እየሩሳሌም ዘውዱ ትባላለች። ብዙም በሴቶች ተመራጭ ያልሆነውንና ሴቶች ደፍረው የማይገቡበትን ሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ነው ያጠናችው። አሁን ላይ የሥራ መስኳ አድርጋ እየሠራችበት ያለችውም ይሄንኑ ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ ነው። “መስኩ ሴቶች በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ላይ ሆነው መሥራት የሚችሉበት ነው። ጉልበት የሚጠይቅ ባለመሆኑም ሳይከብዳቸው በቀላሉ ይሠሩበታል“ ትላለች ጠቀሜታውን ስታብራራ ።
እየሩሳሌም እንደምትለው ከገቢ አንፃርም ቢሆን በቴክኖሎጂው ሴቶች በሌላ መስክ ሠርተው ከሚያገኙት በብዙ እጥፍ የተሻለ ክፍያ ይገኝበታል። ከወንድ ጓደኞቻቸው ወይም ከትዳር አጋሮቻቸው ጥገኝነት ተላቅቀው ዳጎስ ያለ ደሞዝ በማግኘት በተመቻቸ ሁኔታ ራሳቸውን ሊያስተዳድሩበትም የሚያስችል ነው ። ሥራው በየትኛውም ቦታና ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ሊሠራ የሚችል በመሆኑ የዶላር ክፍያ የሚያስገኝበት ዕድል መኖሩ የሴቷን ገቢ የበለጠ ላቅ ያለ እንዲሆን ያደርግላታል። እንደ ዓለምም ሆነ እንደ አገር ቴክኖሎጂው በደረስንበት ዘመን በእጅጉ ተፈላጊ መሆኑንና ለኢትዮጵያም አስፈላጊ መሆኑን ወጣት እየሩሳሌም ታነሳለች። ይሄ አሁን ላይ ከወንዶች በበለጠ ሁኔታ ሥራ አጥ ለሆኑት ሴቶች መልካም አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭው ዓለም በእጅጉ ተፈላጊ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ በስፋት እንዲሠማሩና እንዲጠቀሙ ያደርጋቸዋል።
ሆኖም እየሩሳሌም እንደምትናገረው በሀገራችን በተለይም ቀደም ባሉት ዓመታት ብዙ ሴቶች ወደ ሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ ሙያ መስክ ደፍረው የሚገቡበት ሁኔታ አልተለመደም ነበር። እሷም ብትሆን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ስትገባ ሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ አጠናለሁ የሚል ዕቅድ አልነበራትም። ሆኖም መስክ መረጣ ሳይገባ በመጀመሪያው ሴሚስተር በጨበጠችው የአጠቃላይ ኢንጂነሪንግ ዕውቀት በኋላ ሀገሪቱ ምን ሊያስፈልጋት እንደሚችል፤ዘመኑ የቴክኖሎጂ መሆኑን፤ ብዙ ሴቶች የሌሉበት ግን ለሴቶች በጣም ጠቃሚ መሆኑንና እሷ እዚህ ላይ ብትሠራ ስኬታማ እንደምትሆን ተረድታ ነው የመረጠችው። ደግሞም እንደ ግንባታና ሌሎች ሙያዎችም ጉልበት የማይጠይቅ ቀላል መሆኑ እንድትመርጠው አነሳስቷታል። ‹‹ስለሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ስንማር ወደድኩት። ምን ምን እንደያዘም መገንዘብ ቻልኩ›› ስትልም በዋናነት ይሄንኑ መስክ በመምረጥ ለመማር መወሰኗን ደጋግማ ትገልፃለች። እናም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የከፍተኛ ትምህርቷን ስትከታተል ሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግን እሷን ጨምሮ ጥቂት ቀድሞ ስለ ቴክኖሎጂው ዕውቀቱ ያልነበራቸው ሴቶች ብቻ በነዚህ መስፈርቶች ለማጥናት መረጡት። ‹‹ለኛ ለሴቶች ግን አብዛኛው የቴክኖሎጂው ትምህርት አዲስ ነበር›› ብትልም በሴት ተማሪዎች በኩል ያለው አቀባበል ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየተሻሻለ መምጣቱን ታነሳለች። ከዓመት ወደ ዓመት ሽግግር ሲደረግም በትምህርት አቀባበል በኩል ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል እየሆኑ መምጣታቸውን ታወሳለች። እንደምታስታውሰው በርካታ ወንዶች ነበሩ ለማጥናት የመረጡት። ግን ወንዶች ቴክኖሎጂውን ሊመርጡ የቻሉበት እውነታ ከሴቶች በእጅጉ ይለይ ነበር። ገና ከጅምሩ እንደተረዳችው ወንዶች ከቴክኖሎጂው ጋር የቀደመ ትውውቅ ነበራቸው።
በመሆኑም ሆን ብለውና እሱን ለመምረጥ አስበው ነው ወደ ዩኒቨርሲቲ የገቡት። እሱን መምረጥ የተሻለ ገቢ እንደሚያስገኝና በሥራ ዓለም ለመሠማራት አስቻይ ሁኔታዎች እንደነበሩትም አሳምረው ያውቁ ነበር። ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮ ቴክኖሎጂውን በሚገባ ያውቁት እንደነበርም በኩራት ሲናገሩ የማድመጥ ዕድሉን አግኝታለች። ‹‹ምክንያቱም እነሱ ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ የፈለጉትን ለማድረግ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል አላቸው። በቤት ውስጥ እንደ ሴቷ የሥራ ጫና የለባቸውም። የቤተሰብ ክልከላም ሳይመለከታቸው ነው የሚያድጉት። ሴቷ ስትሆን በአብዛኞቹ ወላጆች የምትሠራው ሁሉ ክትትል ሊደረግባት ይችላል። እንደ ሶፍት ዌር ያሉት ቴክኖሎጂዎች ላይ ትኩረት ብታደርግ እንደ ሥራ ፈት ወይም እንደባለጌ ልትቆጠርና ላይፈቀድላት ይችላል። ወንዶች ግን ከዚህ ሁሉ ተፅዕኖ ነፃ ናቸው። ከቴክኖሎጂው ጋር የቀደመ ትውውቅ ለማድረግ የረዳቸውም ይህ ነው። በዚህ የተነሳ እሷ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ቴክኖሎጂውን በመረጠችበት ዘመን ወንዶች በብዛት መርጠውት እንደነበር በክፍል ቆይታዋ ታዝባለች። የመረጡት ፈልገውት ነው። ልምምድ ሲያደርጉበት ስለቆዩና በትምህርቱ የጠለቀ ዕውቀት ስለነበራቸው ነው ባይ ናት።
እንዲህም ሆኖ ምን አልባት እንበለጣለን የሚል ስጋት ይሁን ስለማይችሉ ውጤታማ አይሆኑበትም የሚልና ሌላ ምክንያት ኖሯቸው ባይገባትም አንዳንድ ወንዶች ተማሪዎችና መምህራን ጭምር ሴቶች ቴክኖሎጂውን ሊመርጡት ይገባል የሚል ዕምነት አልነበራቸውም። በግልፅ አነጋገር እንዲመርጡት የሚያበረታቱ በፍፁም አልነበሩበትም።
እንዲህም ሆኖ እሷን ጨምሮ ቴክኖሎጂውን የመረጡት የተወሰኑ ሴቶች ከወንዶቹ ተማሪዎች ጋር እራሳቸውን በዕውቀቱ ለማመጣጠን ያደርጉት የነበረው ፉክክር ቀላል አልነበረም። ሴቶች አይችሉትም የሚለውን ጨምሮ ውጤታማ እንዳይሆኑ ይደረጉ የነበሩ ተፅዕኖዎች ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በዩኒቨርሲቲው የነበራቸውን ቆይታ አክብዶባቸዋል ።
