ ያለው።
በጉዳዩ ላይ ማዕድን ሚኒስቴር ማንኛውም ልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራች በእጁ ያለውን ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲያስገባ አሳስቦ፣ በቀጣይ መንግሥት ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ወርቅ ወደ ብሔራዊ ባንክ በማያስገቡት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስቦም እንደነበር ከሚኒስቴሩ ድረገጽ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። ሚኒስቴሩ በፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር የሚመራ የተቀናጀ የማዕድን ቁጥጥር ኦፕሬሽን ቡድንና በጋምቤላ ክልል በዲማ ወረዳ ከሚገኙ ከልዩ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ጋር ውይይት አድርጎም እንደነበር መረጃው ይጠቁማል።
የውይይቱ ዓላማ ህገወጥ የወርቅ ኮንትሮባንድ በመቆጣጠር በዲማ ወረዳ የሚመረተው ወርቅ በህጋዊ መንገድ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ለማስቻል ነው። ማዕድን ሚኒስቴር በወርቅ ኮንትሮባንድ ዙሪያ እንደ አገር 4 ቡድን አደራጅቶ ወርቅ በሚመረትባቸው አካባቢዎች ማሰማራቱንና ከዚህ አንዱ ዲማ ወረዳ በመሆኑ ከጥቅምት 23 ጀምሮ የተላከው ቡድን ሥራውን በመጀመር ያሉትን ችግሮች እንደለየ በድረገጹ አመልክቷል።
በሥፍራው የተሰማራው ቡድን ባደረገው ቁጥጥር ከአካባቢው በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም 10 ኪሎግራም፣ በኅዳር ወር 2015 ዓ.ም 18 ኪሎግራም ወርቅ ብሔራዊ ባንክ እንዲገባ ማድረግ ተችሏል። ከአካባቢው መስከረም ወር ላይ ብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ግን ስድስት ኪሎግራም ብቻ እንደነበርና ቁጥጥሩ ከተጠናከረ በኋላ መጠኑ መጨመሩን መረጃው አስታውሷል። ቡድኑ ባደረገው ኦፕሬሽን በኮንትሮባንድ የወርቅ ዝውውር የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ምርመራ እየተደረገባቸውም ይገኛል።
ልማቱ በሚከናወንበት ዲማ ወረዳ ውስጥ ሆነው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ካሉት መካከል የጋምቤላ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ዋና የሥራ ሂደት አቶ ሙድ ሎንግ ባለፈው ታህሳስ አጋማሽ ላይ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፣ ቀደም ሲል እስከ አንድ መቶ ኪሎ ግራም ለብሔራዊ ባንክ ይገባ የነበረው ወርቅ እጅግ ነው ያሽቆለቆለው። ይህ የሆነው ወርቅ አምራቾች ከአገራዊ ጥቅም ይልቅ ራሳቸውን በማስቀደማቸው ነው። ያመረቱትን ወርቅ ለጥቁር ገበያ ነው የሚያቀርቡት። ክፍተቱ የተፈጠረው ከቁጥጥርና ክትትል መላላት ነው።
በፀጥታ ኃይል በመታገዝ ከባለድርሻ አካላት ከተውጣጣ ግብረኃይል ጋር ከሦስት ወራት በፊት የተጀመረው የተቀናጀና የተጠናከረ የቁጥጥር ሥራ ለውጥ ማስገኘቱንም አቶ ሙድ ተናግረዋል። ከግብረ ኃይሉ ጋር የመከላከሉን ሥራ ለመሥራት ከጥቅምት ወር መጨረሻ ጀምሮ የወርቅ ልማቱ በሚከናወንበት ዲማ ወረዳ ውስጥ የሚገኙት አቶ ሙድ፣ የቁጥጥር ሥራው ከተሰራበት ጊዜ ጀምሮ በተከናወነው የቁጥጥር ሥራ ለብሔራዊ ባንክ የገባው የወርቅ መጠን ከ10 ኪሎ ግራም ወደ 18 ኪሎግራም ከፍ ብሏል።
የቁጥጥር ሥራውን ለመሥራት የተዋቀረው የግብረ ኃይል ቡድን የተጠናከረ ሥራ እንዲሰራ ተጨማሪ ጊዜ በስፍራው እንዲቆይ መደረጉንም ተናግረዋል። በግብረኃይሉ ህገወጥነትን ለመከላከል የተዘረጋው አሰራር በዘላቂነት ለሚወሰደው እርምጃም ጥሩ መፍትሄ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ ወረዳውና ዘርፉን የሚመራው አካል ተቀናጅተው አሰራሩን በማስቀጠል ቁጥጥርና ክትትሉን ለማጠናከር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማእድን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሀመድ፣ በክልሉ በጣም ብዙ ወርቅ እንደሚመረት ጠቅሰው፣ ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው ግን እየቀነሰ ነው ይላሉ። ለእዚህ ትልቁ ችግር ጥቁር ገበያ ነው፤ ድርጊቱ የሚፈጸመው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ችግር ለመፍጠር ሆን ተብሎም ሊሆን ይችላል ሲሉም ያብራራሉ።
‹‹ወርቅ የአገር ሀብት ነው፤ ማንም እንደፈለገው ብቻውን የሚያድግበት አይደለም›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹ቁጥጥር የሚያደርግ ግብረ ኃይል እንደ ክልልም አለ። ከፌዴራል አካልም ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው። በዚያ ልክ ግን ለውጥ ሊመጣ አልቻለም።›› ሲሉ አስገንዝበዋል።
‹‹እኛ በአካባቢያችን የሚመረተው ወርቅ አገር ሊገነባ በሚችል መልኩ መገበያየት አለበት ብለን አቋም ይዘን እየሰራን ነው፤ የሚያስፈልገውን ጥበቃና ቁጥጥር ለማድረግ፣ እርምጃም ለመውሰድ ዝግጅት ተደርጓል ሲሉ ነው እሳቸውም ያመለከቱት። የኮንትሮባንድ መቆጣጠር ግብረኃይል በተለይ በወርቅ ላይ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
