የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት የአትሌቲክስ ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን ከትላንት በስቲያ በስካይላይት ሆቴል ባካሄደው ጠቅላላ ጉበዔ መርጧል። በጉባኤው የምክር ቤቱ ፕሬዘዳንት፣ምክትል ፕሬዘዳንትና ዋና ጸሐፊም መርጣል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ሃገራት አትሌቲክስ ሪጅን(ዞን5) አስር ሃገራትን ያቀፈ ሲሆን፣ ምክር ቤቱን የሚመሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትም በየአራት ዓመቱ በሚካሄድ ጉባዔ ይመረጣሉ። የዘንድሮው የምክር ቤቱ ጉባኤ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት የተካሄደ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኬንያና ሩዋንዳ ተሳትፈዋል። በጉባኤው የዞኑን የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ አነስተኛ ኮሚቴም ተቋቁሟል። በጉባዔው የዞኑን አትሌቲክስ ምክር ቤት ባለፉቱ አራት ዓመታት ሲመሩ የነበሩትን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ዳግም ለመምረጥና በሌሎች ጉዳዮች ዙርያ መክሯል። በዚህም የዞኑን አትሌቲክስ ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩት ፕሬዘዳንት፣ምክትል ፕሬዘዳንትና ዋና ጸሐፊ ተመርጠው ይፋ ተደርጓል። የዞኑን አትሌቲክስ በፕሬዘዳንትነት ለመምራት የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት የሆኑት ጀነራል ጃክሰን ተዊን በድገሜ ሲመረጡ፤ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራርቱ ቱሉ ምክትል ፕሬዘዳንት ሆና በድጋሜ ተመርጣለች። ሳዲቅ ኢብራሂም ከሱዳን በዋና ጸሐፊነት መመረጣቸውም ታውቋል።
የአትሌቲክስ ዞኑ ምክር ቤት በጉባኤው የተለያዩ አጀንደዎችን በማንሳት የተወያየና አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ምስራቅ አፍሪካ የአትሌቲክስ እምቅ ሃብት ያለበት አካባቢ እንደመሆኑ ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው ተነስታል። በዓለም አትሌቲክስም በቂት ኩረትና ውክልናን እዲያገኝ አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንዲሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሌላው የስብሰባው ዋነኛ አጀንደ የነበረው የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚነት ጉዳይ ሲሆን፣ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ የህልውና ጉዳይ መሆኑንና አበረታች ቅመሞችን ለመቆጣጠር ጠንካራ ስራ መስራት እንደሚገባ አጽኖት ተሰጥቶታል። በሁሉም የዞኑ አባል ሃገራት ውድድሮች እንዲደረጉና አዘጋጅ ሃገር ትራንስፖርትን ጨምሮ ለመስተንግዶ አስፈላጊውን ነገር ማሟላት እንዳለበትም ተወስኗዋል። ጉባኤው በቀጣይም በየአባል ሃገራት እንደሚደረግ ተነግራል።
በጉበኤው እስከ አሁን እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዴት እየተሰሩ እንዳሉ ግምገማና ወደፊት አትሌቲክሱን እንዴት እናሰድገው የሚሉት ሃሳቦች ውይይት ተደርጎባቸው አቅጣጫ እንደተሰጠባቸውም ታውቋል።
የዞኑ ምክር ቤት በጉባኤው በመጪዎቹ አራት አመታት ምን ስራ እንደሚሰራ፣እንዴት እንደሚሰራና እንዴት በቅንጅትና መግባባት ስኬታማ እንደሚሆንም ምክረሃሳቦች ቀርበዋል፡፡
በጉባኤው አፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዘዳንት ሃመድ ካልካባ በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን፣ ጉባኤው በሁሉም የኮንፌዴሬሽኑ አባል ዞኖች ተደርጎ ከተጠናቀቀ በኋላ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ጉባኤ በመጪው ሚያዝያ የሚደረግ ይሆናል። ይህም ጉባኤው እ.አ.አ ሚያዝያ 23/2023 በዛምቢያ ሉሳካ የሚካሄድ ሲሆን በዚህ ጉባኤ የኮምፌዴሬሽኑ ፕሬዘዳንት ይመረጣል ተብሎ ይጠበቃል። ለዚህም የምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ዞን ድጋፉን ለሃመድ ካልካባ ለመስጠት ቃል ገብተል። ፕሬዘዳንት ሃማድ ካልካባ በበኩላቸው ዞኑ ለሚሰጣቸው ድጋፍ አመስግነው ድጋሚ ከተመረጡ በዞኑ ያለውን የአትሌቲክስ አቅም በደንብ ለመጠቀም እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል። በተጨማሪም ፕሬዘዳንቱ አፍሪካ በዓለም አትሌቲክስ በቂ ተወካይ እንዲኖራትም ጥረት እንደሚያደርጉ አክለዋል። ፕሬዘዳንቱ ‹‹እንደ አትሌትና እንደ ስፖርት ማህበረሰብ ሰላምን መደገፍ አለበን፣ ሰላም ከሌለ ስፖርት አይኖርመም›› ሲሉም ተናግረዋል።
የአትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌዴሬሽን ፕሬዘዳንትና የዞኑ አትሌቲክስ ምክትል ፕሬዘዳንት ረዳት ኮሚሽነር ጄነራል ደራረቱ ቱሉ በበኩሏ፣ በአለም ደረጃ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በውጤት ረገድ የበላይነቱን የሚይዙ ቢሆንም እንደ አገልግሎታቸውና ውጤታቸው በአለም ደረጃ የሚገባቸውን ቦታ አግኝተዋል ተብሎ እንደማይታመን ተናግራለች። ደራርቱ አያይዛም እንደ ምስራቅ አፍሪካና እንደ አጠቃላይ እንደ አፍሪካም ጭምር በአለም አቀፍ አትሌቲክስ ቦታ ማግኘት እንደሚያስፈልግና የሚወጡ ህጎችም ላይ መወያየት እንደሚያስፈልግ አስረድታለች። በአሁኑ ወቅት አፍሪካ በአለም አቀፍ አትሌቲክስ ውስጥ ሶስት ተወካይ እንዳላትና ይህን ቢያንስ ወደ ስድስት ለማሳደግ መስራት አንደሚገባም ገልፃለች። በምስራቅ አፍሪካም የተሻለ አትሌቲክስንና የተሻለ ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራትም ጥረት እንደሚደረግ አክላለች። በተጨማሪም ሁሉም ፌዴሬሽኖች በማዘወተሪያ ቦታዎች መስፋፋት ላይ መስራት አንደሚገባ ስራ አስፈፃሚው በውይይቱ ማሳቱን ደራርቱ አብራርታለች።
የምስራቅ አፍሪካን አትሌቲክስ በጣም እያሰጋ ያለው አበረታች ቅመም(ዶፒንግ) በመሆኑ ይህን ችግር ለመቆጠጠር በርካታ ስራ እንደሚሰራ የተናገረችው ደራርቱ፣ በመጨረሻም ለሃገራችን ሰላም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል ስትል መልዕክቷን አጋርታለች፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 9 /2015