በርግጥ አንዳንድ መምህራን በደንብ ሴት ተማሪዎችን የሚያበረታቱበት ሁኔታ ነበር ፤ጠንክረው እንዲማሩ፤ ከወንዶች እኩል እንዲሠሩና ብቃት እንዲኖራቸው በእጅጉም ይደግፋሉ። ነገር ግን በቆይታዋ ከዚህ በተቃራኒው የሆኑ መምህራኖችም እንደነበሩም እየሩሳሌም ትጠቅሳለች። እንደ እሷ እነዚህ ዓይነቶቹ መምህራን ሴት ተማሪዎች በቴክኖሎጂው ዕውቀት አላቸው ብለው አያስቡም።
ምክንያቱ ደግሞ አንድ ፕሮጀክት ሰጥተዋቸው ሠርተው ሲያቀርቡ ቡድናቸው ውስጥ ወንዶች ካስገቡ ያን ፕሮጀክት በውጤታማነት የሠሩት ወንዶች እንጂ ሴቶች እንዳልሆኑ ያስባሉ። በግልጽም ሴቶች ሳይሆኑ ወንዶች ናቸው የሠሩት ሲሉ ይደመጣሉ። ለሴቶች ድካም ዋጋ አይሰጡም። በፍፁምም ሴቶች የሚሠሩ የማይመስላቸው አስተማሪዎች ነበሩ።
‹‹ደክመን ለፍተን የሠራነውን ፕሮጀክት በቡድናችን ውስጥ ወንድ በመቀላቀላችን እናንተ አልሠራችሁትም ያለን መምህርም ገጥሞን ነበር›› ስትልም ቅሬታ አዘል ትዝብቷን ትገልፃለች። የትኛውም ዓይነት ብቃት የሌለው ወንድ በቡድኑ ውስጥ ቢኖርና ከነሱ ይልቅ እሱ በሴቶቹ ድጋፍ በመደገፉ ብቻ የችሎታው ማነስ ቢሸፈንለት ፕሮጀክቱ በውጤታማነት ተሠርቷል ተብሎ የሚታመነው በዚህ ዓይነቱ ደካማ ወንድ ተማሪ መሆኑ ሲያማርራቸው ቆይቷል። እንዲህ ዓይነቱን ሴቶች አይችሉም የሚል የአንዳንድ መምህራኖቻቸውና የአብዛኞቹ ወንድ ተማሪዎች ጭፍን አመለካከት እነሱ በዘዴ ተቋቁመው ማለፋቸውንም ታወሳለች።
ሴቶች በሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ ቴክኖሎጂ ያለንን ብቃት ለመምህራኖቻችን ለማሳየትና የሰጡንን ፕሮጀክት እራሳችን በራሳችን መሥራታችንን እንዲያውቁ ቡድናችንን ሴት ብቻ እናደርግ ነበር›› ትላለች። እሷ እንደምትለው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቴክኖሎጂው ሴቶች ብቃት የላቸውም የሚለው አሉታዊ ተፅዕኖ ተቋቁመው በመስኩ ውጤታማ ለመሆን ሲሠሩ ነው የቆዩት። በመጨረሻም ውጤታማ በመሆን በጥሩ ውጤት ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ በቅተዋል።
ከነዚህ መካከል በቴክኖሎጂው መስክ የተሻለ ዕውቀት ለመቅሰም የሚያስችል የትምህርት ዕድል በማግኘት ኦሮሚያ ጎዳና የተሰኘችው የክፍል ጓደኛዋ ኔዘርላንድ እንዲሁም ቱንጋ ተሰማ የተባለችው ጓደኛዋ ደግሞ ሩዋንዳ መሄዳቸውን ነግራናለች። በተለይ እሷ ከዩኒቨርስቲው ትምህርቷን በጥሩ ውጤት አጠናቅቃ በፈረንጆቹ በ2020 መመረቋንም ታወሳለች ።
