የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋልያዎቹ በሰባተኛው የቻን ውድድር የምድባቸውን ሁለተኛ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ ምሽት አድርገው በአዘጋጇ አገር አልጄሪያ 1ለ0 ተሸንፈዋል። ዋልያዎቹ የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታቸውን ከሞዛምቢክ ጋር ባለፈው ቅዳሜ አድርገው ካለምንም ግብ መለያየታቸው የሚታወስ ሲሆን የጥሎ ማለፍ ዙሩን ለመቀላቀል የፊታችን ቅዳሜ ከሊቢያ ጋር ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቃቸዋል።
ዋልያዎቹ በተደለደሉበት ምድብ አዘጋጇ አልጄሪያ ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ከወዲሁ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለች ሲሆን ሞዛምቢክ ሊቢያን 3ለ2 በመርታቷ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ ቀጣዩን ዙር የመቀላቀል የተሻለ ዕድል ይዛለች። ይህንንም ተከትሎ ከምድቡ ያልፋሉ ተብሎ የተጠበቁት ዋልያዎቹ ዕድላቸው የጠበበ ሲሆን፣ ለዚህም በሁለቱ ጨዋታዎች ያገኙትን ዕድል በአግባቡ አለመጠቀማቸው ትልቁ ምክኒያት ሆኗል።
ዋልያዎቹ በጠንካራዋ አልጄሪያ ከመሸነፋቸው የበለጠ የምድቡ ደካማ ቡድን የሆነውን ሞዛምቢክን አለማሸነፋቸው የበለጠ የሚቆጭና ዋጋም ያስከፈላቸው ነው። በሞዛምቢኩ ጨዋታ የበላይነትን ያሳዩት ዋልያዎቹ የፈጠሩትን በርካታ የግብ ዕድል ከመረብ የሚያሳርፍ አጥቂ በማጣታቸው ተቀጥተዋል። ይህ ችግር በአልጄሪያውም ጨዋታ ቢያንስ የአቻ ውጤት ይዘው እንዳይወጡ ያደረጋቸው ሲሆን ሞዛምቢክን ማሸነፍ አለመቻላቸው የበለጠ ብዙዎችን አስቆጭቷል። በአንጻሩ ደካማ የተባለችው ሞዛምቢክ ሳትጠበቅ ሊቢያን ማሸነፏ የዋልያዎቹን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።
ዋልያዎቹ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ያላቸው ዕድል ሙሉ በሙሉ ባይከስምም እጅግ ጠባብ ነው። በቀላል ስሌት ዋልያዎቹ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ በመጪው ቅዳሜ መውደቋን ያረጋገጠችው ሊቢያን ቢያንስ ሁለት ለምንም አሸንፈው ሞዛምቢክ በአልጄሪያ መሸነፍ ይኖርባታል። ይህ ደግሞ አልጄሪያ ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠች አገር እንደመሆኗ መነቃቃትና ያልታሰበ ዕድል የገጠማት ሞዛምቢክ ቢያንስ የአቻ ውጤት ካሳካች ለዋልያዎቹ አደጋ ነው። ዋልያዎቹ የሚገጥሟት ሊቢያም ብትሆን ለዋልያዎቹ በቀላሉ እጅ ትሰጣለች ተብሎ አይጠበቅም፣ ምክኒያቱም ሊቢያ መውደቋን ብታረጋግጥም ጨዋታው የክብር ፍልሚያ ይሆናልና።
«በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፤ ማሸነፍም ይገባቸዋል» በማለት ለአልጄሪያዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ «በመጀመሪያው ጨዋታ እና በሁለተኛው ጨዋታ የሰራናቸው ነገሮች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል» ሲሉ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ያም ሆኖ ቡድናቸው ያለውን ጠባብ ዕድል ተጠቅሞ ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ እንደሚፋለም አሰልጣኝ ውበቱ ገልጸዋል። «እኛ በእጃችን ያለውን ጨዋታ ማሸነፍ ነው ያለብን። ከእኛ ቁጥጥር ውጪ ስለሆነው ነገር ምንም ማድረግ አንችልም» ሲሉም አስረድተዋል።
«የአልጄሪያ ተጫዋቾች ከእኛ የተሻለ ከመጀመሪያው ጨዋታ የሚያገግሙበት አንድ ቀን ስላገኙ ትኩስ ጉልበት ነበራቸው። እነሱ ሜዳ ላይ ከእኛ የተሻሉ ነበሩ። ይህንን ተከትሎ ጨዋታው ለእኛ ከባድ ነበር። ጥሩ ተጫውተዋል። በዚህ አጋጣሚ አልጄሪያዎች ወደ ቀጣዩ ዙር ስላለፉ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ» ያሉት አሰልጣኝ ውበቱ፣ «ዛሬ ቢያንስ አቻ ብንወጣ ኖሮ ለእኛ ጥሩ ነበር። በአጠቃላይ በመጀመሪያው ጨዋታ እና በሁለተኛው ጨዋታ የሠራናቸው ነገሮች ብዙ ዋጋ አስከፍለውናል፣ በስታዲየም የነበረው ተመልካች ከ39 ሺ ይበልጣል። ስታዲየሙን የሞሉት ደጋፊዎች በሚገርም ሞራል ከተጫዋቾቻቸው ጎን ሆነው ሲደግፉ ነበር። ተጫዋቾቹም በድጋፉ እየተበረታቱ በደንብ ሲሮጡ ነበር። ደጋፊው ለቡድኑ ጥሩ አበርክቶ ነበረው። ለእንደእኛ ዓይነት ቡድን ትንሽ ጫና ነበረው፤ አንዳንዶቹ ተጫዋቾቻችን እንደዚህ ዓይነት ልምድ የላቸውም። በአጠቃላይ ደጋፊዎቹ ጥሩ ድጋፍ አድርገዋል፤ በጨዋታውም እንደተዝናኑ አስባለሁ። እንኳን ደስ አላችሁም ማለት እፈልጋለሁ። በጨዋታው ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል፤ ማሸነፍም ይገባቸዋል።» ብለዋል።
በመጨረሻ ጨዋታው ሊገባደድ ሲል ውጤቱን ሊለውጥ የሚችል ዕድል ከነዓን ማርክነህ አግኝቶ ያልተጠቀመበት አጋጣሚ እንደተለመደው ቡድኑ ማምከኑ አስቆጪ እንደነበር አሰልጣኝ ውበቱ ገልፀው የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥር 11 /2015