እኛም ህገወጥ እና ህጋዊውን ነጋዴ መለየት ላይ ችግር እንዳለ ተረድተናል ሲሉም ጠቅሰው፤ ህገወጦች እንደፈለጉ የሆኑት በቁጥጥራችን መላላት ነው ብለን አይተናል ሲሉም ተናግረዋል። በደንብ ከተቆጣጠርን ህገወጡ ወደ ህጋዊነት የማይመጣበት ምንም ምክንያት አይኖርም ነው ያሉት። ይህን ችግር ለመፍታት ሁሉም ዜጋ /በማምረቱም ሆነ በግብይቱ የተሰማራም ያልተሰማራም/ የኮንትሮባንድ ንግዱን በመከላከልና በመቆጣጠሩ ሥራ መሳተፍ እንደሚኖርበትም አስገንዝበዋል። ኮንትሮባንዲስቶችን መቆጣጠር ከቻልን እቅዳችንን ማሳካት እንችላለን ሲሉም አመልክተው፣ ወርቅ ስላልተመረተ አይደለም ዝቅተኛ አፈጻጸም የተፈጸመው፤ በኮንትሮባንድ ንግዱ ሳቢያ ነው ይላሉ።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አስፋ፣ የአገር ኢኮኖሚን እየጎዳ የሚገኘውን ህገ-ወጥ የወርቅ ንግድን ለመግታት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በያዝነው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ፣ የማእድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ጨምሮ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወርቅ ማዕድን ልማት ከተመለከቱ በኋላ በዘርፉ ተግዳሮትና መፍትሄዎች ዙሪያም መወያየታቸውን የኢዜአ ዘገባ ያመልክታል።
በወቅቱም የአገር ኢኮኖሚን እየጎዳ የሚገኘውን ህገ-ወጥ የወርቅ ንግድ ለመግታት ቅንጅታዊ አሰራር ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ውይይቱም የተጠናከረ ቁጥጥር ለማድረግ አቅጣጫ የተቀመጠበት መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ አንድ ወርም በህገ-ወጥ የወርቅ ዝውውር ቁጥጥር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል መሠረት ተጥሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የወርቅ አመራረት ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ ለማሸጋገር እየተሠራ ነው ያሉት የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስም፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሚመረተው ወርቅ እስከ 90 በመቶ የሚገኘው ከባህላዊ አምራቾች መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባህላዊ መንገድ ከሚመረተው የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው መጠን እየቀነሰ መምጣቱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፣ የችግሩ ምንጮች ከፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሁም ህገ-ወጥ ወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ዋነኞቹ እንደሆኑም ነው ያመለከቱት።
ይህን ህገወጥነት ለመቆጣጠርም የአገር መከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የክልል መስተዳድሮችና የጸጥታ አካላት እንዲሁም ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ኮሚቴ በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን አስረድተዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሚኒስቴሩ ፖሊሲን ከማሻሻል ጀምሮ ከሚመለከታቸው ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር የጀመራቸው የተቀናጁ ጥረቶች መኖራቸውንም ጠቅሰው፣ በተለይም የአገሪቱ የወርቅ ምርት እንዲጨምርና ለቁጥጥር በሚመች መልኩ አመራረቱን ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በበኩላቸው በአገሪቱ ወርቅ በስፋት በሚመረትባቸው አካባቢዎች እየተበራከተ ለመጣው ህገ-ወጥ ግብይት ምክንያቱ የቁጥጥር ማነስ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንንም በውይይቱ በሚገባ አረጋግጠናል ብለዋል።
“በቅርቡ ስራ እንዲጀምር ያዋቀርነው ኮሚቴም በጋራ ከሠራን ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይትን በማስቆም ሀብቱ ለሀገር ልማት እንዲውል ማድረግ የሚያስችል ውጤት ማምጣት እንችላለን” ነው ያሉት።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል ሃሚድ፤ በክልሉ ህገ-ወጥ የወርቅ ግብይት ለመቆጣጠር የተደረገ ጥረት ቢኖርም ሙሉ በሙሉ ማስቆም አለመቻሉን ተናግረዋል።
ይህም የአገር ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ ገልጸው፤ በውይይቱ የተቀመጠው አቅጣጫ ህገ-ወጥ ወርቅ አምራቾችንና አዘዋወሪዎችን ሥርዓት ለማስያዝ አቅጣጫ ያመላከተ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በባህላዊ መንገድ ከሚመረተው የወርቅ ምርት ወደ ብሔራዊ ባንክ የሚገባው መጠን እየቀነሰ መጥቷል፤ የችግሩ ምንጮች ከፍቃድ አሰጣጥ ጀምሮ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲሁም ህገ-ወጥ ወርቅ አምራቾችና አዘዋዋሪዎች ዋነኞቹ ናቸው
ኃይሉ ሳህለድንግል
አዲስ ዘመን ጥር 12 /2015