‹‹እንዴውም በሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ መስክ በቂ ዕውቀት ስላለኝ በሥራ የተሠማራሁት ከመመረቄ በፊት ነው ›› ብላናለችም እየሩሳሌም። እንደነገረችን ከመመረቃቸው በፊት ለልምምድ Vintage technologies የተሰኘ ካንፓኒ ይወጣሉ። ካንፓኒው እሷና ሌሎች ሴት ጓደኞቿ በሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ ብቃት እንዳላቸው ፈጥኖ ነው የተገነዘበው። በመሆኑም ለልምምድ የሚሰጥ ሥራ ሳይሆን ውጭ የሚወጡ ሥራዎችን ይሰጣቸው ጀመር። በሙያው ገቢ ማግኘት የጀመረችው ከዚህ ጀምሮ ነበር። ተመርቃ እንደወጣች ልምምድ ታደርግበት የነበረው ይሄው ካንፓኒ የቅጥር ጥያቄ አቀረበላት። በሥራ ፍለጋ ያጠፋችው ጊዜ ሳይኖር ፈጥና በመቀላቀልም ዳጎስ ያለ ደሞዝ ተከፋይ ሆነች። ትንሽ እንደሠራች አሁን ላይ እየሠራችበት ያለው JSI inc. የተሰኘ ካንፓኒ ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድራ በማሸነፍ ቀድሞ ትሠራበት ከነበረው በእጅጉ በተሻለ ደሞዝ ለመቀጠር በቃች። አሁን በምታገኘው በሌሎች የሙያ መስኮች ተሰማርቶ ከሚገኘው በእጅጉ የተሻለና ዳጎስ ያለ በጥሩ ሁኔታ ራሷንና ቤተሰቧን እያስተዳደረች በዚሁ ገንዘብ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጀሞ አካባቢ የምትኖረው ወጣት እየሩሳሌም በኮቪድ 19 ምክንያት አንድ ሴሚስተር ዘግይታ ብትመረቅም ያጠናችው ሙያ ሥራ አስፈትቶ እቤት ውስጥ የሚያስቀምጥ ባለመሆኑ በቤቷ ውስጥ ተቀምጣ ስትሠራ ቆይታለች። አንዱ ቴክኖሎጂው ለሴቶች የሚሰጠው ጥቅም ቤት ውስጥም ሆነ በየትኛውም ሥፍራ ሊሠሩት የሚችሉት መሆኑ። በተለይ በወሊድ ጊዜ ልጆቻቸውን እያጠቡና እየተንከባከቡ ይተገብሩታል። ሴቶች በይበልጥ ቢሠሩበት የሚፈለገውምና የሚመረጠውም ለዚህ ነው።
እየሩሳሌም ይሄን ታሳቢ አድርጋም በግሏ በርካታ ሴቶች ቴክኖሎጂውን ምርጫቸው እንዲያደርጉ እየተጋች ትገኛለች። ትጋቷ ዕውቀቷን በተለይ ለጾታ አጋሮቿ በማካፈል የታጀበ ነው። ሴቶች ከፕሮግራሚንግ ጀምሮ ሌሎች የቴክኖሎጂው ዕውቀቶች እንዲኖራቸው በቅጥር በተሠማራችበት የሥራ መስክ ብቻ ሳይሆን በግሏም ነፃ ስልጠና በመስጠት ታግዛቸዋለች። የቴክኖሎጂውን መስክ ቢመርጡትም በተሻለ ሁኔታ ጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሳታሰልስ ግንዛቤ ታስጨብጣለች። ሆኖም ሥራው በኢንተርኔት እንደመሠራቱ በማንኛውም ሁኔታ የሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር እንደሚያስተጓጉለውና በዚህ በኩል እንደ ሀገር መፍትሔ መፈለግ እንደሚገባ ታሳስባለች።
ወጣቷ እንዳወጋችን በቴክኖሎጂው ዳጎስ ያለ ገቢ ከምታገኝበትና ከዋና እና ሴቶችን የሙያው ባለቤት ለማድረግ በግሏ ጭምር ከምትሮጥበት ሥራ በተጓዳኝ ከሌሎች የዕድሜ አቻዎቿ ጋር በመቀናጀት በቴክኖሎጂ ሥራ ለሀገሯም አስተዋፅዖ አድርጋለች። ይሄውም ‹‹የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አስተዳደር የመረጃ ቋት›› በመሰኘት የበለፀገ ሶፍት ዌር ነው። አሁን ላይ ወደ አገልግሎት የገባው ይሄ ቋት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪና አገልግሎት ፈላጊን በመመዝገብ ከመስፈርቶቹ ጋር ሊስማማ የሚችል አገልግሎት ሰጪና ተቀባይን የሚያገናኝ ሲሆን በተለይ የመረጃ ተደራሽ በመሆን ረገድ ብዙ ችግሮች ያሉባቸውን ሴቶች የበለጠ እንደሚጠቅም ታወሳለች።
‹‹በጎ ፈቃድ ላይ ብሠራም ሥራው የሚገኝበትን ሥፍራ በቀላሉ ለመለየትና ለማወቅ ለብዙ ዓመታት በእጅጉ ስቸገር ቆይቻለሁ›› የሚሉት ወይዘሮ እናኑ ሁሴን ወጣቷ ከዕድሜ አቻዎቿ ጋር በመሆን የፈበረከችው ቴክኖሎጂ በእጅጉ እንደጠቀማቸው ያወሳሉ። እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ‹‹ዳንፌ›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሥርተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ወይዘሮ እናኑ ‹‹እኔ ተደራሽ ላደርጋቸው የምፈልጋቸውን ግን ደግሞ በመረጃ እጦት ምክንያት ልደርሳቸው ያልቻልኳቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንዳደርግ አስችሎኛልም›› ይላሉ። ሴቶች በቴክኖሎጂው መሳተፋቸው የበለጠ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ማስቻሉን ያስገነዘባቸው መሆኑን ያስረዳሉ ።
የ‹‹ቤተ ሳይዳ›› በጎ አድራጎት ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ በቀለም የወይዘሮ እናኑን ሀሳብ ይጋራሉ። በተለይ ሴቶች በማኅበረሰቡ ካለባቸው የተለያየ ተፅዕኖ አንፃር ለእንዲህ ዓይነቱ ሶፍት ዌር የማበልፀግ ቴክኖሎጂ ሙያ መቅረብ ሳይችሉ ቀርተው መኖራቸውን ያወሳሉ። በዚህም እራሳቸውንም ሆነ ሌሎች ሴቶችን መጥቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ብዙ ሴት ወጣቶች አሁን ድረስ በማኅበረሰቡ ውስጥ በተለይም በወንዶች ዘንድ ባለ ሴቶችን ከቴክኖሎጂው የማራቅ አስተሳሰብ ተፅዕኖ አሁንም ወደ ሙያው መግባት የሚፈሩ በርካታ ሴቶች መኖራቸውንም በተለያየ አጋጣሚ መታዘባቸውን ይናገራሉ። ወጣቷ እየሩሳሌም ደፍራና የቴክኖሎጂው ለሀገርና ለወገን በተለይም ለሴቶች ያለውን ጥቅም ተረድታ ወደ ቴክኖሎጂው በመቅረቧና አመለካከቱን በተግባር በመስበሯ እሳቸው የሚፈልጉትን መረጃ ማግኘት ማስቻሏንም በማሳያነት ያነሳሉ። በተለይ ቴክኖሎጂው ሴቶች በማኅበረሰብ ውስጥና በተፈጥሮ ልጅ መውለድና መንከባከብ እንዲሁም ካሉባቸው ከሌሎች ኃላፊነቶች አንፃር ቤት ውስጥና የተለያየ አካባቢ ሆኖ መሥራት የሚያስችላቸው መሆኑ ፋይዳውን ያጎላዋል። ዳጎስ ያለ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል መሆኑም ራሳቸውን ያለማንም እርዳታ እንዲያስተዳድሩና የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ያስችላል ብለውናል። እኛም ሀሳባቸውን ሁሉም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መለወጥና መሻሻል ብሎም ሀገራቸውን ማራመድ የሚፈልጉ ዜጎች እንዲገዙት በመመኘት ጽሑፋችንን ደመደምን ።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥር 9 /2015